“መስከረም 2–8፦ ’ጌታን አስታውሱ።’ ሔለማን 7-12፣ ” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ መፅሐፈ ሞርሞን 2024 (እ.አ.አ) (2023[እ.አ.አ])
“መስከረም 2–8። ሔለማን 7-12፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2024 (እ.አ.አ) (2023 [እ.አ.አ])
መስከረም 2–8፦ “ጌታን አስታውሱ።”
ሔለማን 7–12
የኔፊ አባት ሔለማን ልጆቹን “አስታውሱ፣ አስታውሱ” ሲል አበረታቷቸዋል። አያቶቻቸውን እንዲያስታውሱ፣ የነቢያትን ቃላት እንዲያስታውሱ እንዲሁም ከሁሉም በላይ (ሔለማን 5:5–14 ይመልከቱ) አዳኛችን የሆነውን ክርስቶስን እንዲያስታውሱ ፈለገ ይመልከቱ)። ኔፊ በእርግጥ እንዳስታወሰ ግልጽ ነው ምክንያቱም ይህ ከአመታት በኋላ “በፅናት” ለህዝቡ የተናገረው ተመሳሳይ መልዕክት ነው (ሔለማን 10:4)። “አምላካችሁን እንዴት ልትረሱት ቻላችሁ?” (ሔለማን 7:20)። የኔፊ ጥረቶች ሁሉ—ወንጌልን ማስተማሩ፣ መፀለዩ፣ ተዓምራትን ማድረጉ እና ረሃብ እንዲያመጣ እግዚአብሔርን መማጸኑ—ህዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ እና እሱን እንዲያስታውሱ ለመርዳት የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ። እግዚአብሄርን መርሳት በብዙ መንገዶች እግዚአብሄርን ካለማወቅ የከፋ ችግር ነው። እንዲሁም አዕምሯችን “በዚህ ዓለም ከንቱ ነገሮች ”ትኩረቱ ሲሰረቅ እና በሃጢያት ሲሸፈን እርሱን መርሳት ቀላል ነው (ሔለማን 7:21፤ በተጨማሪም ሔለማን 12:2 ይመልከቱ)። ነገር ግን የኔፊ አገልግሎት እንደሚያሳየው ለማስታወስ እና “ወደ ጌታ አምላ[ክ] [ለመመለስ] በፍጹም አልረፈደም (ሔለማን 7:17)።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ ይገልጻሉ።
ሔለማን 7–11 በተለይ ነቢያት ስለሚሠሩት ሥራ ለመማር ጥሩ ቦታ ነው። እነዚህን ምዕራፎች ስታነቡ ለኔፊ ድርጊቶች፣ ሃሳቦች እና ከጌታ ጋር ለነበረው ግንኙነት ትኩረት ስጡ። የኔፊ አገልግሎት የነቢያትን ሚና እንድትገነዘቡ የሚረዳችሁ እንዴት ነው? ጥቂት ምሳሌዎች እነሆ ሌላ ምን ታገኛላችሁ?
-
ሔለማን 7:17–22፦ ነቢያት ንስሐ ስለመግባት ይናገራሉ እንዲሁም ንስሐ ባለመግባት ስለሚከሰት ውጤትም ያስጠነቅቃሉ።
ባነበባችሁት መሰረት፡ ስለነቢይ ምንነት እና ስለሚሰራው ሥራ እንዴት ትገልፁታላችሁ? አጭር ትርጓሜ መፃፍን አስቡ። ከዚያም “ነቢይ” የሚለውን ርዕስ በቅዱሳት መጻህፍት መምሪያ (ወንጌል ላይብረሪ) ወይም፤ “Follow the Living Prophet፣” (የቤተክርስትያኗ ፕሬዚዳንቶች ትምህርቶች፤ እዝራ ታፍት ቤንሰን (2014 (እ.አ.አ))፣ 147–55) ውስጥ ካነበባችሁ በኋላ በእናንተ ትርጓሜ ላይ ምን እንደምትጨምሩ ተመልከቱ።
በሔለማን 7፥11–29 ውስጥ ኔፊ ምን ያህል ደፋር እንደነበረ ትመለከታላችሁ? ኔፊ እንዳደረገው አንዳንድ ጊዜ ነቢያት በድፍረት መናገር እንደሚያስፈልጋቸው የሚሰማችሁ ለምንድነው? በሽማግሌ ኒል ኤል. አንደርሰን “The Prophet of God” መልዕክት (ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 26) “Don’t Be Surprised” የሚል ርዕስ ባለው ክፍል ውስጥ መልሶችን መፈለግን አስቡ።
እነዚህን ሁሉ እውነቶች በአዕምሯችሁ በመያዝ ጌታ በነቢያቱ አገልግሎት አማካኘነት እንዴት እንደባረካችሁ አሰላስሉ። በህይወት ባለው ነቢያችን አማካኝነት በቅርቡ ምን አስተምሯችኋል? ጌታን ለመስማት እና አቅጣጫውን ለመከተል ምን እያደረጋችሁ ነው?
