ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፬


ምዕራፍ ፬

የኔፋውያን ወታደሮች የጋድያንቶን ዘራፊዎችን አሸነፉ—ጊድያንሒ ተገደለ፣ እናም ተከታዩ ዜምነሪያህ ተሰቀለ—ኔፋውያን ለድላቸው ጌታን አወደሱ። ፲፱–፳፪ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በአስራ ስምንተኛው ዓመት መጨረሻ የዘራፊዎቹ ወታደሮች ለጦርነት ተዘጋጁ፤ እናም በድንገት ከኮረብታው ላይ ገሰገሱና፣ ከተራራውም፣ ከምድረበዳውና፣ ከጠንካራው ምሽጋቸው፣ እንዲሁም ከሚስጢራዊው ስፍራዎቻቸው መበታተን ጀመሩ፤ እናም በምድሪቱ በስተደቡብና በምድሪቱ በስተሰሜን ያለውን ምድር መውሰድ ጀመሩ፤ እናም በኔፋውያን የተተዉትን ምድሮች በሙሉና ባዶ የቀሩትን ከተሞች መያዝ ጀመሩ።

ነገር ግን እነሆ፣ በኔፋውያን ከተተዉት ምድሮች ውስጥ የዱር አውሬዎችም ሆኑ የሚታደኑ የሉም፣ እናም ከምድረበዳው በስተቀር በዘራፊዎቹ የሚታደን ምንም አልነበረም።

እናም ምግብ ስለሚያስፈልጋቸው፣ ዘራፊዎቹ ከምድረበዳው በስተቀር ለመኖር አልቻሉም፤ ኔፋውያን ምድራቸውን ባዶ በማድረጋቸው፤ እናም ከብቶቻቸውንና መንጋዎቻቸውንና ሁሉንም ቁሳቁሶቻቸውን በመሰብሰባቸው እነርሱ በአንድነት ነበሩ።

ስለዚህ፣ ከኔፋውያን ጋር ፊት ለፊት ውጊያ ከመምጣት በስተቀር ዘራፊዎቹ ለመዝረፍ እንዲሁም ምግብን ለማግኘት ዕድል አልነበራቸውም፤ ኔፋውያንም አንድ ነበሩ፤ እናም በቁጥርም እጅግ ብዙ ስለነበሩና፣ ቁሳቁሶችንና፣ ፈረሶችን፣ እናም ከብቶችንና፣ ከሁሉም ዐይነት መንጋዎችን በማስቀመጣቸው ለሰባት ዓመታት እንደሚያቆያቸው በመዘጋጀት በነዚህም ዓመታት ዘራፊዎቹን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ተስፋ አድርገው ነበር፤ እናም አስራ ስምንተኛው ዓመት እንደዚህ አለፈ።

እናም እንዲህ ሆነ በአስራ ዘጠነኛው ዓመት ጊድያንሒ ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት መሄዱ አስፈላጊ መሆኑን አወቀ፤ ምክንያቱም ካልዘረፉና፣ ካልሰረቁ፣ እናም ካልገደሉ በስተቀር በህይወት የሚቆዩበት መንገድ ሊኖር አይችልም ነበር።

እናም ኔፋውያን እንዳይመጡባቸውና እንዳይገድሉአቸው፣ በምድሪቱ ገፅ ላይ እራሳቸውን በመበታተን እህል ሊያመርቱ አልደፈሩም፤ ስለዚህ ጊድያንሒ በዚህ ዓመት ወታደሮቹ ከኔፋውያን ጋር ሄደው እንዲዋጉ ትዕዛዝን ሰጠ።

እናም እንዲህ ሆነ ለውጊያው መጥተው ነበር፤ ይህም በስድስተኛው ወር ነበር፤ እናም እነሆ፣ ለውጊያ የሚመጡበትም ቀን ታላቅ፣ እንዲሁም አስፈሪ ነበር፤ እነርሱም የለበሱት እንደዘራፊዎቹ ነበር፤ እናም በወገባቸው ላይ የበግ ቆዳ ታጥቀውና፣ በደም ተነክረው ነበር፣ ራሳቸውንም ተላጭው፣ የራስ ቆብም በላያቸው ላይ ነበራቸው፤ እናም በጦር መሳሪያቸውና በደም በመነከራቸው የጊድያንሒ ወታደሮች አቋም ታላቅ እንዲሁም አስፈሪ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ የኔፋውያን ወታደሮች የጊድያንሒን ወታደሮች አቋም በተመለከቱ ጊዜ ሁሉም በመሬት ላይ ወደቁ፣ እናም ጌታ አምላካቸው ያድናቸውና ከጠላቶቻቸው እጅ ያሰለቅቃቸው ዘንድ ወደ እርሱ ጮሁ።

