2021 (እ.አ.አ)
ሰላም በክርስቶስ፦ በዋጋ የማይታመነው እና ዘመን የማይሽረው “የገና ስጦታ”
ታህሳስ 2021 (እ.አ.አ)


የአካባቢ መሪ መልዕክት

ሰላም በክርስቶስ፦ በዋጋ የማይታመነው እና ዘመን የማይሽረው “የገና ስጦታ”

በዚህ የገና ወቅት እንዲሁም አመቱን ሙሉ ከሰላሙ ልዑል የሚመጣውን ያንን ዘላለማዊ ውስጣዊ ሰላም ለመለማመድ በልባችን እንፈልግ።

እኔ እና ወንድሞቼ በልጅነታችን በአዳኝ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት እና ተልዕኮ ላይ ባተኮረው በትክክለኛ የገና መንፈስ መደሰት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሳናውቅ እና ሳይሰማን አደግን። የገና በዓልን እንደ አንድ የተለየ ቀን ብቻ አድርገን እናከብር ነበር። በብዙ መንገዶች የገና ተሞክሮዬ ከልጅነት የምኞት ሃሳብ ጋር የተቀላቀለ ነበር። ለእኔ ገና ማለት አንድ ነገር ማለት ነበር: “የገና ስጦታ”። ለእኔ ስጦታ የለም ማለት ገና የለም ማለት ነው።

የልጅነት ልባችን “በገና ስጦታ” ላይ ብቻ የሚያተኩር ቢሆንም በዓመታዊ የትምህርት ቤት እረፍት እና በገና ቀን መካከል ያለው ይህ ወቅት ቀላል እንደማይሆን እናውቅ ነበር። “አደብ የሚገዛበት ጊዜ” የምለው አይነት አስቸጋሪ ወቅት ይሆናል። አፍቃሪ ወላጆቻችን ምንም ዓይነት ምክንያት አይቀበሉም ነበር፤ እናም እያንዳንዱ የሚሰራው ነገር መኖሩን ያረጋግጡ ነበር። በእያንዳንዱ ምሽት ከእራት በኋላ የቀጣዩ ቀን የሥራ ዕቅድ በአጭሩ ውይይት ይደረግበትና ዕድሜያችንን የሚመጥኑ የግል ወይም የቡድን ሥራዎች ይሰጡ ነበር። በዚህ “አደብ በሚገዛበት ጊዜ” ውስጥ ነበር ስለሥራ ጥቅም፣ ስለቤተሰብ አንድነት፣ አንዱ የሌላውን ሸክም ስለመሸከም፣ ስለቡድን ሥራ እና ስለሌሎች ጠቃሚ የሕይወት ክህሎቶች የተማርነው። ልክ ከገና በፊት ወላጆቻችን በእነዚህ ሁሉ ራስን የመምራት የቤት ውስጥ እና የግብርና ተግባራት ላይ ምን ያህል ጥሩ እንደሆንን ይገመግሙ ነበር፤ እንዲሁም “የገና ስጦታው” ይሰጠን አይሰጠን ይወስኑ ነበር። ሕይወቴን ዘላለማዊ በሆነ ባህርይ ለቀረፀው እንዲህ ላለው ራስን በዲሲፕሊን የማነጫ “አደብ የሚገዛበት ጊዜ” የልጅነት ተሞክሮ በትህትና ዝቅ እላለሁ እንዲሁም ከልብ አመሰግናለሁ።

ብዙ አመታት አልፈዋል። በሥራ በተጠመደ ሕይወት ተወጥረን ከልጅነት የአዋቂ ህልሞችን ወደማሳደድ አድገናል። “የገና ስጦታዬን” ሳገኝ የነበሩትን እነዚህን አንዳንድ አስደናቂ እና አስደሳች ጊዜያት በደንብ አስታውሳለሁ። በሌላ በኩል “አደብ በሚገዛበት ጊዜ” አፍቃሪ ወላጆቼ የሚጠብቁብኝን ለማሟላት ባለመቻሌ “የገና ስጦታ” ያላገኘሁባቸውን ጥቂት ደስ የማይሉ የገና ቀናት መርሳት ከባድ ነው። የአዳኝን ልደት እና የገናን ወቅት የወደድኩት እና ዋጋ የሰጠሁት በእነዚህ የልጅነት ልምዶች ምክንያት ነበር።

ገና ወቅት እንጂ አንድ የተለየ ቀን ብቻ አለመሆኑን ማወቅ አስደሳች ነው።

በመለኮታዊ ግንዛቤ አማካኝነት ሰላም በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ—ልክ ጳውሎስ እንዳስተማረው “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” (ኤፌሶን 4:7)።