በተጨማሪም የወንጌል ርዕሶች “ነቢያት፣” በወንጌል ላይብረሪ ውስጥ ይመልከቱ።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለኝ እምነት ከምልክቶች እና ከተዓምራት ባለፈ መገንባት አለበት።
ምልክቶች እና ተዓምራት የግለሰብን ልብ ለመለወጥ በቂ ቢሆኑ ኖሮ ኔፊ በሔለማን 9 ውስጥ በሰጣቸው ድንቅ ምልክቶች ሁሉም ኔፋውያን ይቀየሩ ነበር። ነገር ግን ያ አልሆነም። በሔለማን 9–10 ውስጥ ላለው ተዓምር ሰዎች የሰጡትን የተለያየ ምላሽ አስተውሉ። ለምሳሌ በሔለማን 9:1–20 (በተጨማሪም ሔለማን 9:39–41፤10:12–15) የአምስቱን ሰዎች እና የዋና ዳኛውን ምላሾች ልታነፃፅሩ ትችላላችሁ። ክእነዚህ ተሞክሮዎች እምነታችሁን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስለመገንባት ምን ትማራላችሁ?
ጌታ ፈቃዱን ለሚሹ እና ተዕዛዛቱን ለመጠበቅ ለሚጥሩ ሰዎች ኃይል ይሰጣል።
ሔለማን 10:1–12 ስታጠኑ ኔፊ በጌታ ለመታመን ያደረገውን አስተውሉ። የጌታን ፈቃድ እንጂ የራሱን እንደማይፈልግ ያሳየው እንዴት ነው? የኔፊ ተሞክሮ ምን እንድታደርጉ ያነሳሳችኋል?
የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል መገለጥን ይጋብዛል።
የመገፋት፣ የመጨነቅ ወይም ግራ የመጋባት ሥሜት ሲሰማችሁ በሔለማን 10:2–4 ውስጥ ካለው የኔፊ ምሳሌ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ልትማሩ ትችላላችሁ። “ሃዘን” ተሰምቶት በነበረ ጊዜ ምን አደረገ? (ቁጥር 3)።
ፕሬዚዳንት ሄንሪ ቢ. አይሪንግ፣ “ስናሰላስል በመንፈሱ መገለጥን እንጋብዛለን” (“Serve with the Spirit,” ሊያሆና፣ ሕዳር 2010(እ.አ.አ)፣ 60) የማሰላሰልን ልማድ እንዴት ታካብታላችሁ?
ጌታ እንዳስታውሰው ይፈልጋል።
የቤተሰብ አባልን የልደት ቀን ወይም የፈተና መረጃን የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎችን የምታስታውሱት እንዴት ነው? “ጌታን ለማስታወስ” ሊደረግ ከሚገባው ጥረት ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ሔለማን 12፥5)። የሚለየውስ እንዴት ነው?
ሔለማን 12 ሰዎች ጌታን እንዲረሱ ምክንያት የሚሆኗቸውን ብዙ ነገሮች ይገልጻል። ምናልባት ልትዘረዝሯቸው እና ሃሳባችሁ በእርሱ ላይ እንዳሆን ሊያደርጉ ይችሉ እንደሆነ ማሰብ ትችላላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስን እንድታስታውሱት ምን ሊረዳችሁ ይችላል? በተማራችሁት መሠረት ምን ለማድረግ ትነሳሳችሁ?
