ምዕራፍ ፬
አልማ በሺህዎች የሚቆጠሩ የተለወጡትን አጠመቀ—ክፋት በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ገባ፣ እናም የቤተክርስቲያኗ እድገት ተገታ—ኔፊያሀ ዋና ዳኛ ሆኖ ተሾመ—አልማ ሊቀ ካህን በመሆኑ ራሱን ለአገልግሎት ሰጠ። ከ፹፮–፹፫ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እንግዲህ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ስድስተኛ ዓመት የንግስ ዘመን፣ በዛራሔምላ ምድር ምንም ዓይነት ፀብና ጦርነት አልነበረም።
፪ ነገር ግን ህዝቡ ተሰቃይቶ ነበር፣ አዎን፣ ወንድሞቻቸው ስለሞቱባቸው፣ እናም ደግሞ ከብቶቻቸውንና መንጋዎቻቸውን በማጣታቸው፣ እናም ደግሞ የመስኮቻቸው እህሎች በእግር በመረገጡና በላማናውያን ስለጠፉባቸው እጅግ ተሰቃዩ።
፫ እናም ስቃያቸው ታላቅ ሆኖ ሁሉም ነፍስ የሚያዝኑበት ምክንያት ነበራቸው፤ እናም ይህ የእግዚአብሔርን ፍርድ በኃጢአታቸውና በእርኩሰታቸው የተነሳ በላያቸው ላይ በእግዚአብሔር የተላከ ቁጣ እንደሆነ ያምኑ ነበር፤ ስለሆነም ሀላፊነታቸውን ለማስታወስ ነቅተው ነበር።
፬ እናም ቤተክርስቲያኗን ይበልጥ ሙሉ በማድረግ ማቋቋም ጀመሩ፤ አዎን፣ እናም ብዙዎች በሲዶም ወንዝ ተጠመቁ እናም የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል ሆኑ፤ አዎን፣ በቤተክርስቲያኗ ሰዎች ላይ ሊቀ ካህን በመሆን በአባቱ በአልማ በተሾመው በአልማ እጅ ተጠመቁ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ በሰባተኛው ዓመት የንግስ ዘመን ወደ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ነፍሳት በእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ራሳቸውን አባል ያደረጉና የተጠመቁ ነበሩ። እና እንደዚህም በኔፊ ህዝብ የነገሱበት ሰባተኛው የመሳፍንቱ የአገዛዝ ዘመን ተፈጸመ፤ እናም በጊዜውም ሁሉ ዘላቂ ሰላም ነበር።
፮ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ስምንተኛው ዓመት የንግስ ዘመን፣ የቤተክርስቲያኗ ሰዎች በአስደናቂው ሀብቶቻቸውና፣ በመልካሙ ሐሮቻቸውና፣ በተፈተለ ጥሩ በፍታና፣ በብዙ መንጋዎቻቸውና፣ ወርቃቸውና፣ ብራቸው፣ እናም በከበሩ ነገሮቻቸው ሁሉ መኩራት ጀመሩ፤ እናም በእነዚህ ነገሮች ሁሉ በኩራት ተወጠሩ፣ ውድ ልብሶችን መልበስ ጀምረዋልና።
፯ እንግዲህ ይህ ለአልማ፣ አዎን፣ እናም አልማ በቤተክርስቲያኗ ላይ መምህራንና ካህናት፣ እናም ሽማግሌዎች አድርጎ ለቀባቸው ሰዎች ታላቅ ስቃይ መንስኤ ነበር፤ አዎን፣ ብዙዎች በህዝባቸው መካከል ሲጀመር ስለተመለከቱት ኃጢኣትም በምሬት አዘኑ።
፰ የቤተክርስቲያኗ ሰዎች በኩራት ዐይን የተነሳሱና፣ ልባቸውን በሀብት፣ እና በዓለም ከንቱ ነገሮች ላይ ያሳረፉ፣ አንደኛው ሌላኛውን መውቀስ በመጀመራቸውና እንደ ፍቃዳቸውና ፍላጎታቸው ያላመኑትን ማሳደድ በመጀመራቸው በታላቅ ሀዘን አይተውታል እናም ተመልክተውታልና።
፱ እናም በመሣፍንቱ ስምንተኛ የንግስ ዘመን በቤተክርስቲያኗ ሰዎች መካከል ታላቅ ፀብ ተጀመረ፤ አዎን፣ ምቀኝነትና ፀብ፣ እናም ተንኮልና፣ ስደትና ኩራት፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ካልሆኑት የሚበልጥ ኩራት ነበር።
