ምዕራፍ ፶፰
ሔለማን፣ ጊድ፣ እና ቴኦምነር የማንቲን ከተማ በዘዴ ወሰዱ—ላማናውያን ወጡ—የአሞን ህዝቦች ወንድ ልጆች ነፃነታቸውን፣ እና እምነታቸውን ለመከላከል ፀንተው በቆሙ ጊዜ ተጠበቁ። ከ፷፫–፷፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እነሆ፣ እንዲህ ሆነ የሚቀጥለው ዓላማችን የማንቲን ከተማ መያዝ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፣ በጥቂት ሰዎቻችን ከከተማቸው ለማስወጣት አይቻለንም ነበር። እነሆም፣ ቀደም ሲል ያደረግነውን ያስታውሱ ነበር፤ ስለዚህ ከጠንካራ ምሽጋቸው በዘዴ ለማስወጣት አልተቻለም ነበር።
፪ እናም በቁጥርም ከእኛ ወታደሮች የሚልቁ ስለነበር ወደ ጠንካራው ምሽጋቸው በመሄድ ለማጥቃት አልደፈርንም ነበር።
፫ አዎን፣ እናም እኛ መልሰን የወሰድናቸውን እነዚያን የምድሮች ክፍል ለመጠበቅ ሰዎቻችንን መጠቀም አስፈላጊ ነበር፤ ስለዚህ ከዛራሔምላ ምድር ወታደራዊ ኃይል፣ እናም ደግሞ አዳዲስ ስንቆችን እናገኝ ዘንድ መጠበቁ አስፈላጊ ነበር።
፬ እናም እንዲህ ሆነ ስለህዝባችን ጉዳይ እንዲያውቅ ለማድረግ ወደ ምድራችን ገዢ መልዕክተኛ ላክሁኝ። እናም እንዲህ ሆነ ከዛራሔምላ ምድር ስንቆችንና፣ ወታደራዊ ኃይልን ለማግኘት ጠበቅን።
፭ ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ጥቂቱ ብቻ ነበር የጠቀመን፤ ምክንያቱም ላማናውያንም ደግሞ ከቀን ወደ ቀን ታላቅ ብርታትን ይቀበላሉ ነበርና፤ እናም ደግሞ በርካታ ስንቆችን፤ እናም በዚህ ጊዜ የነበርንበት ሁኔታዎች እነኚህ ነበሩ።
፮ እናም ላማናውያን ከጊዜ ወደጊዜ እኛን ለማጥቃት ገሰገሱ፣ እናም እኛን ለማጥፋትም ስልት ቀየሱ፤ ይሁን እንጂ በማፈግፈጋቸውና በጠንካራው ምሽጋቸው ምክንያት ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት ለመምጣት አልቻልንም።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ምግብ አጥተን ልንጠፋ እስከምንቃረብ ድረስ በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ለብዙ ወራት ጠበቅን።
፰ ነገር ግን እንዲህ ሆነ እኛን ለመርዳት ሲባል በሁለት ሺህ ሠራዊት የተጠበቀ ምግብ ተቀበልን፤ እናም እራሳችንንና ሀገራችንን በጠላት እጅ እንዳይወድቁ አዎን ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ጠላቶች ጋር ለመዋጋት የተቀበልነው እርዳታ ሁሉ ይህ ነው።
፱ እናም እንግዲህ ይህ ለችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ፣ ወይም ተጨማሪ ኃይል ለምን እንዳልላኩልን ምክንያቱን አናውቅም፤ ስለዚህ አዝነን ነበር፣ እናም ደግሞ በማንኛውም መንገድ የእግዚአብሔር ፍርድ በምድራችን ላይ ይሆናል፣ ውጤቱም ለእኛ መሸነፍ፣ እናም ፍፁም ጥፋት ይሆናል በሚል ፍርሃት ተሞልተን ነበር።