በተጨማሪም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 20፥77፣79፤ “Reverently and Meekly Now፣” መዝሙር፣ ቁጥር 185 ይመልከቱ።
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
ጌታ እንዳስታውሰው ይፈልጋል።
-
ጌታን ስለማስታወስ ውይይት ለማስጀመር አንድ ነገር ረስታችሁ ስለነበረበት ጊዜ ለልጆቻችሁ ለመንገር ትችላላችሁ። ተመሳሳይ ተሞክሮዎቻቸውን እንዲያጋሩ ፍቀዱላቸው። ከዚያም ሔለማን 7፥20–21 አንድ ላይ ልታቡ ትችላላችሁ እንዲሁም እግዚአብሄርን መርሳት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንደሚያስቡ ልጆቻችሁን ጠይቁ። ምናልባት ልጆቻችሁ ጌታን እንድንረሳ ምክንያት ሊሆኑን የሚችሉ ነገሮችን ምሥል ሊስሉ እና ሥዕሎቻቸውን የኢየሱስን ምሥል ለመሸፈን ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ከዚያም እርሱን ለማስታወስ ሊያደርጉ ስለሚችሏቸው ነገሮች ማሰብ ይችላሉ። ሃሳባቸውን እያጋሩ እያሉ የአዳኙ ምስል እስኪታይ ድረስ ሥዕሎቹን አንድ በአንድ ሊያነሱ ይችላሉ።
ነቢያት ስለኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክራሉ።
-
ስለአኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማሩ ነቢያትን ሥሞች በሔለማን 8:13–23 ውስጥ እንዲፈልጉ ልጆቻችሁን እርዷቸው። ምናልባት አንድ ሥም ባገኙ ቁጥር የኢየሱስን ምሥል ወደሚቀጥለው ልጅ ሊያቀብሉ ይችላሉ። በህይወት ያለ ነቢያችን ስለአዳኙ ምን አስተምሯል?
-
እንዲሁም ስለነቢያት መዝሙር መዘመርም ትችላላችሁ፣ ለምሳሌ “Follow the Prophet” (የልጆች የመዝሙር መጽሐፍ፣ 110-11)። ምናልባት እናንተ እና ልጆቻችሁ ከመዝሙሩ ውስጥ አንድ ቁልፍ ሀረግ ልትመርጡ እና በተለያየ የወረቀት የእግር አሻራ ላይ ከሃረጉ ውስጥ አንድ ቃል መፃፍ ትችላላችሁ። ከዚያም የእግር አሻራውን ወደ አዳኙ ሥዕል በሚያመራው ወለል ላይ ማስቀመጥ ትችላላችሁ፣ ከዚያም ልጆቻችሁ ወደ ሥዕሉ የሚሄዱትን የእግር አሻራዎች ሊከተሉ ይችላሉ። ነቢዩን መከተል ወደኢየሱስ ክርስቶስ የመራን እንዴት ነው?
የእግዚአብሔርን ቃል ማሰላሰል መገለጥን ይጋብዛል።
-
ልጆቻችሁ ማሰላሰል ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለመርዳት “ማሰላሰል” የሚለውን ቃል በቅዱሳት መጻህፍት መመሪያ (ወንጌል ላይብረሪ) ውስጥ አብራችሁ ልታነቡ ትችላላችሁ። ከማሰላሰል ጋር የሚመሳሰሉ ሌሎች ቃላት ምን ምን ናቸው? ምናልባት ሔለማን 10፥1–3ን አብራችሁ ልታነቡ እና ማሰላሰል የሚለውን ቃል በእነዚያ ሌሎች ቃላት መተካት ትችላላችሁ። ማሰላሰልን የቅዱሳት መፃህፍት ጥናት ክፍል ማድረግ ስለሚችሉባቸው መንገዶች ከልጆቻችሁ ጋር ተነጋገሩ።
ሰማያዊ አባትን አከብራለሁ።
-
አስቸጋሪ ነገርን ማድረግ በሚጠይቅበት ጊዜ እንኳን ኔፊ ሰማያዊ አባትን አክብሯል። እናንተና ልጆቻችሁ ለዚህ ምሳሌ ይሆናችሁ ዘንድ ሔለማን 10:2፣ 11–12ን ልታነቡ ትችላላችሁ። ምናልባት ልጆቻችሁ—በክፍሉ ወደ አንድ ጎን በመራመድ (ልክ ወደ ቤታቸው የሚሄዱ ይመስል)፣ በመቆም፣ በመዞር እና በክፍሉ ወደ ሌላኛው ጎን በመሄድ (ልክ ህዝቡን ለማስተማር እየተመለሱ ያሉ ይመስል) ኔፊ ያደረጋቸውን ነገሮች መተወን ይችሉ ይሆናል። የሰማይ አባት እንድናደርግ የሚፈልጋቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምን ናቸው?