ምዕራፍ ፳፫
ኢየሱስ የኢሳይያስን ቃላት አጸደቀ—ህዝቡ ነቢያትን እንዲፈልጉ አዘዘ—ላማናዊው ሳሙኤል ስለትንሣኤ የተናገራቸው ቃላት በመዝገቦቻቸው ተጨምረዋል። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህን ነገሮች ፈልጉ። አዎን፣ እነዚህን ነገሮች በትጋት እንድትፈልጉ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ የኢሳይያስ ቃላት ታላቅ ናቸውና።
፪ የእስራኤል ቤት የሆኑትን ህዝቦቼን በተመለከተ፣ ስለሁሉም ነገሮች በእርግጥ ተናግሯል፤ ስለዚህ ለአህዛብ ደግሞ መናገሩ አስፈላጊ ነው።
፫ እናም የተናገራቸው፣ እንዲሁም በተናገራቸው ቃላት መሰረት፣ ሁሉም ነገሮች ሆነዋልም፣ ይሆናሉም።
፬ ስለዚህ ቃሌን ልብ ብላችሁ አድምጡ፤ የተናገርኳችሁንም ነገሮች ፃፉ፤ እናም በአብ ጊዜና ፈቃድ መሰረት እነርሱ ወደ አህዛብ ይሄዳሉ።
፭ እናም ቃሌን የሚሰማና ንሰሃ የሚገባ እናም የሚጠመቅ እርሱ ይድናል። ነቢያትን ፈልጓቸው፣ ስለነዚህ ነገሮች የሚመሰክሩ ብዙዎች በዚያ ናቸውና።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በድጋሚ በተናገራቸው ጊዜ፣ የተቀበሉአቸውን ቅዱሳን መፃህፍት በጥልቀት ካስረዳቸው በኋላ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነሆ፣ እናንተ ያልጻፍኳቸው፣ እንድትፅፉ የፈለግሁት ሌሎች ቅዱሳን መጽሐፍት አሉ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ለኔፊም እንዲህ አለው፥ ያስቀመጥከውን መዝገብ አምጣ።
፰ እናም ኔፊም መዛግብቱን ባመጣና ከፊቱ ባደረገውም ጊዜ፣ ኢየሱስ ተመለከታቸውና እንዲህ አለ፥
፱ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬን ላማናዊውን ሳሙኤል በዛን ቀን አብ በእኔ ስሙን በሚያስከብርበት ጊዜ ብዙ የሞቱ ቅዱሳን እንደሚነሱና ለብዙዎች እንደሚታዩ፣ እናም እነርሱንም እንደሚያስተምሩ ለዚህ ህዝብ እንዲመሰክር አዘዝኩት። እናም ይህ አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው።
፲ እናም ደቀመዛሙርቱ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፥ አዎን፣ ጌታ ሆይ፣ ሳሙኤል በቃልህ መሰረት ተንብዮ ነበር፣ እናም ሁሉም ተፈጽመው ነበር።
፲፩ እናም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ ብዙዎች ቅዱሳን እንደተነሱና፣ ለብዙዎች እንደተገለጡና እነርሱን እንዳስተማሩ እንዴት አልተፃፉም?
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊም ይህ ነገር እንዳልተፃፈ አስታወሰ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም መፃፍ እንዳለበት አዘዘ፤ ስለዚህ እርሱ እንዳዘዘውም ተፃፈ።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስም እነርሱ የፃፉትን ቅዱሳን መጽሐፍትን በሙሉ በአንድ ላይ በአስረዳቸው ጊዜ፣ እርሱም ለእነርሱ ያስረዳቸውን ነገሮች ማስተማር እንዳለባቸው አዘዛቸው።