ምዕራፍ ፰
ምግባረ ብልሹ የሆኑት ዳብኛዎች ህዝቡ በኔፊ ላይ እንዲነሳሳ ፈለጉ—አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዜኖስ፣ ዜኖቅ፣ ኤፅያስ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ፣ ሌሂ እና ኔፊ ሁሉም ስለክርስቶስ መሰከሩ—ኔፊ በመንፈስ ተነሳስቶ የዋናውን ዳኛ መገደል አስታወቀ። ከ፳፫–፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ኔፊ እነኚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፤ እነሆ ዳኞች የነበሩ፣ ደግሞም የጋድያንቶን የሚስጥር ቡድን አባላት የሆኑ ሰዎች ነበሩና፣ ተቆጥተውት ነበር፤ እናም ለህዝቡም እንዲህ በማለት በእርሱ ላይ ጮኹ፥ ይህ ሰው ለፈፀመው ወንጀል ይፈረድበት ዘንድ ለምን ይዛችሁት አታመጡትም?
፪ ይህ ሰው ህዝቡን ሲሳደብ፣ እናም ህጋችንን ሲቃወም ለምን ዝም ብላችሁ ታዩታላችሁ፤ ለምንስ ትሰሙታላችሁ?
፫ እነሆም ኔፊ ስለህጋቸው ብልሹነት ለእነርሱ ተናግሮ ነበር፤ አዎን፣ ኔፊ ሊፃፉ የማይችሉ ብዙ ነገሮችን ተናግሯል፤ እናም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚቃረን ምንም አልተናገረም ነበር።
፬ እናም ስለጨለማው ስራቸው በግልፅ ይናገር ስለነበር ዳኞቹም ተቆጥተው ነበር፤ ይሁን እንጂ ህዝቡ ስለፈሩ እናም ይጮሁብናል ብለው ስለፈሩ እርሱን ለመንካት አልደፈሩም ነበር።
፭ ስለዚህ በህዝቡ ላይ እንዲህ በማለት ጮኹ፥ ይህ ሰው እኛን እንዲሰድበን ለምን ፈቀዳችሁለት? እነሆም በዚህ ህዝብ ሁሉ ላይ እስከጥፋት ድረስ ይኮንናቸዋል፤ አዎን፣ እናም ደግሞ እነኚህ ታላላቆቹ ከተሞቻችን ከእኛ እንደሚወሰዱ፣ ስለዚህ እኛም በእነርሱ ቦታ እንደማይኖረን ተናግሯል።
፮ እናም እንግዲህ ይህ የማይቻል እንደሆነ እናውቃለን፣ እነሆም ኃያል ነን፣ እናም ከተሞቻችን ታላላቅ ናቸው፤ ስለዚህ ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ስልጣን አይኖራቸውም።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡ በኔፊ ላይ በቁጣ እንዲነሳሳ አደረጉ፤ እናም በመካከላቸው ፀብ ቀሰቀሱ፤ ጥቂቶችም እንዲህ በማለት የሚጮኹ ነበሩ፥ ይህ ሰው መልካም ስለሆነ ተዉት፣ እናም እነዚህ እርሱ ያላቸው ነገሮች ንስሃ ካልገባን በእርግጥ ይሆናሉ፤
፰ አዎን እነሆ ለእኛ የመሰከረው ፍርድ በሙሉ በእኛ ላይ ይመጣል፤ ስለክፋታችን በትክክል መመስከሩን አውቀናልና። እናም እነሆ እነርሱም ብዙ ናቸው፤ እናም ክፋቶቻችንን እንደሚያውቃቸው ሁሉ የሚደርሱብንን ሁሉንም ነገሮች ያውቃል፤
፱ አዎን እናም እነሆ፤ ነቢይ ባይሆን ኖሮ ስለእነዚህ ነገሮች መመስከር ባልቻለም ነበር።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊን ለማጥፋት የፈለጉት ሰዎች፣ በፍርሃታቸው እጃቸውን በእርሱ ላይ እንዳያደርጉ ተገደው ነበር፤ ስለዚህ በጥቂቶች አይኖች ድገፋ በማግኘቱ የተቀሩት እንደሚፈሩ በተመለከተ ጊዜ በድጋሚ ለእነርሱ መናገርን ጀመረ።
፲፩ ስለዚህ እንዲህ በማለት ይበልጥ ለመናገር ተገፋፋ፥ እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ የቀይ ባህር ውሃን በመምታት፣ እናም ለሁለት በመክፈል አባቶቻችን የሆኑትን እስራኤላውያንን በደረቁ መሬት እንዳሻገራቸው፣ እናም ግብፃውያን ወታደሮች ውሃው ተዘግቶባቸው ይውጣቸው ዘንድ ስልጣንን እግዚአብሔር ለዚያ ለአንድ ሰው፣ እንዲሁም ለሙሴ እንደሰጠ አላነበባችሁምን?
