ምዕራፍ ፲፱
አስራ ሁለቱ ደቀመዛሙርት ህዝቡን አስተማሩና መንፈስ ቅዱስንም እንዲቀበሉ ፀለዩ—ደቀመዛሙርቱም ተጠመቁና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ እናም የመላዕክት አገልግሎትንም ተቀበሉ—ኢየሱስ ሊፃፉ የማይችሉ ቃላትን በመጠቀም ፀለየ—ስለነዚህ የኔፋውያንንም እጅግ ታላቅ የሆነ እምነት መሰከረ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ፣ ህዝቡ ተበታተነና፣ እያንዳንዱም ሰው ሚስቱንና ልጆቹን በመያዝ ወደ ቤቱ ተመለሰ።
፪ እናም ህዝቡም ኢየሱስን እንደተመለከቱትና እርሱ እንዳስተማራቸው፣ እናም ደግሞ በሚቀጥለው ቀን እራሱን እንደሚያሳይ ከምሽቱ በፊት ወሬው በህዝቡ መካከል ተዳረሰ።
፫ አዎን፣ እናም ኢየሱስን በተመለከተ በምሽት ሁሉ ወሬው በፍጥነት ተዳረሰ፤ አዎን፣ በሚቀጥለውም ቀን ኢየሱስ እራሱን ለህዝቡ በሚያሳይበት ስፍራ ይሆኑ ዘንድ እጅግ ብዙ ቁጥር ወዳላቸው ሰዎች ተልኮ ምሽቱን ሁሉ ተግተው ሰሩ።
፬ እናም እንዲህ ሆነ በሚቀጥለውም ቀን፣ ህዝቡ በተሰበሰበ ጊዜ፤ እነሆ፣ ኔፊና ከሞት ያስነሳው ወንድሙ ስሙም ጢሞቴዎስ የተባለውና፣ ደግሞ ዮናስ ተብሎ የሚጠራው ልጁ፣ እናም ደግሞ ማቶኒና፣ ወንድሙ ማቶኒያህ፣ እናም ቁመንና፣ ቁመኖንሒ፣ ኤርሚያስም፣ ሼምኖንም፣ ዮናስም፣ ሴዴቅያስም፣ እናም ኢሳይያስ—እንግዲህ እነዚህም ኢየሱስ የመረጣቸው የደቀመዛሙርቱ ስሞች ነበሩ—እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ወደ ፊት ሄዱና በህዝቡ መካከል ቆሙ።
፭ እናም እነሆ፣ ህዝቡም በጣም ብዙ ነበር ስለዚህ በአስራ ሁለት ቡድን ቦታ እንዲከፈሉ አደረጉ።
፮ እናም አስራ ሁለቱም ህዝቡን አስተማሩ፤ እናም እነሆ፣ ህዝቡም በጉልበቱ ወደታች ምድር ገፅ ላይ እንዲንበረከኩና፣ በኢየሱስ ስም ወደ አብ እንዲፀልዩ አደረጉ።
፯ እናም ደቀመዛሙርቱም እንዲሁ በኢየሱስ ስም ወደ አብ ፀለዩ። እናም እንዲህ ሆነ ተነሱና ህዝቡን አስተማሩ።
፰ እናም ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት ባስተማሩ ጊዜ—ቃላቶቹ ኢየሱስ ከተናገራቸው የተለዩ አልነበሩም—እነሆ፣ በድጋሚ ተንበረከኩና በኢየሱስ ስም ወደ አብ ፀለዩ።
፱ እናም ይበልጥ ስለሚፈልጉትም ፀለዩ፤ እናም መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣቸው ይፈልጉ ነበር።
፲ እናም እንደዚህ በሚፀልዩም ጊዜ ወደ ውኃው ጠርዝ ወረዱና ብዙ ህዝብም ተከተላቸው።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊ ወደ ውኃው ወረደና ተጠመቀ።
፲፪ እናም ከውኃው ወጣና ማጥመቅ ጀመረ። እናም ኢየሱስ የመረጣቸውን በሙሉ አጠመቃቸው።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም በተጠመቁና ከውኃ በወጡ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ላይ ወረደ፣ እናም በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ተሞልተው ነበር።
፲፬ እናም እነሆ፣ በእሳት እንደተከበቡ ያህል ሆነው ነበር፤ እናም እርሱም ከሰማይ ወረደና ህዝቡም ይህንን ተመልክቷል፣ ምስክርነታቸውንም ሰጡ፤ እናም መላዕክት ከሰማይ ወረዱና አስተማሩአቸው።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ መላዕክት ለደቀ መዛሙርቱ በሚያስተምሩአቸው ጊዜ፣ እነሆ፣ ኢየሱስ መጣ እናም በመካከላቸው ቆመና፣ አስተማራቸው።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡንም ተናገረና፣ በድጋሚም በመሬት ላይ እንዲንበረከኩ፣ እናም ደግሞ ደቀመዛሙርቱም በመሬት ላይ እንዲንበረከኩ አዘዛቸው።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም በመሬት ላይ በተንበረከኩም ጊዜ፣ ደቀመዛሙርቱም እንዲፀልዩ አዘዛቸው።
፲፰ እናም እነሆ፣ መጸለይ ጀመሩ፤ እናም እርሱን ጌታቸውና አምላካቸው በማለት በመጥራት ወደ ኢየሱስ ፀለዩ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም ከመካከላቸው ወጥቶ ተለይቶአቸው ሄደና፣ ከእነርሱ ትንሽ ራቅ ብሎ ተራመደ፣ እናም ወደ መሬት አጎነበሰና፣ እንዲህ አለ፥
