ምዕራፍ ፲፫
ኢየሱስ ለኔፋውያን የጌታን ፀሎት አስተማረ—በሰማይ ሀብትን ማስቀመጥ ይገባቸዋል—አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ወቅት ስለጊዜያዊ ነገሮች እንዳያስቡ ታዘዙ—ማቴዎስ ፮ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ ለድሆች ምፅዋት እንድትሰጡ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለበለዚያ በሰማይ ካለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ አይኖራችሁም።
፪ ስለዚህ፣ ምፅዋታችሁን ስትሰጡ ግብዞች በሰዎች ዘንድ ክብር ይኖራቸው ዘንድ በምኩራብ እናም በጎዳናዎች እንደሚያደርጉት መለከት አታስነፉ። እውነት እላችኋለሁ እነርሱ ዋጋቸውን አግኝተዋል።
፫ ነገር ግን መፅዋዕትን በምትሰጡበት ጊዜ ቀኝ እጃችሁ ግራ እጃችሁ የሚያደርገውን አይወቅ፤
፬ ምፅዋታችሁ በስውር እንዲሆን፤ እናም በስውር የሚያያችሁ አባታችሁ በግልፅ ይከፍላችኋል።
፭ እናም በምትፀልዩበት ጊዜ እንደግብዞች አትሁኑ፤ ምክንያቱም እነርሱ በምኩራብ እናም በየመንገዱ ዳርቻ በመቆም በሰዎች ለመታየት መፀለይን ይወዳሉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
፮ ነገር ግን በምትፀልዩበት ጊዜ ወደ እልፍኛችሁ ውስጥ ግቡ፣ እናም በራችሁንም በምትዘጉበት ጊዜ፣ በስውር ወዳለው አባታችሁ ፀልዩ፣ እናም በስውር የሚያያችሁ አባታችሁ በግልፅ ይከፍላችኋል።
፯ ነገር ግን አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንደሚሰሙ ይመስላቸዋልና፣ በምትፀልዩበት ጊዜ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።
፰ ስለዚህ እናንተ እንደ እነርሱ አትምሰሉ፣ ምክንያቱም አባታችሁን ከመጠየቃችሁ በፊት ምን እንደምትፈልጉ ያውቃልና።
፱ ስለዚህ እንዲህ ብላችሁ ፀልዩ፥ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።
፲ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን።
፲፩ እናም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን፤
፲፪ ከክፉ አድነን እንጂ፣ እናም ወደ ፈተናም አታግባን።
፲፫ መንግሥት ያንተ ናትና፣ እና ሀይልም፣ ክብርም ለዘላለሙ አሜን።
፲፬ ለሰዎች በደላቸውን ይቅር የምትሉ ከሆነ፣ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ ይቅር ይላችኋል፤
፲፭ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።
፲፮ ከዚህም በተጨማሪ፣ በምትጾሙበት ጊዜ ፊታቸውን እንደሚያጠወልጉት እንደግብዞች አትሁኑ፤ ምክንያቱም ለሰዎች እንደፆመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠወልጋሉና። እውነት እላችኋለሁ፣ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
፲፯ ነገር ግን እናንተ በምትጾሙበት ወቅት ራሳችሁን ተቀቡ፤ እናም ፊታችሁን ታጠቡ፤
፲፰ በስውር ላለው አባታችሁ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ፤ በስውር የሚያያችሁ አባታችሁም በግልፅ ዋጋችሁን ይከፍላችኋል።
፲፱ ብልና ዝገት በሚያጠፉት፣ ሌቦችም ቆፍረው በሚሰርቁት፣ ለራሳችሁ በምድር ላይ ሀብትን አታከማቹ፤
፳ ነገር ግን ብልና ዝገት የማያጠፋውን፣ እናም ሌቦች ቆፍረው የማይሰርቁትን፣ ለራሳችሁ የሚሆን ሀብትን በሰማይ አከማቹ።
፳፩ ሀብታችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
፳፪ የሰውነት ብርሀን ዐይን ናት፤ ስለዚህ ዐይናችሁ ቀና ብትሆን ሰውነታችሁ ሁሉ ብሩህ ይሆናል።
፳፫ ነገር ግን ዐይናችሁ ክፉ ብትሆን ሰውነታችሁ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። ስለዚህ በእናንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ቢሆን ጨለማው እንዴት የበረታ ይሆናል!
፳፬ ማንም ሰው ለሁለት ጌቶች ማገልገል አይቻለውም፤ ምክንያቱም አንዱን ይጠላልና ሌላኛውን ይወዳል፣ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል፣ እናም ሌላኛውን ይንቃል። እግዚአብሔርን ማገልገልና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።
፳፭ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በሚናገርበት ወቅት ወደ መረጣቸው አስራ ሁለቱ ተመለከተ፣ እናም እንዲህ አላቸው፥ የተናገርኳቸውን ቃላት አስታውሱ። እነሆም፣ እናንተ ህዝብን እንድታገለግሉ የመረጥኳችሁ ናችሁ። ስለዚህ ስለህይወታችሁ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ስለሰውነታችሁ በምትለብሱትም አትጨነቁ። ህይወት ከመብል እንዲሁም ሰውነት ከልብስ አይበልጥምን?
፳፮ ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ የተሻላችሁ አይደላችሁምን?
፳፯ ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማነው?
፳፰ እናም ስለልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤
፳፱ እናም ግን እንዲህ እላችኋለሁ፣ ሰለሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደአንዱ አልለበሰም።
፴ ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሳር በዚህ ሁኔታ የሚያለብሰው ከሆነ፣ እናንተም እምነት የጎደላችሁ ካልሆናችሁ እንዲሁ እናንተንም ያለብሳችኋል።
፴፩ ስለዚህ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ ምንም አታስቡ።
፴፪ የሰማይ አባታችሁ እነዚህን ነገሮች በሙሉ እንደምትፈልጉ ያውቃልና።
፴፫ ነገር ግን በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን መንግስትና ፅድቁን ፈልጉ፣ እናም እነዚህ ነገሮች በሙሉ ይጨመሩላችኋል።
፴፬ ስለዚህ ነገ ለራሱ ነገሮች ይጨነቃልና ለነገ ምንም አትጨነቁ። ለክፋቱ ቀኑ ብቁ ነውና።