ምዕራፍ ፪
ሞርሞን የኔፊን ሠራዊት መራ—ምድሪቱን ደም እና እልቂት ጠረጋት—ኔፋውያን እንደተኮነነ አይነት ሀዘን አለቀሱ እናም አዘኑ—የፀጋ ጊዜአቸውም ያለፈ ነው—ሞርሞን የኔፊን ሠሌዳ ወሰደ—ጦርነትም ቀጠለ። ከ፫፻፳፯–፫፻፶ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ በዚያው ዓመት በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል በድጋሚ ጦርነት ሆነ። እናም ወጣት ብሆንም እንኳን በአቋሜ ትልቅ ነበርኩ፤ ስለዚህ የኔፊ ሕዝብ መሪያቸው እንዲሁም የሠራዊቶቻቸው መሪ እንድሆን ሾሙኝ።
፪ ስለዚህ እንዲህ ሆነ በአስራ ስድስተኛው ዓመቴ በላማናውያን ላይ የኔፋውያን የጦሩ መሪ በመሆን ሔድኩ፤ ስለዚህ ሦስት መቶ ሃያ ስድስት ዓመታት አለፉ።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ ሃያ ሰባተኛው ዓመት ላማናውያን እጅግ ታላቅ በሆነ ኃይል በእኛ ላይ መጡ፤ በዚህም የተነሳ ወታደሮቼን አስፈራሩአቸው፤ ስለዚህ እነርሱም አልተዋጉም፣ እናም በስተሰሜን ወዳሉት ሀገሮችም ማፈግፈግ ጀመሩ።
፬ እናም እንዲህ ሆነ ወደ አንጎላ ከተማ መጣንና፣ ከተማዋንም ወሰድን፣ እናም እራሳችንን ከላማናውያን ለመከላከል ዝግጅት አደረግን። እናም እንዲህ ሆነ፣ በጉልበታችን ያህችን ከተማ ምሽጋችን አደረግናት፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ምሽጋችን እንዲህ ቢሆንም ላማናውያን በእኛ ላይ መጡና ከከተማዋ አባረሩን።
፭ እናም ደግሞ ከዳዊት ምድርም አባረሩን።
፮ እናም እኛም ዘመትንና፣ በባሕሩ ዳርቻ በስተሰምዕራብ ጫፍ ወደሚገኘው ወደ ኢያሱ ምድር መጣን።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ህዝባችንን በአንድ ላይ እንዲሆን እናደርግ ዘንድ በተቻለ ፍጥነት በአንድነት ተሰበሰብን።
፰ ነገር ግን እነሆ፣ ምድሪቱ በዘራፊዎች እንዲሁም በላማናውያን ተሞልታ ነበር፤ እናም ታላቅ ጥፋት በህዝቤ ላይ የተመዘዘ ቢሆንም፣ ስለክፉ ስራዎቻቸው ንሰሃ አልገቡም፣ ስለዚህ በኔፋውያንና ደግሞ በላማናውያን በኩል በምድሪቱ ገፅ ሁሉ ደም መፋሰስና እልቂት ሆነ፤ እናም በምድሪቱ ላይ ህዝቡ በህግና በስርዓት ላይ ያምፅ ነበር።
፱ እናም እንግዲህ፣ ላማናውያን ንጉስ ነበራቸው፣ ስሙም አሮን ይባል ነበር፤ እናም ከአርባ አራት ሺህ ወታደሮቹ ጋር በእኛ ላይ መጣ። እናም እነሆ፣ በአርባ ሁለት ሺዎች ተቋቋምኩት። እንዲህም ሆነ ከፊቴ እስኪሸሽ በሠራዊቴ አሸነፍኩት። እናም እነሆ፣ ይህ ሁሉ ተፈፅሟል፣ ሦስት መቶ ሠላሳ ዓመታትም አለፉ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን ለክፋታቸው ንሰሃ መግባት ጀመሩና፣ በነቢዩ ሳሙኤል እንደተተነበየው መጮህ ጀመሩ፤ እነሆ በሌቦቹና በዘራፊዎች፣ እናም በገዳዮቹና፣ በአስማተኞች፣ እንዲሁም በምድሪቱ ባሉት ጠንቋዮች የተነሳ ማንም ሰው የራሱ የሆነውን ለመጠበቅ አልተቻለውምና።
፲፩ በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በምድር በሙሉ፣ በተለይ ከሌሎቹ በበለጠ በኔፊ ሕዝብ መካከል፣ ሀዘን እናም ልቅሶ ሆነ።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ሞርሞን፣ በጌታ ፊት ለቅሶአቸውንና ሀዘናቸውን በተመለከትኩ ጊዜ፣ የጌታን ምህረት እንዲሁም ታጋሽነት በማወቅም፣ ስለዚህ ጌታ እንደገና ፃድቃን ይሆኑ ዘንድ ለእነርሱ መሃሪ እንደሆነ በመገመቴ፣ ልቤ በውስጤ ሀሴት ማድረግ ጀመረች።
፲፫ ነገር ግን እነሆ ደስታዬ ከንቱ ነበር፣ ምክንያቱም ሀዘናቸው በእግዚአብሔር ቸርነት ለንሰሃ አልነበረምና፤ ነገር ግን የባለኩነኔ ሀዘን ነበር ምክንያቱም ጌታ ሁልጊዜም በኃጢያት ደስታን እንዲቀበሉ አልፈቀደላቸውም ነበር።