እናም እንዲህ ሆነ የጊድያንሒ ወታደሮች ይህንን በተመለከቱ ጊዜ ከደስታቸው የተነሳ በሃይል ጮሁ፤ ምክንያቱም ኔፋውያን ወታደሮቻቸውን በመፍራት ይወድቃሉ ብለው ገምተው ስለነበር ነው።

ነገር ግን በዚህ ነገር ተቆጥተዋል፣ ምክንያቱም ኔፋውያን አልፈሩአቸውም ነበርና፤ ነገር ግን አምላካቸውን ፈርተው ነበር፣ እናም እንዲጠብቃቸውም ተማፅነውት ነበር፤ ስለዚህ የጊድያንሒ ወታደሮች ወደ እነርሱ በሮጡ ጊዜ እነርሱን ለመገናኘት ተዘጋጅተው ነበር፤ አዎን፣ በጌታም ብርታት ዘራፊዎቹን ተቀበሉአቸው።

፲፩ እናም ጦርነቱ በስድስተኛው ወር ተጀመረ፤ እናም በዚያ የነበረው ጦርነት ታላቅ እንዲሁም አስፈሪ ነበር፣ አዎን፣ በዚያም የነበረው ግድያ ታላቅ፣ እንዲሁም አስፈሪ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በህዝቡ መካከል እንዲህ ያለ ታላቅ ግድያ በጭራሽ አይታወቅም ነበር።

፲፪ እናም ጊድያንሒ ማስፈራሪያና መሀላ ቢያደርግም፣ እነሆ፣ ኔፋውያን አሸነፏቸው፣ በዚህም የተነሳ ከፊታቸው ማፈግፈግ ጀመሩ።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ጊድጊዶኒ ወታደሮቹ እስከምድረበዳው ዳርቻ እንዲያሳድዱአቸው፤ በእጃቸው የገቡትንም እንዳይተዉአቸው አዘዘ፤ እናም ወደ ምድረበዳው ዳርቻ የጊድጊዶኒ ትዕዛዛት እስከሚፈጸሙ ድረስ አሳደዱአቸውና ገደሉአቸው።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ የቆመውና በድፍረት የተዋጋው ጊድያንሒ በሸሸ ጊዜ ተከተሉት፤ እጅግ ብርቱ በነበረው ጦርነት በመድከሙ ተደረሰበትና ተገደለ። እናም ይህም የዘራፊው ጊድያንሒ መጨረሻ ነበር።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ የኔፋውያን ወታደሮች ወደ ደህንነታቸው ስፍራ በድጋሚ ተመለሱ። እናም እንዲህ ሆነ ይህ አስራ ዘጠነኛ ዓመት አለፈ፤ እናም ዘራፊዎቹ በድጋሚ ለመዋጋት አልመጡም፤ በሀያኛውም ዓመት ቢሆን በድጋሚ አልመጡም።

፲፮ እናም በሃያ አንደኛው ዓመት ለውጊያ አልመጡም፤ ነገር ግን በሁሉም አቅጣጫ በኔፊ ህዝብ ዙሪያ ለመክበብ መጡ፤ የኔፊን ህዝብ ከምድራቸው ከቆረጡአቸውና በሁሉም አቅጣጫ ከከበቡአቸው፣ እናም ከምሽጉ ውጪ ያሉአቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ከከለከሉአቸው፣ እንደፍላጎቶቻቸው እራሳቸውን ለመስጠት እናስገድዳቸዋለን ብለው ገምተው ነበር።

፲፯ እንግዲህ ለራሳቸውም ስሙ ዜምነሪያህ የሚባል ሌላ መሪ ሾመው ነበር፤ ስለዚህ ይህ ዜምናሪያህ ነው የዚህ ዐይነቱ ከበባ እንዲከናወን ያደረገው።

፲፰ ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ለኔፋውያን ጠቃሚ ነበር፤ ምክንያቱም ኔፋውያን በመጋዘናቸው በርካታ ስንቅ በማስቀመጣቸው፣ ዘራፊዎቹ ኔፋውያንን በዙሪያቸውም በሚገባ ለብቁ ጊዜ በመክበብ ምንም አይነት ጉዳት ለማምጣት አስቸጋሪ ነበርና።

፲፱ እናም በዘራፊዎቹ መካከል በነበረው ስንቅ ትንሽነት፤ እነሆም በህይወት ለመቆየት በምድረበዳው ውስጥ ካገኙት ሥጋ በስተቀር ምንም አልነበራቸውም፤

