ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፶፭


ምዕራፍ ፶፭

ሞሮኒ እስረኞች መለዋወጥን ተቃወመ—የላማናውያን ጠባቂዎች በስካር ተጠመዱ፣ እናም ኔፋውያን እስረኞች ተለቀቁ—የጊድ ከተማም ያለደም መፋሰስ ተወሰደች። ከ፷፫–፷፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ይህንን ደብዳቤ ሲቀበል ይበልጥ ተናደደ፣ ምክንያቱም አሞሮን ያጭበርባሪነቱን ፍፁም እውቀት እንዳለው ያውቅ ስለነበር፤ አዎን፣ በኔፊ ህዝብ ላይ ለጦርነት ለመሰለፍ የተነሳሳበት መንስኤው ትክክል እንዳልሆነ አሞሮን ማወቁን እርሱም ያውቃል።

እናም እንዲህ አለ፥ እነሆ፣ በደብዳቤዬ እንደገለፅኩት ዓላማውን ካልቀየረ ከአሞሮን ጋር እስረኞች አልለዋወጥም፤ ምክንያቱም ከነበረው የላቀ ኃይል እንዲኖረው አልፈቅድም።

እነሆ፣ ላማናውያን የወሰዷቸውን እስረኞች የሚጠብቁበትን ስፍራ አውቃለሁ፤ እናም አሞሮን በደብዳቤዬ የጠየቅሁትን ስላልሰጠኝ እነሆ በቃሌ መሰረት አደርጋለሁ፤ አዎን በሞሮኒ ሰዎች መካከል ለሰላም አቤት እስከሚሉ ድረስ ሞትን እፈልጋለሁ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ይህንን ቃል በተናገረበት ጊዜ፣ በሞሮኒ ሰዎች መካከል የላማን ትውልድ የሆነ ሰው ምናልባት ያገኝ ዘንድ በህዝቡ መካከል ፍተሻ እንዲሆን አደረገ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማን ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው አገኙ፤ እናም እርሱ በአማሊቅያ የተገደለው የንጉሱ አንድ አገልጋይ ነበር።

እናም ኔፋውያን እስረኞችን በሚጠብቁት ላይ ላማንና ቁጥር ያላቸው የእርሱ ሰዎች እንዲሄዱ ሞሮኒ አደረገ።

አሁን ኔፋውያን በጊድ ከተማ ይጠበቁ ነበር፤ ስለዚህ ሞሮኒ ላማንን በመሾም እናም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ከእርሱ ጋር እንዲሄዱ አደረገ።

እናም ምሽት በሆነ ጊዜ ላማን ኔፋውያንን ወደሚጠብቁት ሄደ፣ እናም እነሆ፣ ሲመጣ ተመለከቱትና ጠሩት፤ ነገር ግን እንዲህ አላቸው፥ አትፍሩ፣ እነሆ፣ እኔ ላማናዊ ነኝ። እነሆ፣ ከኔፋውያን አምልጠናል፣ እነርሱም ተኝተዋል፤ እናም እነሆ ወይናቸውንም ወሰድንና ከእኛ ጋር አምጥተናል።

እናም ላማናውያን ይህንን ቃል በሰሙ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት፤ እናም እንዲህ ሲሉ ተናገሩት፤ ወይኑን ይዘህ ስለመጣህ ተደስተናል፣ ደክሞናልና እንድንጠጣው ከወይኑ ስጠን።

ነገር ግን ላማን እንዲህ አላቸው፥ ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት እስከምንሄድ ወይናችንን እናትርፍ። ነገር ግን ይህ አባባል በይበልጥ ከወይኑ ለመጠጣት እንዲፈልጉ አደረጋቸው።

፲፩ እንዲህም አሉ፥ እኛ ደክሞናል፣ ስለዚህ ከወይኑ እንውሰድ፣ እናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኔፋውያን ላይ ለመሄድ ብርታት እንዲሰጠን የወይኑ ድርሻችንን እንቀበላለን።