፲ እናም ስምንተኛው የመሣፍንት የንግስ ዘመን ተፈጸመ፤ እናም የቤተክርስቲያኗ ኃጢያት በቤተክርስቲያኗ አባል ላልሆኑት ታላቅ የመሰናከያ አለት ነበር፤ እናም ቤተክርስቲያኗ ከዕድገቷ መገታት ጀመረች።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ በዘጠነኛው ዓመት መጀመሪያ፣ አልማ የቤተክርስቲያኗን ኃጢያት ተመለከተ፣ እናም የቤተክርስቲያኗ አባላት ምሳሌም አማኝ ያልሆኑት ከአንዱ ክፋት ወደሌለኛው ሲመራቸው፣ በዚህም ህዝቡን ወደጥፋታቸው ሲያመጣቸው ተመለከተ።
፲፪ አዎን፣ በህዝቡ መካከል ታላቅ አድልዎን ተመለከተ፣ አንዳንዶች ሌሎችን በመጥላት፣ በተቸገሩና በተራቆቱ እንዲሁም በተራቡ፣ እናም በተጠሙትና፣ በታመሙትና በተሰቃዩት ላይ ጀርባቸውን በመስጠት ራሳቸውን በክፋት ከፍ አደረጉ።
፲፫ እንግዲህ ይህ በህዝቡ መካከል የለቅሶአቸው ታላቅ ምክንያት ነበር፣ ሌሎች እራሳቸውን ሲያዋርዱ፣ ከንብረቶቻቸው ለድሆችና ለተቸገሩት በማካፈል፣ የተራቡትን በመመገብ እርዳታ ማግኘት ለሚፈልጉ እርዳታን በማድረግ፣ እናም እንደትንቢቱ መንፈስ መምጣት ላለበት ክርስቶስ ሲሉም በሁሉም ዓይነት ስቃይ ተሰቃዩ፤
፲፬ ያንን ቀን በመጠባበቅ ኃጢኣታቸውን መሰረያ እንዲህ አገኙ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድና ኃይል መሰረት ከሞት እስር በመላቀቅ በሙታን ትንሣኤ በታላቅ ደስታ ተሞልተው ነበር።
፲፭ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ ትሁት የእግዚአብሔር ተከታዮችን ስቃይ በመመልከቱ፣ እናም በተቀሩት ሰዎች ስደት የተነሳና፣ ክፋታቸውን ሁሉ በመመልከቱ እጅግ ማዘን ጀመረ፤ ይሁን እንጂ የጌታ መንፈስ አልተወውም።
፲፮ እናም ከቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች መካከል አንድ ብልህ ሰው መረጠ፣ እናም ለእርሱ በተሰጠው ህግ መሰረትና በህዝቡም ላይ እንደክፋታቸውና እንደ ወንጀላቸው ያስፈፅም ዘንድ በህዝቡ ድምፅ መሠረት ሥልጣንን ሰጠው።
፲፯ እንግዲህ የዚህ ሰው ስም ኔፊያሀ ነበር፣ እናም እርሱ ዋና ዳኛ በመሆን ተመድቦ ነበር፤ እናም በፍርድ ወንበር ህዝቡን እንዲዳኝና እንዲገዛ ተቀመጠ።
፲፰ እንግዲህ አልማ በቤተክርስቲያኗ ላይ ሊቀ ካህን እንዲሆን ስልጣን አልሰጠውም፤ ነገር ግን የሊቀ ካህንነቱን ሀላፊነት ለራሱ ያዘው፤ ይሁን እንጂ የፍርዱን ወንበር ለኔፊያሀ ሰጥቶታል።
፲፱ እናም ይህን ያደረገው በህዝቡ መካከል እራሱ ይጓዝ ወይም በኔፊ ህዝብ መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ይሰብክ ዘንድ፣ ስራቸውን እንዲያስታውሱ እነርሱን ለማነሳሳት እናም በእግዚአብሔር ቃል ኩራታቸውንና ተንኮላቸው፣ እናም በህዝቡ መካከል ያለውን ፀብ ጎትቶ ለማስወረድ ነበር፣ በእነርሱ ላይ ንጹሁን ምስክር በግድ ከመገፋፋት በስተቀር እነርሱን መልሶ የሚያገኝበት ሌላ መንገድ እንደሌለ ተመልክቶ ነበር።
፳ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ በዘጠነኛው ዓመት የመሣፍንቱ አገዛዝ መጀመሪያ አልማ የፍርዱን ወንበር ለኔፊያሀ እንዲህ ሰጠው፣ እናም እራሱንም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ቅዱሱ ስርዓት ታላቅ ክህነት በራዕይና ትንቢት መንፈስ መሰረት በቃል ምስክርነት ላይ እራሱን ወሰነ።