ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ)
ጥር 4–10። ጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ 1፥1–26፥ “የብርሃን አምድ … ተመለከትኩ”


“ጥር 4–10። ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1፟–26፥ “የብርሃን አምድ … ተመለከትኩ” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰብና ለቤተሰብ፥ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021(እ.አ.አ) [2020 (እ.አ.አ)]

“ጥር 4–10። ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1፟–26” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ 2021 (እ.አ.አ)

ምስል
ቅዱስ ጥሻ

ቅዱስ ጥሻ፣ በግሬግ ኬ. ኦልሰን

ጥር 4–10

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1–26

“የብርሃን አምድ … ተመለከትኩ”

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1–26ን ስታነቡ ለህይወታችሁ ምን አይነት መልእክትን ታገኛላችሁ? ለእናንተና ለቤተሰባችሁ በጣም ታላቁ ዋጋ ምንድን ነው?

ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ለጸሎቶች መልስ የያዘ መጽሃፍ ነው፥ በመጽሃፉ ያሉ ብዙዎቹ የተቀደሱ ራእዮች የተገኙት ለጥያቄዎች ምላሽ ሆነው ነው። ስለዚህም ትምህርት እና ቃልኪዳኖችን ለማጥናት ስንነሳ በተከታታይ ለተሰጡት ራዕዮች መነሻ የሆነውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ቢሆን አግባብነት ይኖረዋል፣ ይህም ጥያቄ በ1820 (እ.አ.አ) ጆሴፍ ስሚዝ በቅዱስ ጥሻ ውስጥ የጠየቀው ነው። “[የቃላት] ጦርነት እና [የአስተያየት] ሁካታ”(ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥10) ጆሴፍ ስሚዝን ስለ ሃይማኖትና ስለ ነፍሱም እጣ ፈንታ ግራ መጋባት ዉስጥ ጥሎት ነበር፣ ምናልባትም እናንተም ይህንን ስሜት ልትጋሩ ትችላላችሁ። በዘመናችን በጣም ብዙ የሚጣረሱ ሃሳቦችና አሻሚ ድምጾች አሉ፣ በእነዚህ መልእክቶች መሃከል አጣርተን እውነትን ለማወቅ ስንፈልግ፣ ጆሴፍ እንዳደረገው ማድረግ እንችላለን። ጥያቄዎችን መጠየቅ፣ ቅዱሳት መጻህፍቶችን ማጥናት፣ ማሰላሰል፣ እና በመጨረሻም እግዚአብሔርን መጠየቅ እንችላለን። ለጆሴፍ ስሚዝ ጸሎት መልስ በመስጠትም፣ የብርሃን አምድ ከሰማይ ወረደ፤ እግዚአብሔር አብ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጹ እናም ጥያቄዎቹን መለሱ። ያም የጆሴፍ ስሚዝ ተአምራዊው ተሞክሮ ማንም “ጥበብ [ቢጎድለው] እግዚአብሔርን መጠየቅ ይችላል እናም አይነቀፍም” (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥26) ብሎ በአጽኖት ያውጃል። ሰማያዊ ራዕይ ባይሆን እንኳን፣ በሰማይ ብርሃን ያንጸባረቀ ግልጽ ራዕይ ሁላችንም መቀበል እንችላለን።

ምስል
የግል ጥናት ምልክቶች

ለግል ቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ጠቃሚ ሃሳቦች

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1–26

ጆሴፍ ስሚዝ የዳግም መመለስ ነቢይ ነው።

የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ አላማ ለእኛ “ተጨባጭ ነገሮችን ለመስጠት” ነበር፣ ምክንያቱም ስለ ጆሴፍ ያለው እውነታ ብዙውን ጊዜ የተዛባ ስለሆነ ነው (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1)። ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥1–26ን ስታነቡ፣ ስለእርሱ መለኮታዊ ጥሪ የእናንተን ምስክርነት የሚያጠነክረው ምንድን ነው? ለዚህ ነቢያዊ ተልዕኮ ጌታ እንዴት ጆሴፍ ስሚዝን እንዳዘጋጀው የሚገልጹትን ማስረጃዎች አስተውሉ። ስታነቡም፣ ስለጆሴፍ ስሚዝ እና ስለ ምስክርነቱ የሚሰማችሁን ስሜት መመዝገብም ትችላላችሁ።

