ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፰


ምዕራፍ ፰

ኃይለኛ ነፋስ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ እሳት፤ አውሎ ነፋስ እናም ታላቁ ጥፋት የክርስቶስን ስቅለት መሰከሩ—ብዙ ሰዎች ጠፉ—ምድርን ለሦስት ቀናት ጨለማ ሸፈናት—በህይወት የተረፉት ሰዎች በዕድላቸው አማረሩ። ፴፫–፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እንግዲህ እንዲህ ሆነ በምዝገባችን መሰረት፣ እናም ምዝገባችን እውነት መሆኑን እናውቃለን፣ ምክንያቱም እነሆ፣ መዛግብቱን የጠበቀው ፃድቅ ሰው ነበርና—እርሱም በኢየሱስ ስም ብዙ ታምራቶችን በእውነት አድርጓል፤ እናም ሁለንተናውን ከክፋት ካላነፃው በስተቀር በኢየሱስ ስም ተአምራት ሊሰራ የሚቻለው ማንም ሰው አልነበረም—

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ፣ በዚህ ሰው የጊዜአችን አቆጣጠር የተሳሳተ ካልሆነ፣ ሠላሳ ሦስተኛው ዓመት አልፏል፤

እናም ህዝቡ በላማናዊው ነቢዩ ሳሙኤል የተሰጠውን ምልክት፣ አዎን፣ በዚያ ጊዜም በምድሪቱ ገጽ ለሦስት ቀናት ጨለማ ለሚሆንበት በታላቅ አትኩሮት መመልከት ጀመሩ።

እናም ብዙ ምልክቶች የተሰጡም ቢሆን፣ በህዝቡ መካከል ታላቅ መጠራጠር፣ እናም ፀብ መሆን ጀሞሮ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በሠላሳ አራተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር፣ በወሩ በአራተኛው ቀን፣ በምድሪቱ ሁሉ በጭራሽ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ውሽንፍር ተነሳ።

እናም ደግሞ ታላቅና አስፈሪ የሆነ ኃይለኛ ነፋስም ነበር፤ እናም ምድሪቱን በሙሉ ሲያንቀጠቅጥ የምትከፈት እስከሚመስል የሚያስፈራ ነጎድጓድ ነበር።

እናም በምድሪቱ ከዚህ በፊት የማይታወቅ እጅግ ኃይለኛ የሆነ መብረቅ ነበር።

እናም የዛራሄምላ ከተማ ተቃጠለች።

እናም የሞሮኒ ከተማ በባህሩ ውስጥ ሰጠመች፣ እናም በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ሰጠሙ።

እናም የሞሮኒህ ከተማም በአፈር ተሸፈነች፣ ስለዚህ በከተማዋም ፈንታ ታላቅ ተራራ ሆነ።

፲፩ እናም በምድሪቱ በስተደቡብ በኩል ታላቅና የሚያስፈራ ጥፋት ነበር።

፲፪ ነገር ግን እነሆ፣ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ይበልጥ ታላቅና አስፈሪ የሆነ ጥፋት ነበር፤ እነሆም፣ በኃይለኛው ነፋስና፣ በአውሎ ነፋሱ፣ እናም በነጎድጓዱና መብረቁ፣ እንዲሁም በምድሪቱም እጅግ ታላቅ በሆነው መንቀጥቀጥ የምድሪቱ ገፅታ በሙሉ ተለውጦ ነበር፤

፲፫ እናም አውራ ጎዳናዎች ተሰነጣጥቀው ነበር፣ እናም የተስተካከለው መንገድም ተበላሽቶ ነበር፤ ለጥ ያሉ ብዙ ስፍራዎች ጎርባጣ ሆኑ።

፲፬ እናም ብዙ ታላላቅና ታዋቂ ከተሞች ሰጠሙ፣ እናም ብዙዎችም ተቃጠሉና በከተሞቹ ያሉት ህንፃዎች በመሬት ላይ እስከሚወድቁ ድረስ ተንቀጠቀጡና፣ በዚያ የነበሩት ነዋሪዎችም ተገደሉ እናም ስፍራው ባዶ ሆነ።

፲፭ እናም ጥቂት ከተሞችም ተርፈው ነበር፤ ነገር ግን የነበረው ጉዳት እጅግ ታላቅ ነበር፤ እናም በእነርሱም ውስጥ ብዙ የተገደሉ ነበሩ።