፲፪ እናም ላማን፣ እንደፍላጎታችሁ ልታደርጉ ትችላላችሁ አላቸው።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ወይኑን በብዛት ጠጡ፤ ጣዕሙም አስደስቶአቸው ነበር፤ ስለዚህ ይበልጥ በብዛት ጠጡ፤ እናም የተዘጋጀውም ጠንካራ እንዲሆን ተብሎ ስለነበር ኃይለኛ ነበር።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ጠጡና፣ ተደሰቱ፣ እናም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሁሉም ሰክረው ነበር።

፲፭ እናም እንግዲህ ላማንና የእርሱ የሆኑት ሁሉም መስከራቸውን፣ እናም ኃይለኛ እንቅልፍ እንደያዛቸው በተመለከቱ ጊዜ፣ ወደ ሞሮኒ ተመለሱና የሆነውን ነገር በሙሉ ነገሩት።

፲፮ እናም አሁን ይህ በሞሮኒ ዕቅድ መሰረት ነበር። እናም ሞሮኒ ተከታዮቹን በጦር መሳሪያዎች ትጥቅ አዘጋጃቸው፤ ላማናውያን ኃይለኛ እንቅልፍ በያዛቸውና በሰከሩ ጊዜ ወደ ጊድ ከተማ ሄዱ፣ እናም ሁሉም እስከሚታጠቁ ድረስም የጦር መሳሪያዎቻቸውን ለእስረኞቹ ወርውረው ሰጡአቸው፤

፲፯ አዎን፣ ሴቶቻቸውን፣ እናም ልጆቻቸውን በሙሉ ብዙዎች የጦር መሳሪያዎችን መጠቀም የሚችሉትን ሁሉ ሞሮኒ አስታጠቃቸው፤ እናም እነዚህ ነገሮች በሙሉ ፍፁም በሆነ ፀጥታ ነበር የተከናወኑት።

፲፰ ነገ ግን ላማናውያንን ቀስቅሰዋቸው ቢሆን ኖሮ፣ እነሆ ሰክረው ስለነበር፣ እናም ኔፋውያን ሊገድሉአቸው ይችሉ ነበር።

፲፱ ነገር ግን እነሆ፣ ይህ የሞሮኒ ፍላጎት አልነበረም፤ በግድያም ሆነ በደም መፋሰስ አይደሰትም ነበር፣ ነገር ግን ህዝቡን ከጥፋት በማዳን ይደሰታል፤ በዚህም የተነሳ በራሱ ላይ የግፍ ስራን አያመጣም፣ ላማናውያንን አያጠቃም፣ እናም በስካራቸው አያጠፋቸውም።

ነገር ግን ፍላጎቱን ፈጸመ፤ በከተማዋ ግንብ ዙሪያ የነበሩትን ኔፋውያን እስረኞች አስታጥቆ ነበር እናም በግንቡ ውስጥ ያሉትን ሥፍራዎች እንዲወስዱ ኃይልን ሰጥቷቸው ነበር።

፳፩ እናም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች አንድ እርምጃ እንዲርቁ አደረገ፣ እናም የላማናውያንን ወታደሮች ከበቡአቸው።

፳፪ እናም እነሆ ይህ የተፈፀመውም በምሽት ነበር፣ ስለዚህ ላማናውያን ጠዋት ሲነቁ ከግንቡ በውጭ በኩል በኔፋውያን መከበባቸውን ተመለከቱ፣ እናም በውስጥ በኩል የነበሩት እስረኞቻቸውም ታጥቀው ከበዋቸው ነበር።