እናም እንዲህ ሆነ የዱር አደኑ በምድረበዳው ውስጥ በቂ አልነበረም፤ በዚህም የተነሳ ዘራፊዎቹ በረሃብ ሊጠፉ ደርሰው ነበር።

፳፩ እናም ኔፋውያን ያለማቋረጥ በቀን እንዲሁም በምሽት እየዘመቱና ወታደሮቻቸውን ያጠቁና በሺህ እናም በአስር ሺህ የሚቆጠሩትን ይገደሉአቸው ነበር።

፳፪ እናም በቀንና በምሽት በእነርሱ ላይ በሆነው ታላቅ ጥፋትም የተነሳ የዜምነሪያህ ሰዎች ዕቅዳቸውን በመተው ለማፈግፈግ ፈልገው ነበር።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ዜምነሪያህ ህዝቡ ከተከበቡበት እንዲያፈገፍጉ እንዲሁም በምድሪቱ በሰሜን በኩል ራቅ ወዳለው ስፍራ እንዲዘምቱ አዘዘ።

፳፬ እናም እንግዲህ፣ ጊድጊዶኒ ስለዕቅዳቸው በመገንዘቡ፣ እናም ምግብ በመፈለጋቸውምና፣ በመካከላቸው በነበረው ታላቅ ግድያ መዳከማቸውን በማወቁ፣ በምሽት ወታደሮቹን ላከና፣ የማፈግፈጊያውን መንገድም አገደባቸው፤ እናም በሚያፈገፍጉበት መንገድም ወታደሮቹን አስቀመጠ።

፳፭ እናም ይህንን ያደረጉት በምሽት ነበር፤ እናም ከዘራፊዎቹ አልፈው ተጓዙ፤ ስለዚህ በሚቀጥለውም ቀን ዘራፊዎቹ መንገዱን በጀመሩበት ጊዜ ከፊለፊት እንዲሁም ከጀርባቸው ከኔፋውያን ወታደሮች ጋር ተገናኝተው ነበር።

፳፮ እናም በስተደቡብ የነበሩትም ሌቦች ከማፈግፈጊያው ቦታ መንገዱ ተገድቦባቸው ነበር። እናም እነዚህ ነገሮች በሙሉ የተደረጉት በጊድጊዶኒ ትዕዛዝ ነበር።

፳፯ እናም ብዙ ሺህዎች ለኔፋውያን ራሳቸውን እስረኛ አድርገው ሰጥተው ነበር፤ እናም ቀሪዎቹም ተገደሉ።

፳፰ እናም መሪአቸው፣ ዜምነሪያህ፣ ተወሰደና በዛፉ ላይ አዎን፣ እስከሚሞት ድረስ በጫፉ ላይ ተሰቀለ። እናም እስከሚሞት ድረስ በሰቀሉት ጊዜም ዛፉን መሬት ላይ ጣሉትና፣ እንዲህም ሲሉ በሀይል ጮሁ፥

፳፱ ይህን ህዝብ በስልጣን እንዲሁም በሚስጥራዊ ሴራዎች የተነሳ እነርሱን ለመግደል ለሚፈልጉ፣ ሁሉ፣ ይህ ሰው በመሬት ላይ ተቆርጦ እንደተጣለው እነርሱንም እንዲቆረጡ ያደርጓቸው ዘንድ ጌታ ህዝቡን በፅድቅ እንዲሁም በልብ ቅድስና ይጠብቃቸው።

እናም ተደሰቱና በድጋሚ በአንድ ድምጽ እንዲህ ሲሉ ጮኹ፥ ይህ ህዝብ የአምላኩን ስም ለጥበቃው እስከጠሩ ድረስ ሁሉ የአብርሃም አምላክ፤ እናም የይስሃቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ በፅድቅ ይጠብቃቸው።

፴፩ እናም እንዲህ ሆነ በጠላቶቻቸው እጅ እንዳይወድቁ በመጠበቅ ታላቅ ነገር ስላደረገላቸው ሁሉም በአንድነት መዘመር እንዲሁም አምላካቸውን ማወደስ ጀመሩ።

፴፪ አዎን፣ ሆሳዕና ለልዑል እግዚአብሔር ብለውም ጮሁ። እናም ልዑል እግዚአብሔር፣ ሁሉን የሚገዛው ጌታ እግዚአብሔር ስሙ የተባረከ ይሁን በማለትም ጮኹ።

፴፫ እናም እግዚአብሔር በታላቅ ቸርነቱ ከጠላቶቻቸው እጅ እንዲወጡ ስላደረጋቸው እንባ እስከሚወጣቸው ድረስ ልባቸው በደስታ ተሞልቶ ነበር፤ እናም ከንስሃቸውና ትሁትነታቸው የተነሳ ከዘላለም ጥፋት መዳናቸውን ያውቁ ነበር።