በተጨማሪም ቅዱሳን፣ 1፥3–19ን ይመልከቱ።

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥5–20

በእምነት ከጠየኩ እግዚአብሔር ይመልሳል።

“ጥበብ ጎድሏችሁ” ወይንም መወሰን ስላለባችሁ ውሳኔ ግራ ተጋብታችሁ ታውቃላችሁን? (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥13)። ከቁጥሮች 5–20 ውስጥ ከሚገኙት የጆሴፍ ስሚዝ ተሞክሮ ምን ትማራላችሁ? ስለራሳችሁ ጥበብ መሻትና የላቀ መረዳት አስቡ፣ እናም እንዴት አድርጋችሁ እውነትን እንደምትሹ አስቡበት።

በተጨማሪም፣ 1 ኔፊ 10፥17–1915፥6–11፤ ራስል ኤም. ኔልሰን “ለቤተክርስቲያኗ ራዕይ፣ ለህይወታችን ራዕይ፣” ኤንዛይን ወይንም ሊያሆና፣ ግንቦት 2018 (እ.አ.አ)፣ 93–96 ይመልከቱ።

ምስል
ወጣት ሴት ስትጸልይ

በጸሎት አማካኝነት እግዚአብሔርን ጥያቄዎቻችንን መጠየቅ እንችላለን።

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥15–20

ስለመጀመሪያው ራዕይ የተለያዩ ጽሁፎች ያሉት ለምንድን ነው?

ጆሴፍ ስሚዝ በህይወት ሳለ በቅዱስ ጥሻ ውስጥ ያጋጠመውን ተሞክሮ አብዛኛውን ጊዜ ጸሀፊዎችን ተጠቅሞ ቢያንስ አራት ጊዜ ያህል ጽፏል። በተጨማሪም፣ ጆሴፍ ስለ ራእዩ ሲናገር በሰሙ ሰዎችም ቀጥተኛ ያልሆኑ ጽሁፎች ተጽፈዋል። ምንም እንኳን እነዚህ ጽሁፎች በአዳማጮቹና በሁኔታዎች አንጻር ይዞታቸው ቢለያዩም፣ በጠቅላላው ተመሳሳይ ናቸው። ልክ አራቱ ወንጌሎች የአዳኙን ተልዕኮ በደንብ እንድንረዳ እንደሚረዱን፣ እያንዳንዱ ጽሁፍ የየራሱን ማብራሪያ የያዘበመሆን ስለ ጆሴፍ ስሚዝ ተሞክሮ በደንብ እንድንረዳ ይረዱናል።

የጆሴፍን ተጨማሪ ጽሁፎች ለማንበብ “First Vision Accounts [የመጀመሪያ ራዕይ ጽሁፎች]” (Gospel Topics [የወንጌል አርዕስቶች]፣ topics.ChurchofJesusChrist.org) ይመልከቱ። እነዚህን ሁሉ ጽሁፎች በማንበብ ምን ተማራችሁ?

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥15–20

የመጀመሪያው ራዕይ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ዳግም መመለስ ጀመረ።

ጆሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚመልስለት አምኗል፣ ነገር ግን መልሱ የርሱንም ህይወት ሆነ አለምን እንዴት ሊቀይር እንደሚችል ሊገምት አይችልም ነበር። ስለ ጆሴፍ ስሚዝ ተሞክሮ ስታነቡ፣ የመጀመሪያው ራዕይ እንዴት አድርጎ ህይወታችሁን እንደቀየረው አሰላስሉ። ለምሳሌ ይህንን አረፍተ ነገር በተለያዩ መንገዶች በመመለስ ልታሟሉት ትችላላችሁ፥ “የመጀመሪያው ራዕይ በመከሰቱ የተነሳ፣ እኔ _______ አውቃለሁ።” በመጀመሪያው ራዕይ የተነሳ እንዴት ተባርካችኋል?

