“ጥቅምት 2–8 (እ.አ.አ)። ኤፌሶን፤ ‘ቅዱሳን … ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ’” ኑ፣ ተከተሉኝን—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ አዲስ ኪዳን 2023 (እ.አ.አ) (2022 (እ.አ.አ))
“ጥቅምት 2–8 (እ.አ.አ)። ኤፌሶን፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ 2023 (እ.አ.አ)
ጥቅምት 2–8 (እ.አ.አ)
ኤፌሶን
“ቅዱሳን … ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ”
በአጠቃላይ ጉባኤ ውስጥ ባሉ መልእክቶች እና በጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ይታያችኋል?
ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ
በኤፌሶን ውስጥ ወንጌል መስፋፋት ሲጀምር በኤፌሶን ውስጥ “ብዙ ሁከት” ፈጥሯል (የሐዋርያት ሥራ 19፥23)። ለጣዖት አምላኪዎች ቤተ መቅደሶችን ይሰሩ የነበሩ የአካባቢው የእጅ ባለሞያዎች ክርስትናን ለኑሮአቸው እንደ ስጋት አድርገው ተመለከቱ፤ ብዙም ሳይቆይ “ቍጣ ሞላባቸው … ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ” (የሐዋርያት ስራ 19፥27–29ን ይመልከቱ)። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ወደ ወንጌል አዲስ የተለወጠ መሆንን አስቡ። በዚህ “ሁከት” (የሐዋርያት ሥራ 19፥40) ውስጥ ብዙ የኤፌሶን ሰዎች ወንጌልን ተቀብለው ኖረዋል፣ እናም ጳውሎስ “[ክርስቶስ] … ሰላማችን ነው” (ኤፌሶን 2፥13–14) በማለት አረጋገጠላቸው። እነዚህ ቃላት፥ “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ” (ኤፌሶን 4፥31) ከሚለው ግብዣ ጋር ጥንት እንደነበረው አሁንም ወቅታዊ እና የሚያጽናኑ ይመስላሉ። ለኤፌሶን ሰዎች፣ እንዲሁም ለእያንዳንዳችን፣ መከራን ለመቋቋም ጥንካሬ “በጌታ እና በኃይሉ ችሎት” ይመጣል (ኤፌሶን 6፥10–13ን ተመልከቱ)።
ለግል የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ሃሳቦች
እግዚአብሔር በምድር ላይ የተወሰኑ ኃላፊነቶችን ለመወጣት መርጦኛል ወይም አስቀድሞ ወስኗል።
ጳውሎስ ቅዱሳኑ “አስቀድመው የተወሰኑ” እና “ዓለም ከመፈጠሩ በፊት” የእርሱ ሰዎች እንዲሆኑ እግዚአብሔር እንደመረጣቸው ተናግሯል። ሆኖም፣ ፕሬዘደንት ሔንሪ ቢ. አይሪንግ እንዳመለከቱት፣ ይህ ማለት “እግዚአብሔር ልጆቹን የትኛውን እንደሚያድናቸው አስቀድሞ ወስኖ ወንጌልን ለእነሱ አቅርቦላቸዋል፤ ወንጌልን ፈጽሞ ያልሰሙት ደግሞ ባጭሩ ‘የተመረጡ’ አይደሉም ማለት አይደለም። … የእግዚአብሔር ዕቅድ እጅግ በጣም የፍቅር እና ከዚያ በላይ ነው። የሰማይ አባታችን ሁሉንም ቤተሰቡን ለመሰብሰብ እና ለመባረክ ይጨነቃል” (“የእግዚአብሔርን ቤተሰብ መሰብሰብ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2017 (እ.አ.አ) 20–21)። በቅዱስ ቤተመቅደሶች ውስጥ ለሙታን በተሠራው ሥራ ምክንያት ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች ወንጌልን እና ሥርዓቶቹን መቀበል ይችላሉ።
የማንም ሰው መዳን ወይም አለመዳን አስቀድሞ የተወሰነ ባይሆንም፣ የዘመናችን መገለጥ አንዳንድ የእግዚአብሔር ልጆች በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ዓላማዎች ለመፈጸም የተወሰኑ ኃላፊነቶችን ለመወጣት በቅድመ ዓለም ውስጥ እንደ ተመረጡ ወይም “እንደተወሰኑ” ያስተምራሉ። ኤፌሶን 1 ን እና ከወንጌል ርዕሶች “ቀድሞ መመረጥ” (topics.ChurchofJesusChrist.orgን በምታነቡበት ጊዜ፣ ይህ እውነት ለእናንተ እንዴት እንደሚተገበር አስቡ።
እግዚአብሔር “ሁሉንም በክርስቶስ ይጠቀልላል”
ዘመናችን ለምን “የዘመን ፍጽሜ” ተብሎ ይጠራል? “ሁሉንም በክርስቶስ መጠቅለል” ምን ማለት ሊሆን ይችላል? እነዚህን ሐረጎች ስታሰላስሉ የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ ኤፌሶን 4፥13፤ 2 ኔፊ 30፥7–8፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 110፥11–16፤ 112፥30–32፤ 128፥18–21። የእነዚህን ሐረጎች የራሳችሁን ማብራሪያዎች ለመጻፍ ልትነሳሱ ትችላላችሁ።
በተጨማሪም ዴቪድ ኤ. ቤድናርን “ሁሉን በክርስቶስ መጠቅለል፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2018 (እ.አ.አ) 21–24 ተመልከቱ።
ቤተክርስቲያን በሐዋርያት እና በነቢያት ላይ ተመስርታለች፤ እናም ኢየሱስ ክርስቶስ ዋናው የማዕዘን ድንጋይ ነው።
በኤፌሶን 2፥19–22፤ 3፥1–7፤ 4፥11–16፣ መሰረት ነቢያትና ሐዋርያት ያሉን ለምንድነው? በአጠቃላይ ጉባኤ ወቅት የሰማችኋቸውን የነቢያት እና የሐዋርያት መልእክቶች አስቡ። ትምህርታቸው ጳውሎስ የገለጻቸውን ዓላማዎች እንዴት ይፈጽማሉ? ለምሳሌ፣ እነዚህ ትምህርቶች “በትምህርት ነፋስ ሁሉ [እየተፍገመገማችሁ]” እንዳይሆን እንዴት ረድቷችኋል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የማዕዘን ድንጋይ የሚሆነው እንዴት ነው? እሱ ለሕይወታችሁ እንደ የማዕዘን ድንጋይ የሆነው እንዴት ነው?
