ምዕራፍ ፶፪
አሞሮን የላማናውያን ንጉስ በመሆን አማሊቅያን ተካው—ሞሮኒ፣ ቴአንኩም፣ እናም ሌሂ ከላማናውያን ጋር ባደረጉት ጦርነት ኔፋውያንን በድል አድራጊነት መሩአቸው—የሙሌቅ ከተማ በድጋሚ ተወሰደች፣ እናም ዞራማዊው ያዕቆብ ተገደለ። ከ፷፮–፷፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሀያ ስድስተኛ የንግስ ዘመን፣ እነሆ፣ በመጀመሪያው ወር በጠዋት ላማናውያን ሲነቁ፣ እነሆ፣ አማሊቅያ በራሱ ድንኳን ውስጥ ሞቶ አገኙት፤ እናም ደግሞ በዚያን ቀን ቴአንኩም ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት ዝግጁ መሆኑን ተመለከቱ።
፪ እናም እንግዲህ፣ ላማናውያን ይህንን በተመለከቱ ጊዜ ፈርተው ነበር፤ እናም ወደ ሰሜን ክፍል ለመዝመት ከነበራቸው ዕቅድ አንፃር ዕቅዳቸውን ተዉት፤ ከወታደሮቻቸው ጋርም ወደ ሙሌቅ ከተማ አፈገፈጉና፣ በምሽጋቸውም ጥበቃን ፈለጉ።
፫ እናም እንዲህ ሆነ የአማሊቅያ ወንድም በህዝቡ ላይ ንጉስ ሆኖ ተሾመ፤ እናም ስሙ አሞሮን ይባል ነበር፤ የአማሊቅያ ወንድም ንጉስ አሞሮን በአማሊቅያ ምትክ እንዲነግስ ተሹሞ ነበር።
፬ እናም እንዲህ ሆነ አሞሮን በደም መፋሰስ የተወሰዱትን ከተሞች ህዝቡ እንዲቆጣጠር አዘዘ፣ የትኞቹንም ከተሞች ብዙ ደም ያለማፋሰስ አልወሰዱም ነበር።
፭ እናም እንግዲህ፣ ቴአንኩም ላማናውያን የወሰዷቸውን ከተሞችና የያዟቸውን ቦታዎች ለመቆጣጠር ቆራጥ ውሳኔ አድርገው እንደነበር ተመለከተ፤ እናም ደግሞ ቴአንኩም በቁጥር እጅግ ብዙ መሆናቸውን በተመለከተ ጊዜ ላማናውያንን በምሽጋቸው ውስጥ እንዳሉ ለማጥቃት መሞከሩ አስፈላጊ አለመሆኑን አሰበ።
፮ ነገር ግን የእርሱ የሆኑትን ሰዎች ለጦርነት ያዘጋጀ በማስመሰል በዙሪያው እንዲሆኑ አደረገ፤ አዎን፣ እናም በኔፋውያን ከተሞች ዙሪያ ግንብ ገነባ፣ እናም ጠንካራ ስፍራን አዘጋጀ፣ ይህንንም ያደረገው በእርግጥ እራሱን ከእነርሱ ለመከላከል ነበር።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ወታደሮቹን ለማጠናከር ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እስከሚልክ ድረስ ለጦርነት መዘጋጀቱን ቀጠለ።
፰ እናም ደግሞ ወደ እርሱ እጅ የገቡትን እስረኞችን በሙሉ እንዲጠብቁ ሞሮኒ መመሪያዎችን ላከ፤ ላማናውያን ብዙ እስረኞችን በመውሰዳቸው፣ ለወሰዱአቸው ማስለቀቂያ ይሆኑ ዘንድ የላማናውያን የሆኑትን እስረኞች እንዲጠብቁ ማድረግ ነበረበት።
፱ እናም ደግሞ የለጋስን ምድር እንዲመሽጋት፣ እናም ላማናውያን ሥፍራዎቹን በመያዝ በሁሉም አቅጣጫ ለማጥቃት ኃይልን እንዳያገኙባቸው፣ ወደሰሜኑ በኩል የሚወስደውን ቀጭኑን ጎዳና እንዲከላከል ትእዛዛትን ላከበት።
፲ እናም ደግሞ ሞሮኒ ያለበትን ምድር በመከላከል ታማኝ እንዲሆን በመፈለጉና፣ በዚያች ምድር ላማናውያንን በሁሉም አጋጣሚ በስልጣኑ እስካለ ድረስ ለማጥቃትና፣ በተገኘው ሥልት ወይንም በሌላ መንገድ ከእጃቸው የወጡትን ከተሞች ዳግም ለመያዝ እድልን እንዲፈልግ፣ እናም ደግሞ በላማናውያን እጅ ያልወደቁትን በዙሪያው ያሉትን ከተሞች ምሽግ እንዲጠናክር ፈልጎት ነበር።