፳፫ እናም ላማናውያን በኔፋውያን ላይ ስልጣን እንደነበራቸውም ተመልክተው ነበር፤ እናም በዚህ ሁኔታ ከኔፋውያን ጋር መዋጋታቸው አስፈላጊ ሆኖ አላገኙትም ነበር፤ ስለዚህ ሊቀ ሻምባሎቻቸው የጦር መሳሪያዎቻቸውን ይፈልግ ነበር፣ እናም ወደፊት አመጡአቸውና፣ ምህረትን በመለመን በኔፋውያን እግር ስር ጣሉአቸው።

፳፬ እናም እነሆ፣ ይህ የሞሮኒ ፍላጎት ነበር። የጦር ምርኮኛ አድርጎ ወሰዳቸው፣ ከተማዋንም ያዘ፣ እናም ኔፋውያን የነበሩት እስረኞችን በሙሉ እንዲለቀቁ አደረገ፤ እናም እነርሱ ከሞሮኒ ወታደሮች ጋር ተቀላቀሉ፣ ለወታደሮቹም ታላቅ ድጋፍ ነበሩ።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ እስረኞች አድርጎ የወሰዳቸውን ላማናውያን በጊድ ከተማ ዙሪያ ያሉትን ምሽጎች ለማጠናከር ስራ እንዲጀምሩ አደረገ።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ እንደፍላጎቱ የጊድን ከተማ ምሽግ ባደረገ ጊዜ፣ እስረኞቹ ወደ ለጋስ ምድር እንዲወሰዱ አድርጎ ነበር፤ እናም ደግሞ ከተማዋን እጅግ ታላቅ በሆነ ኃይል ያስጠብቅ ነበር።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ይህንን ያህል ሴራ ቢያደርጉም ኔፋውያን የያዙአቸውን እስረኞች በሙሉ ጠበቁአቸው፣ እናም ደግሞ በድጋሚ ወስደውት የነበረውን ምድርና የበላይነታቸውን ተቆጣጠሩ።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን በድጋሚ ድል ማድረግ ጀመሩ፣ እናም ጥቅማቸውንና መብታቸውን ማስጠበቅ ጀመሩ።

፳፱ ብዙ ጊዜ ላማናውያን እነርሱን በምሽት ለመክበብ ይሞክሩ ነበር፣ ነገር ግን በዚህ ሙከራቸው ብዙ አስረኞቻቸውን አጥተዋል።

እናም በስካር ወይንም በመርዝ ያጠፏቸው ዘንድ ለኔፋውያን ወይኖቻቸውን ሊሰጧቸው ብዙ ጊዜ ሞክረዋል።

፴፩ ነገር ግን እነሆ፣ ኔፋውያን በስቃያቸው ጊዜ ጌታ አምላካቸውን ለማስታወስ የዘገዩ አልነበሩም። በእነርሱ ወጥመድም ሊያዙ አይችሉም ነበር፤ አዎን፣ ለጥቂት ላማናውያን እስረኞች በቅድሚያ ካልሰጡ በቀር ከወይኑአቸው አይጠጡላቸውም ነበር።

፴፪ እናም በመካከላቸው መርዝ እንዳይሰጣቸው ይጠነቀቁ ነበር፤ ወይኑ ለላማናውያን መርዝ ከሆነ ለኔፋውያንም መርዝ ይሆናልና፤ እናም መጠጦቻቸውን በሙሉ እንደዚህ ቀመሱ።

፴፫ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ የሞሪያንተንን ከተማ ለማጥቃት ሞሮኒ ዝግጅት ማድረጉ አስፈላጊ ነበር፤ እነሆም ላማናውያን የሞሪያንተንን ከተማ እጅግ ጠንካራ እስከምትሆን ድረስ በድካማቸው መሽገዋታል።

፴፬ እናም ላማናውያን አዲስ ኃይል ወደ ከተማዋ፣ እናም ደግሞ አዳዲስ አቅርቦቶችን፣ ያለማቋረጥ ያመጡ ነበር።

፴፭ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ሀያ ዘጠነኛ የንግስ ዘመን ተፈፀመ።