“በቤተክርስቲያን የእሁድ ስብሰባዎች ምን ይከናወናል?፣” ሊያሆናሰኔ 2022 (እ.አ.አ)
ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ሰኔ 2022 (እ.አ.አ)
በቤተክርስቲያን የእሁድ ስብሰባዎች ምን ይከናወናል?
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እግዚአብሄርን ለማምለክ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እርስበርስ ለመማማር በእያንዳንዱ እሁድ ይሰበሰባሉ። ሁሉም እንዲመጡ ይጋበዛሉ እንዲሁም አባላት የመጸለይ፣ ንግግር የመስጠት፣ እና ፍላጎት ካላቸውም የማስተማር እድል ያገኛሉ። እነዚህ ስብሰባዎች አባላት እርስበርስ በእምነት እና “ልባቸው በአንድ ላይ በአንድነት እና አንዱ ሌላኛውን ባለው ፍቅር” እንዲጠናከሩ ይረዳሉ” (ሞዛያ 18፥21)።
የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ
የአጥቢያው ወይም የቅርንጫፉ አባላት በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ለመሳተፍ በእያንዳንዱ እሁድ ይሰበሰባሉ። (የእኛ እምነት አባል ያልሆኑ ሰዎችም እንዲታደሙ ተጋብዘዋል።) ጌታን እንዲያስታውሱ ለመርዳት በዚህ ስብሰባ ውስጥ ቅዱስ ቁርባን ለአባላት ይሰጣቸዋል (ስለቅዱስ ቁርባን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚያዝያ 2022 (እ.አ.አ) የወንጌል መሰረታዊ ነገሮች ጽሁፍ ተመልከቱ)። በተጨማሪም ስብሰባው ጸሎቶችን፣ የአምልኮ መዝሙሮችን እና ስለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በአባላት የሚሰጡ ንግግሮችን ያካትታል።
ሌሎች ስብሰባዎች
ከቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በኋላ አባላት ወደተለያዩ ክፍሎች እና ቡድኖች ይሄዳሉ። ከ18 ወር እስከ 11 ዓመት የሆናቸው ልጆች በመጀመሪያ ክፍል ይሳተፋሉ። በየወሩ በመጀመሪያው እና በሶስተኛው እሁዶች ሁሉም ሌሎች አባላት በሰንበት ትምህርት ቤት ይሳተፋሉ። በሁለተኛው እና በአራተኛው እሁዶች በሴቶች መረዳጃ ማህበር፣ በወጣት ሴቶች ወይም በክህነት ቡድን ስብሰባዎች ይሳተፋሉ።
ጸሎቶች
በቤተክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ጸሎቶች በአባላት ይደረጋሉ። ጸሎቶች ቀላል እና በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ናቸው። አባላት ለሰማይ አባት ፍቅርን እና ክብርን የሚገልጹ ቃላትን በመጠቀም ይጸልያሉ። ይህም ወደእርሱ በሚጸልዩበት ጊዜ ክብራዊ እና አምልኮአዊ ቃላትን መጠቀምን ይጨምራል።
ንግግሮች
የኤጲስ ቆጶስ ወይም የቅርንጫፉ አመራር አባላት በቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ አባላትን ይጠይቃሉ። አነዚህ ንግግሮች በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ላይ ያተኩራሉ። ተናጋሪዎች ንግግራቸውን በሚያዘጋጁበት ወቅት ቅዱሳት መጻህፍትን እና የቤተክርስቲያን መሪዎችን ቃላት ይጠቀማሉ። የወንጌል መርሆዎች በህይወታቸው ውስጥ ስላመጧቸው በረከቶችም ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ትምህርቶች
ከቅዱስ ቁርባን ስብሰባ በኋላ አባላት አነስ ባሉ ክፍሎች ስለወንጌል ይማራሉ። ትምህርቶቹ ከቅዱሳት መጻህፍት፣ በአጠቃላይ ጉባኤ ከተሰጡ ትምህርቶች ወይም ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ። ምንም እንኳን አስተማሪው ትምህርቱን ቢመራውም፣ ይህ ንግግር አይደለም። የክፍሉ አባላት ሁሉ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ ሊያጋሩ ይችላሉ።
ምስክርነት
በወር አንድ ጊዜ የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ የምስክርነት ስብሰባን ይጨምራል። ብዙውን ጊዜ ይህ የሚሆነው በወሩ የመጀመሪያ እሁድ ላይ ነው። በዚህ ስብሰባ አባላት ስለኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለኃጢያት ክፍያው ምስክርነታቸውን ሊሰጡ ይችላሉ። ምስክርነት መስጠት ማለት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የወንጌልን እውነታዎች መናገር ማለት ነው።
ዝግጅት
አባላት በጸሎት፣ ቅዱሳት መጻህፍትን በማንበብ እና የመንፈስ ቅዱስን አነሳሽነት ለማግኘት ዝግጁ በመሆን ለእሁድ ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ። ንግግር እንድታደርጉ ወይም ትምህርት እንድታስተምሩ ከተጠየቃችሁ የወንጌልን መርሆች እንዴት ልታስተምሩ እንደምትችሉ በጸሎት መንፈስ አስቡ። ቅዱሳት መጻህፍትን ተጠቀሙ። የእውነት ምስክርነትን ስጡ። አስፈላጊ ከሆነ የቤተክርስቲያናችሁ መሪዎች እንድትዘጋጁ ሊረዷችሁ ይችላሉ።
© 2022 by Intellectual Reserve, Inc. All rights reserved. Printed in USA. እንግሊዘኛ የተፈቀደበት፦ 6/19። ትርጉም የተፈቀደበት፦ 6/19። የMonthly Liahona Message, June 2022 ትርጉም። Amharic። 18315 506