፲፩ እናም ደግሞ እንዲህ አለው፥ ወደ አንተ እመጣ ነበር፣ ነገር ግን እነሆ፣ ላማናውያን በባህሩ በስተምዕራብ በኩል ባለው ምድር ዳርቻ እየመጡብን ነው፤ እናም እነሆ፣ በእነርሱ ላይ እዘምታለሁ፣ ስለዚህ ወዳንተ ልመጣ አልችልም።
፲፪ እንግዲህ፣ ንጉሱ (አሞሮን) ከዛራሔምላ ምድር ወጣ፣ እናም ለንግስቲቱ የወንድሙን መሞት ነገራት፣ እናም ብዙ ሰዎችን በአንድነት ሰበሰበና፣ በባህሩ በስተምዕራብ ዳርቻም በኩል በኔፋውያን ላይ ዘመቱ።
፲፫ እናም ኔፋውያንን ለማጥቃትና ከባህሩ በስተምዕራብ ካለው ዳርቻም ኃይላቸውን እንዲያስወጡ ሞክሮ ነበር፤ እርሱ የወሰዳቸውን ከተሞች እንዲወርሱ የተዋቸውን በባህሩ በምስራቅ ዳርቻ በኩል ደግሞ ኔፋውያንን እንዲያጠቁአቸው፣ እናም እንደ ኃይላቸው፣ በሰራዊቶቻቸው ጉልበት መሰረት የእነርሱን ምድሮች እንዲወስዱም አዝዞአቸው ነበር።
፲፬ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሀያ ስድስተኛ ዓመት ንገሳ መጨረሻ ላይ ኔፋውያን በእንዲህ ያለ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነበሩ።
፲፭ ነገር ግን እነሆ፣ በመሣፍንቱ ሀያ ሰባተኛ ዓመት የንግስ ዘመን ቴአንኩም በሞሮኒ ትዕዛዝ፣ መርኒም የምድሪቱን ደቡብ፣ እና ምዕራብ ዳርቻዎች ለመጠበቅ ወታደሮችን በአቋቋመው፣ እናም ቴአንኩም ከህዝቡ ጋር የተቀማውን ከተሞች በድጋሚ ለማስመለስ ዘመቻውን ወደለጋስ ምድር አድርጎ ነበር፤
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ ቴአንኩም በሙሌቅ ከተማ ላይ ጥቃትን ለማድረግ፣ እናም የሚቻል ከሆነ በድጋሚ ለመውሰድ ትዕዛዝ ተቀበለ።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ቴአንኩም በሙሌቅ ከተማ ላይ ጥቃት ለማድረስ ተዘጋጀ፣ እናም በላማናውያን ላይ ከወታደሮቹ ጋር ለመዝመት ዝግጅት አደረገ፤ ነገር ግን በምሽጋቸው በነበሩበት ጊዜ እነርሱን ማሸነፍ የማይቻል መሆኑን ተመልክቶ ነበር፤ ስለዚህ ለወታደሮቹ ተጨማሪ ኃይልን ያገኝ ዘንድ የሞሮኒን መምጣት ለመጠበቅ ዕቅዱን ተወና፣ ወደለጋስ ከተማ በድጋሚ ተመለሰ።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሀያ ሰባተኛ ዓመት የንግስ ዘመን መጨረሻ ላይ ሞሮኒ ከሠራዊቱ ጋር በለጋስ ምድር ደረሰ።
፲፱ እናም በሀያ ስምንተኛው ዓመት መጀመሪያ፣ ሞሮኒና ቴአንኩም እናም በርካታ ዋና ሻምበሎች ስለጦርነቱ—ላማናውያን ከእነርሱ ጋር እንዲዋጉ ለማስወጣት፤ ወይም ኔፋውያን በጥቂት ዘዴዎች ላማናውያንን ከጠንካራው ምሽጋቸው እንዲያስወጡአቸው በድጋሚም በእነርሱ ላይ ኃይልን ያገኙ ዘንድ፣ እናም በድጋሚ የሙሌቅን ከተማ ለመውሰድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተማከሩ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ የሙሌቅን ከተማ ወደሚጠብቁት የላማናውያን ሠራዊት መሪ ወደሆነው፣ ያዕቆብ ተብሎ ወደሚጠራው፣ ከሠራዊቱ ጋር በሁለቱ ከተሞች መካከል ባለው ባዶ ስፍራ እንዲገናኙ እንደሚፈልጉ መልዕክተኛ ላኩ። ነገር ግን እነሆ፣ ዞራማዊ የነበረው፣ ያዕቆብ፣ በገላጣው ስፍራ ከእነርሱ ጋር ለመገናኘት ከሠራዊቱ ጋር አልመጣም።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ በገላጣው ስፍራ ሞሮኒ እነርሱን እንደሚያገኛቸው ተስፋ ስላልነበረው፣ ስለዚህ፣ ላማናውያንን ከጠንካራው ምሽጋቸው ያወጣቸው ዘንድ አንድን ዕቅድ አዘጋጀ።
፳፪ ስለዚህ ቴአንኩም ጥቂት ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እንዲወስድ፣ እናም በባህሩ ዳርቻ አጠገብ እንዲዘምቱ አደረገ፤ እናም ሞሮኒና፣ ወታደሮቹ በምሽት በሙሌቅ ከተማ በስተምዕራብ በኩል ወደ ምድረበዳው ሄዱ፤ እናም በሚቀጥለው ቀን፣ የላማናውያን ጠባቂዎች ቴአንኩምን ባገኙት ጊዜ፣ ሮጡ፣ እናም ለመሪያቸው ለያዕቆብ ነገሩት።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ወታደሮች በቴአንኩም ላይ ዘመቱ፤ እናም በቁጥርም የቴአንኩም ሰዎችን በቁጥር ትንሽ ስለነበሩ እናሸንፋቸዋለን ብለው ገመቱ። እናም ቴአንኩም የላማናውያን ወታደሮች በእርሱ ላይ መምጣታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ በሰሜን በኩል በባህሩ ዳርቻ ማፈግፈግ ጀመረ።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን እርሱ መሸሹን በተመለከቱ ጊዜ፣ ድፍረትን አገኙና በወኔ ተከታተሉአቸው። እናም በከንቱ የተከተሉአቸውን ላማናውያን ቴአንኩም ባሳደዷቸው ጊዜ፣ እነሆ፣ ሞሮኒ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰራዊቶቹን እንዲዘምቱና ከተማዋን እንዲይዙ አዘዛቸው።
፳፭ እናም እንደዚህም አደረጉና፣ ከተማዋን ለመከላከል የቀሩትን፣ አዎን፣ ሁሉንም የጦር መሳሪያዎቻቸውን ያላስረከቡትን በሙሉ ገደሉአቸው።
፳፮ እናም ቴአንኩምን አሳደውት ከሚመለሱት ላማናውያን ጋር ለመገናኘት ከሚቀሩት ወታደሮች ጋር እየዘመተ እያላ፣ የሞሮኒ ሰራዊት ክፍል እንደዚህ የሙሌቅን ከተማ ያዙ።
፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን በለጋስ ምድር አጠገብ እስከሚመጡ ድረስ ቴአንኩምን ተከተሉት፣ እናም ከሌሂና ለጋስ ከተማን እንዲጠብቁ ከተተዉት ጥቂት ወታደሮች ጋር ተገናኙ።
፳፰ እናም አሁን እነሆ የላማናውያን የጦር አዛዥ ሌሂ ከወታደሮቹ ጋር ወደ እነርሱ መምጣታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ ሌሂ በእነርሱ ላይ ከመድረሱ በፊት የሙሌቅን ከተማ ለመያዝ አንችልም ብለው በመፍራታቸው በድንጋጤ ሸሹ፤ እነርሱም በጉዞአቸውም የተነሳ ደክመው ነበር፣ እናም የሌሂ ሰዎች ግን አልደከሙም ነበር።