፲ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲያበረታንና፣ ከጠላቶቻችን እጅ እንዲያድነን፣ አዎን፣ እናም ደግሞ ህዝባችንን ለመርዳት፣ ከተሞቻችንንና፣ ምድራችንን፣ እናም ሀብታችንን እናስመልስ ዘንድ ብርታትን ይሰጠን ዘንድ ከልባችን ፀለይን።
፲፩ አዎን፣ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ አምላካችን እኛን እንደሚያድነን ለማረጋገጥ ጎብኝቶናል፤ አዎን፣ ለነፍሳችን ሰላምን ተናግሮናል፣ ታላቅ እምነትንም ሰጥቶናል፣ እናም በእርሱም ለመዳናችን ተስፋ እንዲኖረን አድርጓል።
፲፪ እናም ጠላታችንን ለማሸነፍና፣ ምድራችንንና፣ ሀብታችንንና፣ ሚስቶቻችንንና፣ ልጆቻችንንና፣ የነፃነታችን መንስኤ የሆኑትን ለመጠበቅ ወሰንን፣ ባገኘነውም ጥቂት ኃይል ድፍረትን አገኘን።
፲፫ እናም ባለን ኃይል ሁሉ በማንቲ ከተማ ወደነበሩት ላማናውያን ሄድን፤ እናም በከተማዋ አቅራቢያ በሚገኘው ምድረበዳ ድንኳኖቻችንን ተከልን።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ በሚቀጥለው ቀን፣ በከተማዋ አጠገብ በምድረበዳው ዳርቻ መሆናችንን ላማናውያን በተመለከቱ ጊዜ፣ የወታደሮቻችንን ቁጥር እንዲሁም ጥንካሬ ለማወቅ ሰላዮቻቸውን ላኩብን።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እንደቁጥራችን ብዛት ጠንካራ አለመሆናችንን በተመለከቱ ጊዜ፣ እናም ከእኛም ጋር ለመዋጋትና፣ እኛን ለመግደል የማይመጡ ከሆነ፣ እርዳታው ይቋረጥብናል ብለው በመፍራትና ደግሞ በበርካታ ሰራዊታቸው በቀላሉ ልናጠፋቸው እንችላለን ብለው በመገመታቸው፤ ስለዚህ ከእኛ ጋር ለመዋጋት ዝግጅት ጀመሩ።
፲፮ እናም ከእኛ ጋር ለመዋጋት ዝግጅት ማድረጋቸውን በተመለከትን ጊዜ፣ እነሆ፣ ጊድ ከጥቂት ሰዎቹ ጋር እራሱን በምድረበዳው እንዲሸሽግ አደረግሁ፣ ደግሞም ቲኦመነርና ጥቂት ሰዎች እራሳቸውን በምድረበዳው እንዲሸሽጉ አደረግሁ።
፲፯ እንግዲህ ጊድና የእርሱ ሰዎች በስተቀኝ በኩል፣ እናም የተቀሩት በስተግራ በኩል ነበሩ፤ እናም እራሳቸውን በሸሸጉ ጊዜ፣ እነሆ፣ ላማናውያን ከእኛ ጋር ለመዋጋት በመጀመሪያ ጊዜ በወጡበት ድንኳናችንን በተከልንበት ስፍራ፣ ከተቀሩት ወታደሮቼ ጋር ቀረሁ።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ከበርካታ ሠራዊቶቻቸው ጋር በእኛ ላይ መጡ። እናም በመጡ ጊዜና በጎራዴ ሊያጠቁን በተቃረቡ ጊዜ፤ ከእኔ ጋር የነበሩትን ህዝቦቼን ወደ ምድረበዳው እንዲያፈገፍጉ አደረግሁ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን እኛን ይገድሉን ዘንድ በጣም እጅግ ፍላጎታቸው በታላቅ ፍጥነት ተከተሉን፤ ስለዚህ ወደ ምድረበዳው ተከተሉን፤ በጊድ፣ እናም በቲአምነር መካከል ስናልፍም በላማናውያን አልተገኙም ነበር።
