ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፩


መፅሐፈ ሞርሞን

ምዕራፍ ፩

አማሮን ስለቅዱሳን መዛግብት ለሞርሞን መመሪያዎችን ሰጠው—በኔፋውያን እና በላማናውያን መካከል ጦርነት ተጀመረ—ሦስቱ ኔፋውያን ተወሰዱ—ክፋት፣ አለማመን፣ አስማትና ጥንቆላ ሰፈነ። ከ፫፻፳፩–፫፻፳፮ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ እኔ ሞርሞን፣ ስላየኋቸውና ስለሰማኋቸው ነገሮች ታሪክ ፃፍኩ፣ እናም መፅሐፈ ሞርሞን ብዬ ጠራሁት።

እናም አማሮን በጌታ መዛግብቱን ሊደብቅ ባለበት ጊዜ፣ ወደ እኔ መጣ፣ (እኔም አስር ዓመቴ ስለነበርና ሕዝቦቼ እንደተማሩት በመጠኑ መማር ጀመርኩ) እናም አማሮን እንዲህ አለኝ፥ እንደምገምተው አንተ አስተዋይ እንዲሁም ያስተማሩህን በፍጥነት የምትረዳ ልጅ ነህ፤

ስለዚህ፣ ሃያ አራት ዓመት ሲሆንህ ስለነዚህ ሰዎች የተመለከትካቸውን ነገሮች እንድታስታውስ እፈልጋለሁ፤ እናም በዚያም ዕድሜም ስትደርስ ሺም ተብላ በምትጠራ ኮረብታ ወደ አንቱም ምድር ሂድ፤ እናም በዚያ ይህንን ሕዝብ በተመለከተ ቅዱስ የሆኑ የተፃፉትን ሁሉ በጌታ እዚያ ደብቄአቸዋለሁ።

እናም እነሆ፣ የኔፊን ሠሌዳዎች ለራስህ ትወስዳለህና የተቀሩትን በነበሩበት ሥፍራ ትተዋቸዋለህ፤ ስለነዚህ ሰዎች የተመለከትካቸውን ነገሮች በሙሉ በኔፊ ሠሌዳ ላይ ትፅፋለህ።

እናም እኔ ሞርሞን፣ የኔፊ ዝርያ በመሆኔ (እናም የአባቴም ስም ሞርሞን ነበር) አማሮን ያዘዘኝን ነገሮች በሙሉ አስታወስኩ።

እናም እንዲህ ሆነ አስራ አንድ አመት ሲሆነኝ፣ በምድሪቱ በስተደቡብ በኩል እስከ ዛራሄምላ ምድርም በአባቴ ተወሰድኩኝ።

ምድሪቱ በሙሉ በህንፃ ተሸፍናለች፣ እናም ህዝቡም እንደባህር አሸዋ በቁጥር በዝተው ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በዚህ ዓመት ኔፋውያንና፣ ያዕቆባውያን፣ እናም ዮሴፋውያንና፣ ዞራማውያን ባሉበት በኔፋውያን መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ እናም ይህም ጦርነት በኔፋውያንና፣ በላማናውያንም፣ በልሙኤላውያን፣ እንዲሁም በእስማኤላውያን መካከል ነበር።

እንግዲህ ላማናውያንና፣ ልሙኤላውያን፣ እናም እስማኤላውያን፣ ላማናውያን ተብለው ይጠሩ ነበር፣ እናም ሁለቱ ቡድኖችም ኔፋውያን እናም ላማናውያን ነበሩ።

እናም እንዲህ ሆነ ጦርነቱም በሲዶም ውሃ በዛራሔምላ ዳርቻ በመካከላቸው ተጀመረ።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን ሠላሳ ሺህ እስከሚበልጡ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በአንድነት ሰበሰቡ። እናም እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመትም ብዙ ጦርነቶች ነበሩአቸው፣ በዚህም ኔፋውያንም ላማናውያንን አሸነፉአቸውና ብዙዎችን ገደሉአቸው።

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ዕቅዳቸውን ተዉና፣ በምድሪቱም ላይ ሠላም ነበር፤ እናም ለአራት ዓመታት ሠላም ሰፍኗል፣ ስለዚህ ምንም ደም መፋሰስ አልነበረም።

፲፫ ነገር ግን ኃጢያት በምድሪቱ ገፅ ላይ ሠፈነ፣ በዚህም የተነሳ ጌታ የተወደዱ ደቀመዛሙርቱን ወሰደ፣ እናም በህዝቡም ክፋት የተነሳ የተዓምር ሥራና ፈውስ ቆመ።

፲፬ እናም ከጌታም ምንም ዐይነት ስጦታዎች አልነበሩም፣ እናም በክፋቶቻቸው እናም ባለማመናቸው የተነሳ መንፈስ ቅዱስ በማንም ላይ አልመጣም ነበር።

፲፭ እናም አስራ አምስት ዓመት ሲሆነኝና ጥቂት አስተዋይ በመሆኔ በጌታ ተጎብኝቼ ነበር፣ እናም የኢየሱስን ቸርነት ቀምሼ አውቄም ነበር።

፲፮ እናም ይህን ሕዝብ ለመስበክ ጥረት አደርግ ነበር፣ ነገር ግን አንደበቴ ተዘጋና፣ እንዳልሰብክላቸውም ተከልክዬ ነበር፤ ምክንያቱም እነሆ ወደው በአምላካቸው ላይ አምፀው ነበርና፤ እናም በክፋታቸው የተነሳ የተወደዱ ደቀመዛሙርት ከምድሪቱ ተወስደዋል

፲፯ ነገር ግን እኔ በመካከላቸው ቀረሁ፣ ነገር ግን በልባቸው ጠጣርነት ምክንያት እንዳልሰብክላቸው ተከለከልኩ፤ እናም በልባቸው ጠጣርነት የተነሳ ምድሪቱ ተረግማ ነበር።

፲፰ እናም እነዚህ ከላማናውያን መካከል የነበሩት የጋድያንቶን ዘራፊዎች፣ ምድሪቱን ወረሩአት፤ በዚህም የተነሳ በዚያን ሥፍራ ይኖሩ የነበሩት ሀብቶቻቸውን በመሬት ውስጥ ቀበሩ፤ እናም ለመያዝ እንዳይችሉና በድጋሚ እንዳይዙ ወይም እንዳያገኙ ጌታ ምድሪቷን ስለረገማት እነዚህም የማይጨበጡ ሆኑ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ መናፍስትን ጠሪዎችና ጠንቋዮች፣ እንዲሁም አስማተኞች ነበሩ፤ እናም የአቢናዲና ደግሞ የላማናዊው ሳሙኤል ቃል ሁሉ እስከሚፈፀም የክፉው ሥልጣን በምድሪቱ ገፅ ሁሉ ላይ ይሰራ ነበር።