፳ አባት ሆይ፣ እኔ ለመረጥኳቸው ለነዚህ መንፈስ ቅዱስ ስለሰጠሃቸው አመሰግንሃለሁ፤ እናም በእኔም ባላቸው እምነት ምክንያት ነው ከዓለም የመረጥኳቸው።
፳፩ አባት ሆይ፣ በቃላቸው ለሚያምኑት ሁሉ መንፈስ ቅዱስህን ትሰጣቸው ዘንድ እፀልያለሁ።
፳፪ አባት ሆይ፣ በእኔም ስለሚያምኑ መንፈስ ቅዱስ ሰጥተሃቸዋል፤ እናም ሰምተሃቸዋልና በእኔም እንደሚያምኑ ተመልክተሃል፣ እነርሱም ወደ እኔም ፀልየዋል፤ እናም ከእነርሱም ጋር በመሆኔ ወደ እኔ ፀልየዋል።
፳፫ እናም እንግዲህ አባት ሆይ፣ ስለ እነርሱና ደግሞ በእነርሱ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ በእኔ ያምኑ ዘንድ፣ አብ ሆይ፣ አንተ በእኔ እንዳለህ፣ እኔም በእነርሱ እሆን ዘንድ እኛም አንድ እንሆን ዘንድ፣ ስለእነርሱ እፀልያለሁ።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ወደ አብ በፀለየ ጊዜ፣ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣ፣ እናም እነሆ፣ ወደ እርሱ መፀለያቸውን አሁንም ሳያቋርጡ ይቀጥሉ ነበር፤ ምን መፀለይ እንዳለባቸው ስለተገለፀላቸውም በፀሎታቸው ብዙ ቃላት አይናገሩም ነበር፣ በፍላጎትም ተሞልተው ነበር።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ወደ እርሱ በሚፀልዩበት ጊዜ ባረካቸው፤ የፊቱም ፈገግታ በላያቸው ላይ ነበር፣ የፊቱም ብርሃን ያንፀባርቅባቸው ነበር፣ እናም እነሆ እነርሱም እንደገፅታውና ደግሞ እንደ ኢየሱስ መጎናፀፊያ ነጭ ነበሩ፤ እናም እነሆ ንጣታቸውም ከነጭ ነገር ሁሉ እጅግ የበለጠ ነበር፤ አዎን፣ በምድር ላይም በዚያ ከነበረው ንጣት የበለጠ ሊሆን አይቻለውም ነበር።
፳፮ እናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ ፀልዩ፤ ይሁን እንጂ ፀሎታቸውን አላቋረጡም ነበር።
፳፯ እናም በድጋሚ ከእነርሱ ተመለሰ፤ ጥቂትም ራቅ ብሎ ሄደና በመሬትም ላይ አጎነበሰ፤ እናም እንዲህ ሲል በድጋሚ ወደ አብ ፀለየ፥
፳፰ አባት ሆይ፣ የመረጥኳቸውን በእምነታቸው የተነሳ ስላነፃሃቸው አመሰግንሃለሁ፣ ለእነርሱ እናም ደግሞ በቃላቸው ለሚያምኑ በቃላታቸው እምነት በእኔ እንደተነጹም፣ በእኔ እንዲነጹ ዘንድ ለእነርሱ እፀልያለሁ።
፳፱ አባት ሆይ፣ በእምነታቸው የተነሳ በእኔ ይነጹ ዘንድ፤ አብ ሆይ፣ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔና አንተም አንድ እንደሆንን፣ እኔም በእነርሱ እሆን ዘንድ፤ በእነርሱም እከብር ዘንድ ስለዓለም ሳይሆን፣ ከአለም ስለሰጠኸኝ ነው የምጸልየው።
፴ እናም ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ በድጋሚ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣ፤ እናም እነሆ ያለማቋረጥ በፅናት ወደ እርሱ ፀለዩ፤ እርሱም በእነርሱ ላይ ፈገግ አለባቸው፤ እናም እነሆ እነርሱ እንደ ኢየሱስ ነጭ ነበሩ።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ ትንሽ ራቅ በሎ ሄደና፣ ወደ አብም ፀለየ፤
፴፪ እናም በፀሎቱ የነበሩትን ቃላት አንደበት ሊናገራቸው፣ ወይም የጸለያቸውን ቃላት ሰው ሊፅፈው አይቻለውም።
፴፫ እናም ህዝቡ አዳመጡና መሰከሩ፤ እናም ልባቸውም ተከፈተና የፀሎቱን ቃላት በልባቸው ተረዱት።
፴፬ ይሁን እንጂ፣ የፀሎቱ ቃላትም እጅግ ታላቅና አስገራሚ ስለነበሩ በሰው ሊፃፉም ሆነ ሊነገሩ አይችሉም።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም ፀሎቱን በጨረሰ ጊዜ በድጋሚ ወደ ደቀመዛሙርቱ መጣ፣ እናም እንዲህ አላቸው፤ በአይሁዶች ሁሉ መካከል እንደዚህ ያለ ታላቅ እምነት በጭራሽ አላየሁም፤ ስለሆነም ስለማያምኑ እንደዚህ የሆነ ታላቅ ተአምራት ላሳያቸው አልቻልኩም።
፴፮ እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ እንዳያችሁት እንደዚህ ታላቅ ነገሮችን የተመለከተ ከእነርሱ ማንም የለም፤ እንደሰማችሁት ታላቅ ነገሮችንም እነርሱ አልሰሙም ነበር።