የገና ወቅት ለሚያምኑት እና ሊያውቁት ለሚፈልጉት በርግጥ ልዩ ጊዜ ነው። በምንኖርባቸው በእነዚህ ታይተው በማይታወቁ ጊዜያት ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ለማሰላሰል እና ትኩረታችንን ወደ አዳኙ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማዞር ይህንን ጊዜ መጠቀም እንችላለን። አዳኙ ሞቅ ባለ ጥሪ ያቀርብልናል፣ “ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደእኔ ተመልከቱ፤ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ” (ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 6፥36)።

የዘላለማዊ ሰላም ማረጋገጫ ይሰጠናል። “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፥ እኔ የምሰጣችሁ አለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም” (ዮሃንስ 14፥27)።

የአዳኙ መወለድ በዋጋ የማይተመን እና ጊዜ የማይሽረው ከአፍቃሪው የሰማይ አባታችን ለልጆቹ የተሰጠ ስጦታ መሆኑን በማወቄ አመስጋኝ ነኝ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።

“ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሄር ወደ አለም አልላከውምና” (ዮሃንስ 3፥16–17)።

ስለውድ ልጁ ስጦታ ለሰማያዊ አባታችን እጅግ ዝቅ እላለሁ እንዲሁም አመሰግናለሁ። ከእርሱ ሰላምን ስንፈልግ በመንፈሱ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ወደ ታማኝ ልጆቹ የሚመጡት የመጽናናት ስሜቶች በእርግጥም እውነተኛ “የገና ስጦታ” ናቸው። ሁልጊዜ እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም ሊኖረን በሚያስችለን ሁኔታ ውስጥ ለመኖር በየቀኑ መጣር አለብን። እነዚህ ስሜቶች ከሰላሙ ልዑል ይመጣሉ። ነቢዩ ኢሳያስ እንደተናገረው፦ “ህጻን ተወልዷልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቷልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፥ ስሙም ድንቅ መካር፥ ሃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳይያስ 9፥6)።

ይህ ሰላም በእርሱ አማካኝነት አካላዊ እና መንፈሳዊ ሞትን ማሸነፍ የምንችልበት ቀላል ነገር ግን መለኮታዊ የሆነ እውነትን በመረዳት ይመጣል። በእርሱ ምክንያት እንደገና ለመኖር እንችላለን። ንስሐ በመግባት ይቅር እንድንባል አስችሎናል። ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይወደናል። ሰብዓዊ ችሎታችን ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ያውቀናል። በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ በምንሆንበትም ጊዜ እንኳን እኛን ይገነዘበናል። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት እንዳደረገው ሁሉ ዘላለማዊ ሰላሙን እንድንሻ ያለማቋረጥ ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርብልናል። በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፦ ነገር ግን አይዟችሁ፥ እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሃንስ 16፥33)።

በቅርቡ ጌታ እንዲህ ብሏል፣ “ከእኔ ተማር፣ እናም ቃላቴን አድምጥ፤ በመንፈሴ በትህትና ተጓዝ፣ እናም በእኔ ሰላምን ታገኛለህ” (ት እና ቃ 19፥23)።

በዚህ የገና ወቅት እንዲሁም አመቱን ሙሉ ከሰላሙ ልዑል የሚመጣውን ያንን ዘላለማዊ ውስጣዊ ሰላም ለመለማመድ በልባችን እንፈልግ። ከዚያም በኋላ ወንጌሉ በሚያመጣው ሰላምና ደስታ ዓለምን ማብራት እንችላለን። ጌታ እንዳለው፣ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴዎስ 5፥16)።

ስለአዳኙ መወለድ አመስጋኝ ነኝ፣ ህይወቱ፣ ምሳሌነቱ እና የኃጢያት ክፍያው ከሰማይ አባታችን ለሁሉም ልጆቹ ከተሰጡት የማያልቅ ፍቅር ውድ ስጦታ አካል እንደሆኑ አውቃለሁ። እሱ ሁል ጊዜ በልቤ በጥልቅ ክብር የምይዘው “ስጦታ” ነው።

ላውሪያን ፒ. ባሊሌምዋ በጥቅምት 2020 (እ.አ.አ) እንደ አካባቢ ሰባ ተጠራ። ከሃፒነስ ካጌሙሎ ጋር ትዳር መስርቷል፤ የሁለት ልጆች ወላጆች ናቸው። የሚኖረው በታንዛኒያ ዳሬሰላም ነው።

አትም