፲፬ እናም በተሰበረ ልብና በተዋረደ መንፈስ ወደ ኢየሱስም አልመጡም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ይረግሙታል እናም ሞትን ይመኛሉ። ይሁን እንጂ በህይወት ለመቆየት በጎራዴአቸው ይታገላሉ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ሀዘኔም በድጋሚ ወደ እኔ ተመለሰ፣ በጊዜያዊም እንዲሁም በመንፈሳዊ የጸጋ ቀናቸው ማለፉን ተመልክቻለሁ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት በገሃድ በአምላካቸው ላይ በማመፃቸው፣ ሲገደሉና እንደፍግ ሰውነታቸው በመሬት ላይ ሲቆለል ተመልክቻለሁና። እና በዚሁ ሦስት መቶ አርባ አራት ዓመት አለፈ።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ አርባ አምስተኛው ዓመትም ኔፋውያን ከላማናውያን ፊት መሸሽ ጀመሩ፤ እናም ሲያፈገፍጉም እነርሱን ማቆም ከመቻሉ በፊት በያሾን ምድር እስከሚመጡ ድረስ ተከተሉአቸው።
፲፯ እናም እንግዲህ፣ የጄሸን ከተማ አማሮንም መዛግብቱ እንዳይጠፋ ለጌታ ያስቀመጠበት ምድር አጠገብ ነበር። እናም እነሆ አማሮን እንዳዘዘኝ አደረግሁና፣ የኔፊን ሠሌዳ ወሰድኩኝ፣ እናም አማሮን እንዳዘዘኝ ታሪኩን ፃፍኩኝ።
፲፰ እናም በኔፊ ሠሌዳ ላይ ስለክፋቶችና ስለ ርኩሰቶች በሙሉ ታሪክን ፃፍኩ፤ ነገር ግን የሰዎችን ባሕሪይ ለማየት ከቻልኩበት ዕድሜዬ ጀምሮ በዐይኔ የማያቋርጥ ክፋትና ርኩሰትን በመመልከቴ በነዚህ ሠሌዳዎች ላይ ስለክፋታቸውና ርኩሰታቸው የነበረውን ታሪክ በሙሉ ከመፃፍ ተቆጥቤ ነበር።
፲፱ እናም በክፋቶቻቸው የተነሳ ለእኔም ወዮልኝ፤ ምክንያቱም በዘመኔ ሁሉ በክፋታቸው የተነሳ ልቤ በሀዘን ተሞልታለችና፤ ይሁን እንጂ፣ በመጨረሻው ቀን ከፍ እንደምል አውቀዋለሁ።
፳ እናም እንዲህ ሆነ በዚያ ዓመትም የኔፊን ሰዎች ታድነውና ተባርረው ነበር። እናም እንዲህ ሆነ የሺም ምድር ተብላ በምትጠራም በስተሰሜን እስከምንወጣ ድረስ ተባረርን።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ የሺምን ከተማ ምሽግ አደረግናትና፣ ሕዝባችንን ከጥፋት እናድን ዘንድ በሚቻለው መጠን በአንድ ላይ ሰበሰብን።
፳፪ እናም እንዲህ ሆነ በሦስት መቶ አርባ ስድስተኛው ዓመት በድጋሚ ወደ እኛ መምጣታቸውን ጀመሩ።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ሕዝቤ በላማናውያን ፊት በድፍረት እንዲቆሙና፣ ለሚስቶቻቸውና፣ ለልጆቻቸው፣ ለመኖሪያቸውና ለቤታቸው እንዲዋጉ በታላቅ ሀይል ተናገርኩአቸው፣ እናም አበረታኋቸው።
፳፬ እና ቃሌም በጥቂቱ አበረታታቸው፣ በዚህም የተነሳ ከላማናውያን ፊት አልሸሹም ነበር፣ ነገር ግን በፊታቸው በድፍረት ቆመው ነበር።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ ከሠላሳ ሺህ ወታደሮቻችን ጋር ነበር ከሃምሳ ሺህ ወታደሮች ጋር የገጠምነው። እናም እንዲህ ሆነ በፊታቸው በፅናትም ቆምን እነርሱም ከፊታችን ሸሹ።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ በሸሹ ጊዜ ከወታደሮቻችን ጋር ተከተልናቸው፣ እናም በድጋሚ አገኘናቸውና አሸነፍናቸው፤ ይሁን እንጂ የጌታ ብርታት ከእኛ ጋር አልነበረም፤ አዎን፣ የጌታ መንፈስ ከእኛ ጋር ስላልነበረ በብቻችን ነበርን፣ በዚህም፤ ስለዚህ ልክ እንደ ወንድሞቻችን ደካሞች ሆነን ነበር።
፳፯ እናም በህዝቦቼም ክፋትና ርኩሰት የተነሳ በደረሰው ታላቅ መቅሰፍት ልቤ አዝና ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ በላማናውያንና በጋድያንቶን ዘራፊዎች ላይ የትውልድ ምድራችንን በድጋሚ እስከምንወስድ ድረስ ሄድን።
፳፰ እናም ሦስት መቶ አርባ ዘጠነኛው ዓመት አለፈ። እናም በሦስት መቶ ሃምሳኛው ዓመት ከላማናውያንና ከጋድያንቶን ዘራፊዎች ጋር ስምምነት አደረግንና፣ የትውልድ ምድራችንንም ተከፋፈልን።
፳፱ እናም ላማናውያን በስተሰሜን በኩል ያለውን መሬት ሰጡን፤ አዎን፣ በቀጭኑ ማለፊያ ወደ ምድሪቱ ደቡብ የሚያመራውን ጭምር። እናም ለላማናውያን በምድሪቱ በስተደቡብ ያለውን ሁሉ ሰጠናቸው።