ቅዱሳት መጻህፍት
ሔለማን ፬


ምዕራፍ ፬

ከኔፋውያን የተገነጠሉትና ላማናውያን ኃይላቸውን አቀላቀሉ፣ እናም የዛራሔምላ ምድርን ያዙ—የኔፋውያን ሽንፈት የመጣው በኃጢኣታቸው ምክንያት ነው—ቤተክርስቲያኗ ተመናመነች፣ እናም ህዝቡ እንደላማናውያን ደካማ ሆነ። ከ፴፰–፴ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በሀምሳ አራተኛው ዓመት በቤተክርስቲያኗ ብዙ መለያየት ነበር፤ እናም ደግሞ ብዙ ደም እስከሚፈስ ድረስ በህዝቡ መካከልም ፀብ ነበር።

እናም አማፅያን የሆኑት ተገደሉና፣ ከምድሪቱ ተባረሩ፣ እናም ወደ ላማናውያን ንጉስ ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያንን ከኔፋውያን ጋር በውጊያ ለማወክ ጥረት አደረጉ፤ ነገር ግን እነሆ ላማናውያን የእነዚያን የተገነጠሉትን ቃል ለመስማት እስከማይፈልጉም እጅግ ፈርተው ነበር።

ነገር ግን እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሀምሳ ስድስተኛው ዓመት የንግስና ዘመን ከኔፋውያን ወደላማናውያን የሄዱ ተቃዋሚዎች ነበሩ፤ እናም በኔፋውያን ላይ ለቁጣ በማነሳሳት ድልን አገኙ፤ እናም ሁሉም በዚያን ዓመት በሙሉ ለጦርነት ተዘጋጅተው ነበር።

እናም በሀምሳ ሰባተኛው ዓመት ለውጊያ በኔፋውያን ላይ መጡና፣ የሞትን ስራ ጀመሩ፤ አዎን በመሣፍንቱ ሀምሳ ስምንተኛ ዓመት የንግስ ዘመን የዛራሔምላን ምድር አዎን እናም ደግሞ ከለጋስ ምድር አጠገብ ያሉትን ቦታዎች በሙሉ ለመያዝ ድል አገኙ።

እናም ኔፋውያንና የሞሮኒሀም ወታደሮች ወደ ለጋስ ምድር ተባረሩ፤

እናም ከባህሩ በስተምዕራብ በኩል እስከምስራቅ ከላማናውያን እራሳቸውን ሸሸጉ፤ ኔፋውያን ሰሜናዊውን ሀገራቸውን ለመከላከል ወታደሮቻቸውን የሸሸጉበት፣ እና ያሰፈሩበት መስመር የአንድ ቀን ጉዞ ያህል ነበር።

እናም እነዚያ ከኔፋውያን የተገነጠሉት ከብዙ ላማናውያን ወታደሮች እርዳታ ጋር በምድሪቱ በደቡብ በኩል ያሉትን የኔፋውያንን ይዞታዎች በሙሉ አገኙ። እናም ይህ ሁሉ የሆነው በመሣፍንቱ ሀምሳ ስምንተኛና ዘጠነኛ የንግስ ዘመን ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ስልሳኛ ዓመት የንግስ ዘመን ሞሮኒሀ ከሠራዊቱ ጋር የምድሪቱን ብዙ ቦታዎች ለማግኘት ተሳካለት፤ አዎን እነርሱም በላማናውያን እጅ የወደቁትን ብዙ ከተሞች በድጋሚ አገኙ።

እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ስልሳ አንደኛ የንግስና ዘመን የይዞታዎቻቸውን ግማሽ እንኳን በድጋሚ ለማግኘት ተሳካላቸው።

፲፩ እንግዲህ ይህ የኔፋውያን ታላቅ ጥፋት፣ እናም በመካከላቸው የነበረው ታላቅ ሞት፣ በመካከላቸው በነበረው በኃጢአተኝነታቸውና በእነርሱ ርኩስና ባይሆኑ ኖሮ አይኖርም ነበር፤ አዎን፣ እናም ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል ነን በሚሉትም መካከል የሚገኝም ነበር።

፲፪ እናም ይህም በልባቸው ኩራት፣ እጅግ ሀብታም በመሆናቸው የተነሳ፣ አዎን ድሆችን በመጨቆናቸው፣ ለረሃብተኞችም ምግባቸውን ስለከለከሉአቸው፣ ከታረዙት የሚለብሱትን በመከልከላቸው፣ ትሁት የሆኑ ወንድሞቻቸውንም በጥፊ ስለመቱአቸው፣ ቅዱስ በሆነውም ስለተሳለቁ፣ የትንቢትን እና የራዕይን መንፈስ በመካዳቸው፣ በመግደላቸው፣ በመዝረፋቸው፣ በመዋሸታቸው፣ በመስረቃቸው፣ ዝሙትን በመፈፀማቸው፣ ለፀብ በመነሳሳታቸው፣ እናም ወደኔፊ ምድር፣ ከላማናውያን መካከል፣ ጥለው በመሄዳቸው ምክንያት ነበር—