፳ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ባለፉ ጊዜ፣ ወይንም ሠራዊቱ ባለፉ ጊዜ፣ ጊድና ቴኦምነር ከተሸሸጉበት ስፍራ ወጡ፤ እናም ወደከተማዋ እንዳይመለሱ የላማናውያን ሰላዮችን ቆርጠው አስቀሩአቸው።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ቆርጠው ካስቀሩአቸው በኋላ፣ ወደ ከተማዋ ሮጡና እስከሚያጠፉአቸው፣ እናም ከተማዋንም እስከሚወስዱ ድረስ፣ ከተማዋን እንዲጠብቁ የቀሩትን ጠባቂዎች አጠቁአቸው።
፳፪ እንግዲህ ይህ የሆነው ከጥቂት ጠባቂዎቻቸው በስተቀር ወደ ምድረበዳው እንዲሄዱ ላማናውያን ለሠራዊቶቻቸው በሙሉ ስለፈቀዱላቸው ነበር።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ጊድና ቴኦምነር በዚህ ዘዴ ጠንካራ ምሽጋቸውን ወሰዱ። እናም እንዲህ ሆነ ወደ ዛራሔምላ በምድረበዳው ብዙ ከተጓዝን በኋላ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ተጓዝን።
፳፬ እናም ላማናውያን ወደ ዛራሔምላ ምድር መዝመታቸውን በተመለከቱ ጊዜ፣ እጅግ ፈሩ፣ ይህም የሆነበት ወደ ጥፋት የሚመራቸው ዕቅድ የተዘጋጀ መስሏቸው ስለነበር ነው፤ ስለዚህ በድጋሚ ወደ ምድረበዳው ማፈግፈግ ጀመሩ፤ አዎን፣ በመጡበት መንገድም ተመለሱ።
፳፭ እናም እነሆ፣ ምሽት ነበርና፣ ድንኳናቸውን ተክለው ነበር፣ ምክንያቱም የላማናውያን ዋና አዛዦች ኔፋውያን በጉዞአቸው ደክመዋል በማለት ገምተው ነበር፤ እናም ወታደሮቻቸውን ሁሉ ከፊት እንዳስወጡ ስለገመቱ፣ በዚህም የተነሳ የማንቲን ከተማ በተመለከተ አላሰቡባትም ነበር።
፳፮ እንግዲህ እንዲህ ሆነ ምሽት በሆነ ጊዜ፣ የእኔ ሰዎች እንዳይተኙ፣ ነገር ግን በሌላ አቅጣጫ ወደ ማንቲ ምድር ወደፊት እንዲሄዱ አደረግሁ።
፳፯ እናም በዚህ በምሽቱ ጉዞአችን የተነሳ፤ እነሆ፣ በሚቀጥለው ቀን ላማናውያን በርቀት ቀድመናቸው ስለነበር አስቀድመን ወደ ማንቲ ከተማ ደረስን።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ በዚህ ዓይነት ስልት፣ ደም መፋሰስ ሳይኖር፣ የማንቲን ከተማ ያዝን።
፳፱ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ወታደሮች በከተማዋ አጠገብ በደረሱ ጊዜና፣ ከእነርሱ ጋር ለመገናኘት መዘጋጀታችንን በተመለከቱ ጊዜ፣ እጅግ ተገርመው ነበር፣ እናም ወደ ምድረበዳው እስከሚሸሹ ድረስ በታላቅ ፍርሃት ተውጠው ነበር።