፳፱ እንግዲህ ላማናውያን ሞሮኒ ከወታደሮቹ ጋር ከበስተጀርባቸው እንደሆነ አላወቁም ነበር፣ እናም ሁሉም የፈሩት ሌሂንና የእርሱን ህዝቦች ነበር።
፴ እንግዲህ ሌሂ ላማናውያንን ሞሮኒንና ወታደሮቹን እስከሚያገኙ ሊይዛቸው አልፈለገም ነበር።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን እርቀው ከማፈግፈጋቸው በፊት በኔፋውያን፣ በአንድ በኩል በሞሮኒ፣ እናም በሌላ በኩል በሌሂ ሰዎች ተከበው ነበር፤ ሁሉም ነቃ ያሉና በጥንካሬ የተሞሉ ነበሩ፤ ነገር ግን ላማናውያን ብዙ ስለተጓዙም ደክመው ነበር።
፴፪ እናም ሞሮኒ እነርሱ የጦር መሳሪያዎቻቸውን እስከሚያስረክቡ ድረስ ህዝቡ እንዲያጠቃቸው አዘዘ።
፴፫ እናም እንዲህ ሆነ፣ ያዕቆብ፣ መሪያቸው በመሆኑ፣ እንዲሁም ዞራማዊ በመሆኑ፣ እናም የማይሸነፍ መንፈስ ስለነበረው፣ ላማናውያን በኃይል ከሞሮኒ ጋር እንዲዋጉ መራቸው።
፴፬ ሞሮኒ ላማናውያን በሚጓዙበት አቅጣጫ ስለነበረ፣ ስለዚህም ያዕቆብ እነርሱን ለመግደል፣ እናም መንገዱን ወደ ሙሌቅ ከተማ ለመቁረጥ ወስኖ ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ ሞሮኒና ህዝቡ እጅግ ኃይለኞች ነበሩ፤ ስለዚህ ከላማናውያን ፊት አላፈገፈጉም ነበር።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ ከሁለቱም በኩል እጅግ በኃይል ተዋጉ፤ እናም በሁለቱም በኩል ብዙዎች ሞቱ፤ አዎን እናም ሞሮኒ ቆስሎ ነበር፣ ያዕቆብም ተገድሎ ነበር።
፴፮ እናም ሌሂ በኃይል ከጠንካራዎቹ ህዝቦቹ ጋር ከጀርባቸው በሀይል አጥቅቷቸው፣ ላማናውያንም የጦር መሳሪያዎቻቸውን አስረከቡ፤ እናም የተቀሩት እጅግ ግራ በመጋባታቸው ወዴት መሄድም፣ ሆነ እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው አያውቁም ነበር።
፴፯ እንግዲህ ሞሮኒ ግራ መጋባታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ እንዲህ አላቸው፤ የጦር መሳሪያዎቻችሁን ወደዚህ ስፍራ የምታመጡ፣ እናም የምታስረክቡ ከሆነ፣ እነሆ ደማችሁን ማፍሰሳችንን እናቆማለን።
፴፰ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ይህንን ንግግር በሰሙ ጊዜ፣ ዋና አዛዦቻቸው፣ ከሞት የተረፉት ሁሉ፣ ወደፊት በመምጣት በሞሮኒ እግር ስር የጦር መሳሪያዎቻቸውን ጣሉት፣ እናም ደግሞ ህዝቦቻቸውን በሙሉ እንደዚሁ እንዲያደርጉ አዘዙአቸው።
፴፱ ነገር ግን እነሆ፣ የጦር መሳሪያዎቻቸውን ያልጣሉ ብዙዎች ነበሩ፤ እናም ጎራዴዎቻቸውን ያልሰጡ ተወሰዱና፣ ታሰሩ፣ እናም የጦር መሳሪያዎቻቸውንም ተቀሙና፣ ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ለጋስ ምድር ለመሄድ ተገደዱ።
፵ እናም አሁን የተወሰዱት እስረኞች ከተገደሉት፣ አዎን፣ ከሁለቱም በኩል ከተገደሉት በቁጥር ይበልጡ ነበር።