በተጨማሪም “እግዚአብሔርን ጠይቁ፥ የጆሴፍ ስሚዝ የመጀመሪያ ራዕይ፣” ቪዲዮ፣ ChurchofJesusChrist.orgቅዱሳን፣ 1፥14–19፤ ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “እርሱን ስሙት፣” ኢንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ግንቦት 2020 (እ.አ.አ)፣ 88-92 ይመልከቱ።

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥21–26

ምንም እንኳን ሌሎች ባይቀበሉኝም፣ ስለማውቀው ነገር በታማኝነት እጸናለሁ።

የቅዱሳት መጻህፍት አንዱ በረከታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት መከራን በተቀበሉ ፅኑ ወንዶችና ሴቶች አነቃቂ ተምሳሌት የተሞሉ መሆናቸው ነው። ጆሴፍ ስሚዝ ባየው ራዕይ አማካኝነት ተቃውሞ ሲደርስበት፣ ራዕይን አይቻለሁ በማለቱ ስደት ከደረሰበት ከሐዋሪያው ጳውሎስ ጋር ተመሳስሎ ነበር። ስለ ጆሴፍ ስሚዝ ተሞክሮ ስታነቡ፣ ምን ለምስክርነታችሁ ታማኝ ሆናችሁ እንድትቆዩ ያበረታታችኋል? ከቅዱሳት መጻህፍት እና ከምታውቋቸው ሰዎች በተጨማሪ ሌላ ምን አይነት ምሳሌዎች ላጋጠማችሁ መንፈሳዊ ተሞክሮ ታምናችሁ እንድትቆዩ ፅናትን ይሰጧችኋል?

ምስል
የቤተሰብ ጥናት ምልክቶች

ለቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ጠቃሚ ሃሳቦች

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥6ልክ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተገለጹት ሰዎች እንደሚያደርጉት ስያሆን ያሉንን ልዩነቶች ያለግጭት እንዴት አድርገን መፍታት እንችላለን?

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥11–13እነዚህን ጥቅሶች ማንበብ የቤተሰብ አባላትን የቅዱሳት መጻህፍት ክፍል ልባቸውን እንዴት እንደነካቸውና እንዴት ተግባራዊ ለማድረግ እንዳነሳሳቸው ለማካፈል ያነሳሳቸው ይሆናል።

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥16–20ቤተሰባችሁ እነዚህን ጥቅሶች በሚያነቡበት ወቅት፣ ከዚህ ክፍል ጋር የተያያዘውን ሰዕል ወይም ሌላ የመጀመሪያውን ራዕይ የሚያሳይ ፎቶ ለማሳየት አስቡበት (ምናልባትም ቤተሰባችሁ የራሳቸውን ምስል መሳል ያስደስታቸው ይሆናል)። በተጨማሪም “እግዚአብሔርን ጠይቁ፥ የጆሴፍ ስሚዝ የመጀመሪያ ራዕይ” የሚለውን ቪድዮ (ChurchofJesusChrist.org) መመልከት ትችላላችሁ። እያንዳንዳችሁ ስለ ራእዩ የተማራችሁትን እውነታ መመዝገብ፣ ከዚያም እያንዳንዳችሁ ለሌሎች የዘረዘራችሁትን ማካፈል ትችላላችሁ። ይህ የቤተሰብ አባላት ስለ ጆሴፍ ስሚዝ የመጀመሪያ ራዕይ ያላቸውን ምስክርነት እንዴት ማግኘት እንደቻሉ እንዲገልጹ የማድረግ መልካም ጊዜ ይሆናል።

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥17)።እግዚአብሔር ለጆሴፍ ስሚዝ በተገለጸ ወቅት ጆሴፍን በስሙ ጠራው። የቤተሰቦቻችሁ አባላት እግዚአብሔር በግል እንደሚያውቃቸው የተሰማቸው ጊዜ መቼ ነው?

ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥21–26ሰዎች ምስክርነታችንን ጥያቄ ላይ ሲጥሉ እንዴት መመለስ እንችላለን?

ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት፣ የዚህን ሳምንት ዝርዝርንኑ፣ ተከተሉኝ—ለልጆች ይመልከቱ።

የሚመከር መዝሙር፥ “የጆሴፍ ስሚዝ የመጀመሪያ ጸሎት፣” መዝሙር፣ ቁጥር 26።

ምስል
በዳግም የመመለስ ድምጾች ምልክት

በዳግም የመመለስ ድምጾች

የጆሴፍ ስሚዝ ቤተሰብ

እያንዳንዳችን በቤተሰባችን ህይወት ጥልቅ ተጽዕኖ ስር ነን፣ እና ጆሴፍ ስሚዝም ከዚህ የሚለይ አልነበረም። የቤተሰቡ የወንጌል ጽናትና ተግባሮች በዳግም መመለስ እንዲሳካ ያደረጉ የእምነት ዘሮችን ተክለዋል። የጆሴፍ የግል ማስታወሻ ይህንን አክብሮት ይዟል፥ “እንዲህ ያህል የተከበሩ ወላጆችን ለሰጠኝ እግዚአብሔር ያለኝን ምስጋና ለመግለጽ ቃላት እና ቋንቋ በቂ አይደሉም።”1

በስሚዝ ቤተሰብ ውስጥ ስለነበረው የወንጌል ተጽዕኖ የተወሰነ ለመገንዘብ፣ እናቱ ሉሲ ማክ ስሚዝ፣ ወንድሙ ዊሊያም ስሚዝ እና ራሱ ነቢዩ የተናገሩት ቀጣይ ጥቅሶችች ፍንጭ ይሰጡናል።

ምስል
የስሚዝ ቤተሰብ

የጆሴፍ ስሚዝ ቤተሰብ፣ በዳን ባክስተር

ሉሲ ማክ ስሚዝ

ምስል
ሉሲ ማክ ስሚዝ

[በ1802 (እ.አ.አ) አካባቢ] ታምሜ ነበር። … ለራሴም እንዲህ አልኩኝ፣ የክርስቶስን መንገድ ስለማላውቅ ለመሞት የተዘጋጀሁ አይደለሁም፣ ለእኔ እንደሚሰማኝ ከሆነ በእኔ እና በክርስቶስ መሃከል ላቋርጠው የማልደፍረው ጨለማ እና ጥልቅ ልዩነት እንዳለ ይሰማኛል። …

“ወደ ጌታ ተመለከትኩና ልጆቼንም ማሳደግ እንድችልና የባለቤቴንም ልብ ማጽናናት እንድችል ህይወቴን እንዲምርልኝ ለመንኩት ተማጸንኩትም፤ በዚህም ሁኔታ ለሊቱን ሙሉ አሳለፍኩ። … ከእግዚአብሔርም ጋር እንድኖር ከፈቀደልኝ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ይሁን ወይም የትም በሚገኝበት፣ ከመንግስተ ሰማያትም በእምነት እና ጸሎትም እሚገኝ ቢሆን እንኳን፣ እርሱን በአግባቡ እንዳገለግለው የሚያስችለኝን እምነት ለማግኘት ለመጣር ቃል ኪዳን ገባሁ። በስተመጨረሻም አንድ ድምጽ አናገረኝና እንዲህም አለኝ፣ ‘ለምኚ፣ ይሰጣሻል፤ ፈልጊ፣ ታገኚማለሽ፤ አንኳኪ፣ ይከፈትልሻል። ልብሽ ይጽና። በእግዚአብሔር ታምኛለሽ፤ በእኔም እመኚ።’ …

“ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ ብርታትን አገኘሁ። ምንም እንኳን አእምሮዬን በሞላ ቢቆጣጠረውም፣ ስለ ሃይማኖት ያለው አርዕስት ብዙ አላወራሁም፣ እናም ጠንቃቃ የሆነ ስለእግዚአብሔር መንገድ የሚያውቅ እና ስለሰማያዊ ነገሮች የሚያስተምረኝ ሰው ሳገኝ እያንዳንዱን ጥረት አደርጋለሁ ብዬ አሰብኩ።”2

ዊሊያም ስሚዝ

ምስል
ዊሊያም ስሚዝ

“በጣም ጠንቃቃ ሴት የነበረችው እና ስለልጆቿ ህይወት አሁንም ወደፊትም በጣም የምትጨነቅ የነበረችው እናቴ፣ የወላጅነት ፍቅሯ እስከሚፈቅደው ድረስ የነፍሳችንን ደህንነት ወይንም (በወቅቱ ይባል እንደነበረው) ‘ሃይማኖተኛ እንድንሆን’ የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ጥራለች። በስብሰባዎች እንድንሳተፍ ገፋፋችን፣ እናም ቤተሰቡ በሙሉ በዚህ ጉዳይ ፍላጎትን አሳየን እናም እውነትን ፈላጊ ሆንን”።3

“ማስታወስ እስከምችልበት ጊዜ ጀምሮ ሁልጊዜ የቤተሰብን ጸሎት እናደርግ ነበር። አባቴ መነጽሩን በሰደርያው ደረት ኪስ ውስጥ ያስቀምጠው እንደነበረ በደንብ አስታውሳለሁ፣ … እኛ ወንዶች ልጆቹ መነጽሩን መዳበስ ሲጀምር ጸሎት የመጀመሪያው ሰአት መድረሱን ማመላከቻ እንደሆነ እናውቃለን፣ እናም ካላየነው እናታችን እንዲህ ትላለች፣ ‘ ዊሊያም፣’ ወይም ያላስተዋለውን ሰው፣ ‘ለጸሎት ተዘጋጅ’ ትላለች። ከጸሎቱ በኋላ የምንዘምረው መዝሙርም ነበረን።”4

ምስል
መነጽር በቅዱሳት መጻህፍት ላይ

ጆሴፍ ቀዳማዊ እና ሉሲ ስሚዝ ቤተሰባቸውን ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑ አስተምረዋል።

ጆሴፍ ስሚዝ

ምስል
ጆሴፍ ስሚዝ

“አሁን እንዲህ እላለሁ፣ [የእኔ አባት] እኔ እስከማውቀው ድረስ በህይወቱ ጎጂ የሚባል ማንኛውንም መጥፎ ድርጊት ሲፈጽም አይቼው አላውቅም። አባቴንና ስለእርሱ ያሉኝን ትውስታዎች እወዳቸዋለሁ፤ ድንቅ የሆኑ ተግባሮቹም ትውስታ በአዕምሮዬ በግዝፈት ሰፍረዋል፤ እንዲሁም የእርሱ መልካምና አባታዊ ቃሎች በልቤ ማህተም ተጽፈዋል። ለእኔ የተቀደሱ የሆኑት፣ ከተወለድኩ ጀምሮ በራሴ የተገነዘብኳቸውና በአእምሮዬ የሚመላለሱ በዛም ሰፍረው የሚገኙ በጣም የምወዳቸው የህይወቱ ታሪኮች ናቸው። … እናቴም ከሁሉም የላቀችና ከሁሉም ሴቶች ምርጧ ናት።”5

ምስል
የመጀመሪያው ራዕይ

በዳግም መመለስ የመጀመሪያ ራዕይ፣ በማይክል ቤዳርድ

አትም