፴ አዎን፣ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ሠራዊት ከምድሪቱ ክፍል ሁሉ ሸሽተው ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ ብዙ ሴቶችንና ልጆችን ይዘው ከምድሪቱ ወጡ።
፴፩ እናም በላማናውያን የተወሰዱት እነዚያ ከተሞች ሁሉ በዚህን ጊዜ በእኛ ቁጥጥር ሥር ናቸው፤ እናም በላማናውያን ምርኮኞች ሆነው ከተወሰዱት በቀር አባቶቻችንና፣ ሴቶቻችን፣ እናም ልጆቻችን ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
፴፪ ነገር ግን እነሆ፣ ወታደሮቻችን በቁጥር በርካታ የሆኑትን ከተሞች፣ እና በርካታ ንብረቶች ለመጠበቅ ጥቂት ናቸው።
፴፫ ነገር ግን እነሆ፣ የእኛ የነበሩትን ስፍራዎች፣ እናም ከተሞች እስከምናገኝ ድረስ በምድሪቱ ላይ ድልን በሰጠን አምላካችን እምነት አለን።
፴፬ እንግዲህ መንግስት የበለጠ ድጋፍን ለእኛ የማይሰጥበትን መንስኤ አናውቅም፤ ወደ እኛ የመጡትም ሰዎች ለምን ታላቅ ድጋፍ እንዳላገኘን አያውቁም።
፴፭ እነሆ፣ ድል እንዳላገኛችሁ ለመሆን እንደሚችል፣ እናም ወታደሮችን ወደዚያ ምድር ወስደህም እንደሆነ እንገምታለን፤ ይህ ከሆነ ለማጉረምረም አንፈልግም።
፴፮ እናም ይህ ካልሆነ፣ እነሆ፣ ስለዚህ በመንግስት መከፋፈል ምክንያት በተጨማሪ ሰዎችን ለእኛ እርዳታ እንደማይልኩ እንፈራለን፣ ከላኳቸው የበለጠ በቁጥር ብዙ መሆናቸውን እናውቃለንና።
፴፯ ነገር ግን እነሆ ይህ ምንም ማለት አይደለም—ምንም እንኳን ወታደሮቻችን ደካሞች ቢሆኑ፣ እግዚአብሔር እንደሚያድነን እናምናለን፤ አዎን፣ እናም ከጠላቶቻችን እጅ ያስለቅቀናል።
፴፰ እነሆ፣ ይህ በሀያ ዘጠነኛው ዓመት መጨረሻ ነበር፣ እኛም ምድሮቻችንን ይዘናል፤ እናም ላማናውያን ወደ ኔፊ ምድር ሸሽተዋል።
፴፱ እናም በከፍተኛ ሁኔታ የተናገርኳቸው የአሞን ህዝቦች ወንድ ልጆች፣ በማንቲ ከተማ ከእኔ ጋር ናቸው፤ ጌታም ረድቷቸዋል፣ አዎን፣ እናም አንድም ነፍስ እንኳን እስከማይጠፋ ድረስ በጎራዴ እንዳይጠፉ ተጠብቀዋል።
፵ ነገር ግን እነሆ፣ በብዛት ቆስለዋል፣ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ነፃ ባደረጋቸው በዚያ ነፃነት በፅኑነት ቆመዋል፤ እናም ከቀን ወደ ቀንም ጌታ አምላካቸውን በማስታወስ ጠንቃቆች ናቸው፤ አዎን፣ ህጎቹንና፣ ፍርዱን፣ እንዲሁም ትዕዛዛቱን፣ ለመጠበቅ ጥረት አድርገዋል፤ እናም የሚመጣውን በተመለከተ ስለተተነበየው እምነታቸውም ጠንካራ ነው።
፵፩ እናም አሁን፣ የተወደድህ ወንድሜ ሞሮኒ፣ እኛን የፈወሰንና፣ ነፃ ያደረገን ጌታ አምላካችን፣ ያለማቋረጥ በፊቱ ይጠብቅህ፤ አዎን፣ እናም ህዝቦቹን ይውደድ፣ ለእኛም እርዳታ የነበሩትን ላማናውያን የወሰዱብንን ንብረቶች ለማግኘት ድል እንድታገኝ እርሱ ይርዳህ። እናም እንግዲህ፣ እነሆ ደብዳቤዬን እደመድማለሁ። እኔ ሔለማን፣ የአልማ ልጅ ነኝ።