፲፫ እናም በዚህ በታላቁ ኃጢአታቸው የተነሳና፣ በጉልበታቸውም በመኩራታቸው፣ በእራሳቸው ጥንካሬ ተትተው ነበር፤ ስለዚህ አልበለፀጉም፣ ነገር ግን ተሰቃዩና፣ ተመቱ፣ እናም ምድሪቱን በሙሉ ለማጣት እስከሚቀርቡ ድረስ ከላማናውያን ፊት ተባርረዋል።

፲፬ ነገር ግን እነሆ፣ ሞሮኒሀ በክፋታቸው የተነሳ ለህዝቡ ብዙ ነገሮችን ሰበከላቸው፣ እናም ደግሞ የሔለማን ልጆች የነበሩት ኔፊና ሌሂ፣ ለህዝቡ ብዙ ነገሮችን ሰበኩ፣ አዎን እናም ስለክፋታቸውና፣ ለኃጢአታቸው ንስሃ ካልገቡ በእነርሱ ላይ ምን እንደሚመጣም ተነበዩላቸው።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ንስሃ ገቡ፤ እናም ንስሃ በመግባታቸውም መበልፀግ ጀመሩ።

፲፮ ሞሮኒሀ ንስሃ መግባታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ የንብረቶቻቸውን ግማሽ እናም የምድራቸውን ግማሽ እስከሚያገኙ ድረስ እነርሱን ከቦታ ቦታ፣ እንዲሁም ከከተማ ከተማ ለመምራት ሞከረ።

፲፯ እናም የመሣፍንቱ ሥልሳ አንደኛ የንግስና ዘመን እንደዚህ ተፈፀመ።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ስልሳ ሁለተኛ የንግስና ዘመን ሞሮኒሀ ከላማናውያን ይበልጥ ይዞታዎችን ማግኘት አልቻለም።

፲፱ ስለዚህ የተቀረውን ምድር የማግኘት ዕቅዳቸውን ተዉት፤ ምክንያቱም ላማናውያን እጅግ ብዙ ስለ ነበሩ ለኔፋውያን በእነርሱ ላይ ይበልጥ ኃይልን ለማግኘት አስቸጋሪ ሆነ፤ ስለዚህ ሞሮኒሀ የወሰዳቸውን ቦታዎች ለማቆየት ወታደሮቹን በሙሉ አሰማራ።

እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ቁጥር ብዙ በመሆኑ፣ ላማናውያን እንዳያሸንፏቸው፣ እናም እንዳይረግጧቸውና፣ እንዳይገድሏቸው፣ እንዲሁም እንዳያጠፏቸው ዘንድ ኔፋውያን በጣም ፈርተው ነበር።

፳፩ አዎን የአልማን ትንቢቶች፣ እናም ደግሞ የሞዛያን ቃላት ማስታወስ ጀመሩ፤ እናም አንገተ ደንዳና ህዝቦች መሆናቸውንና፣ የእግዚአብሔርንም ትዕዛዛት ከንቱ እንዳደረጉ ተመለከቱ፤

፳፪ እናም የሞዛያን፣ ወይም ጌታ ለህዝቡ እንዲሰጥ ያዘዘውን፣ ህግ እንደለወጡትና በእግራቸው እንደረገጡት፣ እናም ህግጋቶቻቸው እንደተበላሹና፣ እነርሱም እንደ ላማናውያን አይነት ኃጢአተኞች እስኪሆኑ ድረስ ኅጥያተኛ ህዝቦች እንደሆኑ ተመለከቱ።

፳፫ እናም በክፋታቸው የተነሳ ቤተክርስቲያኗ መመንመን ጀመረች፤ እናም በትንቢት መንፈስና፣ በራዕይ መንፈስ እምነት ማጣት ጀመሩ፤ የእግዚአብሔር ፍርድም በእነርሱ ላይ በአትኩሮት ተመለከታቸው።

፳፬ እናም እንደ ወንድሞቻቸው እንደ ላማናውያን ደካማ መሆናቸውን፣ እናም የጌታ መንፈስም ከዚህ በኋላ እንዳላዳናቸውም ተመለከቱ፤ አዎን፣ የጌታ መንፈስ ቅዱስ ባልሆነ ቤተመቅደስ ስለማይኖርም ከእነርሱ ሸሸ—

፳፭ ስለዚህ ጌታ በአስደናቂውና፣ ወደር በሌለው ኃይል እነርሱን መጠበቁን አቆመ፤ ምክንያቱም እምነት ወደማጣትና፣ በአሰቃቂ ኃጢያት ወድቀዋልና፤ እናም ላማናውያን ከእነርሱ ይልቅ እጅግ ብዙ መሆናቸውን፣ እናም ወደጌታ አምላካቸው በታማኝነት ካልጸኑ በማይቀር ሁኔታ መጥፋት እንዳለባቸው ተመለከቱ።

፳፮ እነሆም የላማናውያን ጥንካሬ እንደ እነርሱ ጥንካሬ፣ እንዲሁም አንድ ሰው ለአንድ ሰው አይነት፣ መሆኑን ተመለከቱ። እናም ስለዚህ ወደዚህ ታላቅ መተላለፍ እንደዚህ ወደቁ፤ አዎን፣ በጥቂት ዓመታት በመተላለፋቸውም ምክንያት እንደዚህ ደካሞች ሆኑ።