፲፮ እናም በአውሎ ነፋሱ የተወሰዱም ጥቂቶች ነበሩ፤ እናም ከመወሰዳቸው በቀር ወዴት እንደሄዱ የሚያውቅ ማንም አልነበረም።

፲፯ እናም ኃያሉ ነፋስ፤ እናም ነጎድጓድና፣ መብረቅና፣ በመሬት መንቀጥቀጡ የተነሳ ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ገፅታዋ ተለወጠ።

፲፰ እናም እነሆ፣ አለቶቹም ተሰነጣጠቁ፤ በምድረ ገፅ ላይም ሁሉ ተሰባበሩ፤ በዚህም የተነሳ በምድሪቱ ገፅ ላይ ሁሉ የተቆራረጡ ብጥስጣሽና በቀጭኑ የተሰነጣጠቁ፣ እናም ፍርክስካሽ ሆነው ተገኙ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ነጎድጓዱም፣ መብረቁም፣ ውሽንፍሩም፣ ኃያሉ ነፋስ፣ እናም የመሬት መንቀጥቀጡ በቆመበት ጊዜ—እነሆም የቆየውም ለሦስት ሰዓታት ነበር፤ ጥቂት ሰዎችም ከዚህ በበለጠ ቆይቷል ብለው ተናግረዋል፤ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ታላቅና አስፈሪ ነገሮች ሁሉ የተከናወኑት ለሦስት ሰዓታት ነበር—እናም ከዚያ በኋላ እነሆ፣ በምድሪቱ ገፅ ላይ ጨለማ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ገጽ ሁሉ ላይም ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ያልሞቱት በዚያን ስፍራ የነበሩትም ነዋሪዎች የጨለማው ጭጋግ ሊሰማቸው ይችሉ ነበር፤

፳፩ እናም በጨለማውም የተነሳ ምንም ብርሃን ሊሆን አልቻለም ነበር፤ ሻማም ሆነ ችቦም በማንም ሰው ሊቀጣጠል አልቻለም፤ በምርጡ እናም እጅግ ደረቅ በሆነው እንጨትም እሳት ሊቀጣጠል አልቻለም፤ ስለዚህ ባጠቃላይ ምንም ብርሃን ሊሆን አልቻለም፤

፳፪ እናም በምድሪቱ ገፅ ላይ የነበረው የጨለማ ጭጋግ እጅግ ታላቅ በመሆኑ እሳትም ሆነ ጭላንጭል፤ ፀሐይም ሆነ ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት አይታዩም ነበር።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ለሦስት ቀናትም ምንም አይነት ብርሃን አልታየም ነበር፤ እናም በህዝቡ ሁሉ መካከልም የማያቋርጥ ሀዘንና፣ ጩኸት፣ እንዲሁም ለቅሶ ነበር፤ አዎን በጨለማውና በላያቸው ላይ በመጣው ታላቅ ጥፋት የተነሳ የህዝቡ ለቅሶ ታላቅ ነበር።

፳፬ እናም በአንድ ስፍራም እንዲህ በማለት ሲጮኹ ተሰምተዋል፥ ከዚህ ታላቅና አስፈሪ ከሆነው ቀን በፊት ንሰሃ ብንገባ ኖሮ፤ እናም ወንድሞቻችን ይተርፉና በታላቁ የዛራሄምላም ከተማም በእሳቱ ባልተቃጠሉም ነበር።

፳፭ እናም በሌላ ስፍራ እንዲህም በማለት ሲጮኹና፣ ሲያዝኑ ተሰምተዋል፥ ከዚህ ታላቅና አስፈሪ ከሆነው ቀን በፊት ንሰሃ ብንገባ፣ እናም ነቢያትን ባንገድል፣ እንዲሁም በድንጋይ ባንወግራቸው፣ እንዲሁም ባንወረውራቸው ኖሮ፤ ስለዚህ እናቶቻችንና፣ መልካም የሆኑት ሴቶች ልጆቻችንና ልጆቻችን ይተርፉ ነበር፤ እናም በታላቋ የሞሮኒሀ ከተማ አይቀበሩም ነበር። እናም የህዝቡም ጩኸት እንደዚህ ታላቅና አስፈሪ ነበር።