በተጨማሪም የሐዋሪያት ስራ 4፥10–12ን ተመልከቱ።
የአዳኙን ምሳሌ መከተል የቤተሰቤን ግንኙነቶች ማጠናከር ይችላል።
ኤፌሶን 5፥21–6፥4ን በምታነቡበት ጊዜ በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያለው ምክር የቤተሰባችሁን ግንኙነቶች እንዴት እንደሚያጠናክር አስቡ።
በኤፌሶን 5፥22–24 ውስጥ የጳውሎስ ቃላት የተጻፉት በዘመኑ ማኅበራዊ ልማዶች አውድ ውስጥ መሆኑን ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። ዛሬ ነቢያት እና ሐዋርያት ወንዶች ከሴቶች እንደማይበልጡ እና ባለትዳሮች “እኩል አጋሮች” መሆን እንዳለባቸው ያስተምራሉ (“ቤተሰብ፤ ለአለም አዋጅ፣” ChurchofJesusChrist.orgን ተመልከቱ)። ያም ሆኖ አሁንም ኤፌሶን 5፥25–33፣ ውስጥ ጠቃሚ ምክርን ማግኘት ትችላላችሁ። ለምሳሌ፣ ክርስቶስ ለቅዱሳን ያለውን ፍቅር እንዴት ያሳያል? ይህ ባለትዳሮች እንደ እኩል አጋሮች እርስ በእርስ እንዴት መተያየት እንዳለባቸው ይጠቅሳል? በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለራሳችሁ ምን መልእክቶች ታገኛላችሁ?
የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ ከክፉ ነገር ይጠብቀኛል።
ኤፌሶን 6፥10–18ን በምታነቡበት ጊዜ ጳውሎስ እያንዳንዱን የጦር መሣሪያ ለምን እንደሰየመ አስቡ። “የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ” ከምን ይጠብቃችኋል? እያንዳንዱን የጦር መሣሪያ በየቀኑ ሙሉ በሙሉ ለመልበስ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
በተጨማሪም 2 ኔፊ 1፥23፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 27፥15–18
ለቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ሃሳቦች
-
ኤፌሶን 1፥10።ስለዚህ ጥቅስ ለማስተማር፣ ሽማግሌ ዴቪድ ኤ ቤድናር የገመድ ምሳሌን ተጠቅሟል (“ሁሉን በክርስቶስ መጠቅለል”ን ተመልከቱ)። የሽማግሌ ቤድናርን መልእክት ክፍሎች ስታጋሩ የቤተሰብ አባላትን ገመድ በማሳየት እንዲይዙትና እንዲመረምሩት አስቡ። እግዚአብሔር ሁሉንም በክርስቶስ እንዴት ይሰበስባል? በዚህ ስብሰባ ምክንያት እንዴት እንባረካለን?
-
ኤፌሶን 2፥4–10፤ 3፥14–21።በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተገለጸውን የእግዚአብሔር እና የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እና ምሕረት የተሰማቸውን ተሞክሮዎች የቤተሰብ አባላት እንዲያካፍሉ ጋብዙ።
-
ኤፌሶን 2፥12–19።ቤታችሁ ካለ ትራስ ወይም ሌሎች ነገሮች ግድግዳን በመገንባት፣ ከዚያ በማፍረስ ቤተሰባችሁ ሊደሰቱ ይችላሉ። ጳውሎስ በአሕዛብ እና በአይሁድ መካከል ያለውን “ቅጥር” ሲጠቅስ፣ ዛሬ ምን ዓይነት ቅጥር ሰዎችን ይለያል? ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህን ግድግዳዎች “ያፈረሰው” እንዴት ነው? እርሱ “እኛን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀው” እንዴት ነው? (ቁጥር 16)።
-
ኤፌሶን 6፥10–18።ቤተሰባችሁ የቤት እቃዎችን በመጠቀም የራሳቸውን “የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ” ሊሠሩ ይችላሉ። “የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ” ቪዲዮ (ChurchofJesusChrist.org) የቤተሰብ አባላት ይህንን ትጥቅ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲመለከቱ ሊረዳቸው ይችላል፣ “የእግዚአብሔር የጦር ዕቃ” (ጓደኛ፣ ሰኔ 2016 (እ.አ.አ)፣ 24–25) ውስጥ ቀላል ማብራሪያዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። እያንዳንዱ የጦር ዕቃ በመንፈስ የሚጠብቀን እንዴት ነው? በየቀኑ እርስ በርሳችን “የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሁሉ [እንድንለብስ]” ((ኤፌሶን 6፥11) ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?
ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ሳምንት ዝርዝር በኑ፣ ተከተሉኝ—ለመጀመሪያ ክፍል ተመልከቱ።
በሀሳብ የሚቀርብ መዝሙር፦ “የእስራኤል ተስፋ፣” መዝሙሮች፣ ቁጥር 259።