“የዳግም መመለስ ድምጾች፦ ‘የራዕዩ’ ምስክርነቶች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“‘የራዕዩ’ ምስክርነቶች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
የዳግም መመለስ ድምጾች፦ “የራዕዩ” ምስክርነቶች
ውልፈርድ ውድረፍ
ጆሴፍ ስሚዝ እና ስድኒ ሪግደን በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76 ውስጥ የሚገኘውን ራዕይ ከተቀበሉ ከሁለት አመታት በኋላ፣ ውልፈርድ ውድረፍ በታህሳስ 1833 (እ.አ.አ) ቤተክርስቲያኗን ተቀላቀሉ። በወቅቱ ኒው ዮርክ ውስጥ ይኖሩ ነበር እናም በአካባቢው እያገለገሉ ከነበሩ ሚስዮናውያን ስለ “ራዕዩ” አወቁ። ከዓመታት በኋላ፣ በዚህ ራዕይ ላይ ስለነበራቸው ግንዛቤ ተናግረዋል።
“ከልጅነቴ ጀምሬ የተማርኩት አንድ መንግስተ ሰማይ እና አንድ ሲኦል እንዳለ ነበር፤ እንዲሁም ክፉዎች አንድ አይነት ቅጣት እንዲሁም ጻድቃን አንድ ክብር … እንዳላቸው ተነግሮኝ ነበር።
“… ራዕዩን ሳነብ …፣ አዕምሮዬን አበራልኝ እንዲሁም ታላቅ ደስታ ሰጠኝ፣ ይህን መርህ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ጥበበኛ፣ ፍትሃዊ እና እውነተኛ፣ የምርጥ ባህርያት እና የእውቀት ባለቤት እንደሆነ ተገለጠልኝ፤ እርሱ ከፍቅር፣ ከምህረት፣ ከፍትህ እና ከፍርድ ጋር የማይለዋወጥ እንደሆነ ተሰማኝ እናም በህይወቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጌታን እንደወደድኩት ተሰማኝ።”
“ይህ ‘ራዕይ’ በማንኛውም መጽሐፍ ውስጥ ካነበብነው ከማንኛውም ራዕይ የበለጠ ብርሃን፣ የበለጠ እውነት እና የበለጠ መርህ የሚሰጥ ራዕይ [ነው]። አሁን ስላለንበትን ሁኔታ፣ ከየት እንደመጣን፣ ለምን እዚህ እንደመጣንና የት እንደምንሄድ ያለንን ግንዛቤ ግልፅ ያደርገዋል። በዚያ ራዕይ አማካኝነት ማንኛውም ሰው የእርሱ ክፍል እና ሁኔታ ምን እንደሚሆን ሊያውቅ ይችላል።”
“ጆሴፍን ከማየቴ በፊት ስለዕድሜው ወይም ምን ያህል ትልቅ ወይ ትንሽ እንደሆነ፣ ምን ይመስል እንደነበረ፣ ጸጉሩ ረዥም ይሁን አጭር፣ ግድ አልነበረኝም፤ ያንን ራዕይ [በክፍል 76ውስጥ የተመዘገበን ራ ዕይ] የተቀበለ ሰው የእግዚአብሔር ነቢይ ነው አልኩኝ። እኔ ራሴ ይህን አውቄዋለሁ።”
ፊቢ ክሮዝቢ ፔክ
ፊቢ ፔክ፣ ጆሴፍ እና ስድኒ “ስለራዕዩ“ እንደሚያስተምሩ በሰማችበት ጊዜ፣ በሚዙሪ ትኖር የነበረች ሲሆን ነጠላ ወላጅ በመሆን አምስት ልጆችን እያሳደገች ነበር። ራዕዩ በጣም ስላስደነቃት እና ስላነሳሳት፣ የተማረችውን ለዘመዶቿ ለማካፈል የሚከተለውን ጻፈች፦
“ጌታ የሰማያዊ መንግስቱን ሚስጥሮች ለልጆቹ እየገለጸ ነው። … ጆሴፍ ስሚዝ እና ስድኒ ሪግደን ባለፈው ጸደይ ወቅት ጎበኙን፣ እዚህ ሳሉም ብዙ አስደሳች ስብሰባዎች አደረግን፣ እንዲሁም ለእኔ ትልቅ ማበረታቻ የሰጡኝ ብዙ ሚስጥሮች ለእኛ እይታ ተገልጠውልን ነበር። ለልጆቹ የሰላም ማረፊያ ስፍራን በማዘጋጀቱ የእግዚአብሔርን ትህትና ማየት ችለናል። የወንጌሉን ሙላት የማይቀበል እና ለክርስቶስ መልካም ስራ እንደ ጀግኖች ወታደሮች የማይቆም ሁሉ በአብ እና በወልድ ፊት መኖር አይችልም። ሆኖም ለማይቀበሉት ሁሉ የተዘጋጀ ቦታ አለ፣ ነገር ግን በሰለስቲያል መንግሥት ውስጥ ከመኖር በጣም ያነሰ ክብር ያለው ቦታ ነው። አሁን በህትመት ላይ ስለሆኑ እና ወደ ዓለምም ስለሚሄዱ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ሌላ ምንም ለመናገር አልሞክርም። እናም ምናልባት ራሳችሁ ለማንበብ ዕድል ይኖራችኋል፣ እናም እድሉን ካገኛችሁ በጥንቃቄ እና በጸሎት ልብ እንደምታነቡት ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ናቸውና። እንዲሁም፣ እነሱን እንድትመረምሩ እፈልጋለሁ፣ ምክንያቱም በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው አለም ለደስታችን አስተዋጽዖ የሚያደርገው እርሱ ነውና።”