፲፪ እናም አሁን እነሆ፣ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው እንደዚህ ዓይነት ስልጣን ከሰጠ፣ ንስሃ ካልገባችሁ በእናንተ ላይ ለፍርድ የሚመጣውን አውቅ ዘንድ ስልጣን አልሰጠውም በማለት እርስ በእርሳችሁ ለምን ትጣላላችሁ?
፲፫ ነገር ግን እነሆ፣ ቃሌን ብቻ አይደለም የካዳችሁት፣ ነገር ግን በአባቶቻችን የተነገሩትን ቃላት በሙሉ ክዳችኋል፤ ደግሞም ይህ ታላቅ ስልጣን በተሰጠው በሙሴ የተነገሩትን ቃላት፣ አዎን ስለመሲሁ መምጣት የተናገሯቸውም ቃላት ክዳችኋል።
፲፬ አዎን፣ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚመጣ አልመሰከረምን? እናም የናስ እባብን በምድረበዳው ውስጥ እንዳነሳ የሚመጣውም እንዲሁ ይነሳል።
፲፭ እናም ብዙዎች እባቡን ተመልክተው በህይወት እንደኖሩ፣ በእምነት፣ በተዋረደ መንፈስ በመሆን የእግዚአብሔርን ልጅ ቢመለከቱ እስከዘለዓለማዊው ህይወት እንኳን ህያው እስከሚሆኑ ድረስም ይኖራሉ።
፲፮ እናም አሁን እነሆ፣ ስለእነዚህ ነገሮች የመሰከረው ሙሴ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ከእርሱ ዘመን ጀምሮ እስከ አብርሃም ዘመን ቅዱሳን ነቢያትም ሁሉ ናቸው።
፲፯ አዎን፣ እናም እነሆ፣ አብርሃም ስለእርሱ መምጣት ተመልክቷልና፣ በስኬት ተሞልቶ ነበር፤ እናም ተደስቶ ነበር።
፲፰ አዎን፣ እናም እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ስለእነዚህ ነገሮች ያውቅ የነበረው አብርሃም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ከአብርሃም ዘመን በፊት በእግዚአብሔር ስርዓት የተጠሩ ብዙዎች ነበሩ፤ አዎን በልጁም ስርዓት መሠረት እንኳን፤ እናም ይህም ቤዛነትም እንኳን ለእነርሱ እንደሚመጣ፣ ከእርሱ መምጣት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ለህዝቡ ይታይ ዘንድ ነው።
፲፱ እናም እንግዲህ ከአብርሃም ዘመን ጀምሮ ስለእነዚህ ነገሮች ብዙ የመሰከሩ ነቢያት መኖራቸውን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ አዎን፣ እነሆ፣ ነቢዩ ዜኖስ በድፍረት መስክሯል፤ ለዚህም ተገድሏልና።
፳ እናም እነሆ፣ ደግሞ ዜኖቅም፣ ደግሞ ኤፅያስም፣ ደግሞ ኢሳይያስም፣ ኤርምያስም (ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት የተነበየው ይኸው ነቢዩ ኤርምያስ) እናም አሁን እንደ ኤርምያስ ቃል ኢየሩሳሌም እንደጠፋች እናውቃለን። አቤቱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደትንቢቱ መሰረት ለምን አይመጣም?
፳፩ እናም እንግዲህ ኢየሩሳሌም እንደጠፋች በዚህ ትከራከራላችሁን? የሴዴቅያስ ልጆች ከሙሌቅ በስተቀር ሁሉም አልተገደሉም ትላላችሁን? አዎን እናም የሴዴቅያስ ዘሮች ከእኛ ጋር መሆናቸውንና፣ ከኢየሩሳሌም ምድር መባረራቸውን አልተመለከታችሁምን? ነገር ግን እነሆ፣ ይህ ብቻም አይደለም—
፳፪ አባታችን ሌሂ ስለእነዚህ ነገሮች በመመስከሩ ከኢየሩሳሌም እንዲወጣ ተደርጓል። ኔፊም ደግሞ ስለእነዚህ ነገሮች መስክሯል፣ እናም ደግሞ ከሞላ ጎደል አባቶቻችን ሁሉ እስከዚህ ጊዜ ድረስ መስክረዋል፤ አዎን ስለክርስቶስ መምጣት መስክረዋል፤ የወደፊቱንም ጠብቀዋል፤ እናም ሊመጣ ባለውም በእርሱም ቀን ተደስተዋል።
፳፫ እናም እነሆ፣ ክርስቶስ አምላክ ነው፣ እርሱም ከእነርሱ ጋር ነው፣ እራሱንም ገልፆላቸዋል፣ በእርሱም ድነዋል፤ እናም በሚመጣውም የተነሳ ለእርሱ ክብርን ሰጥተውታል።
፳፬ እናም እንግዲህ፣ እነዚህን ነገሮች በማወቃችሁ፣ እናም ካልዋሻችሁ በቀር ልትክዱአቸው አትችሉም፤ ስለዚህ በዚህም ኃጢያትን ሰርታችኋል፤ ምክንያቱም ምንም እንኳን ብዙ ምስክሮችን የተቀበላችሁ ቢሆንም አዎን እውነት ለመሆናቸው ምስክር እንዲሆኑ በሰማይ እንዲሁም በምድር ያሉትን ነገሮች በሙሉ ከተቀበላችሁ በኋል፣ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ስላልተቀበላችሁ ነው።
፳፭ ነገር ግን እነሆ፣ እውነትን አልተቀበላችሁም እናም በቅዱሱ አምላካችሁም ላይ አምፃችኋል፤ እናም በዚህ ጊዜም እንኳን ቢሆን በሰማይ ንፁህ ያልሆነ ነገር ሊመጣበት በማይችለው ሥፍራ ለራሳችሁ የማይበላሸውን ሀብት በማስቀመጥ ፈንታ በፍርድ ቀን የሚሆን ቁጣን በራሳችሁ ላይ ታከማቻላችሁ።
፳፮ አዎን፣ በዚህ ጊዜም እንኳን በመግደላችሁ፤ እናም ዝሙት በመፈፀማችሁ እንዲሁም በክፋታችሁ ለዘለዓለማዊው ጥፋት በስላችኋል፤ አዎን፣ እናም ንስሃ ካልገባችሁ በቅርቡ በራሳችሁ ላይ ይመጣል።
፳፯ አዎን፣ እነሆ ይህም አሁን በደጃችሁ ላይ ነው፤ አዎን፣ ወደ ፍርድ ወንበሩ ሂዱና ፈልጉ፤ እናም እነሆ የእናንተ ዳኛ ተገድሎና፣ በደሙም ውስጥ ወድቋል፤ በፍርድ ወንበሩ ላይ ለመቀመጥ በፈለገው በወንድሙም ተገድሏል።
፳፰ እናም እነሆ ሁለቱም ደራሲ ጋድያንቶንና የሰዎችን ነፍስ ለማጥፋት የሚፈልገው የክፉው የሆነው የሚስጥራዊው ቡድን አባላት ናቸው።