ምዕራፍ ፵፯
አማሊቅያ የላማናውያን ንጉስ ለመሆን ክህደትን፣ ግድያን፣ እናም ሴራን ተጠቀመ—ከኔፋውያን የተገነጠሉት ከላማናውያን የበለጡ ክፉዎች እና አስፈሪዎች ናቸው። በ፸፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እንግዲህ እኛም በምዝገባችን ወደ አማሊቅያና ከእርሱ ጋር ወደ ምድረበዳው ስለሸሹት እንመለስ፤ እነሆም፣ ከእርሱ ጋር የሄዱትን ይዞ ሄደ፣ እናም ወደ ኔፊ ምድር በላማናውያን መካከል ሄደ፣ እናም የላማናውያን ንጉስ ከኔፋውያን ጋር በድጋሚ እንዲዋጉ እራሳቸውን በአንድ ላይ እንዲሰበስቡ አዋጁን በምድሪቱ ላይ እስከሚልክ ድረስ ላማናውያንን በኔፊ ህዝብ ላይ ለቁጣ እንዲነሳሱ አደረገ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ አዋጁ በእነርሱ መካከል በደረሰ ጊዜ እጅግ ፈርተው ነበር፤ አዎን፣ ንጉሱን ለማስቀየምም ፈርተው ነበር፤ እናም ደግሞ ህይወታችንን እናጣለን በማለት ስለፈሩም ከኔፋውያን ጋር መዋጋትን አልደፈሩም። እናም እንዲህ ሆነ አልተቀበሉም ነበር፣ ወይም ከእነርሱም አብዛኛዎቹ የንጉሱን ትዕዛዛት አልተቀበሉም።
፫ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ንጉሱ ታዛዥ ባለመሆናቸው ተቆጥቶ ነበር፤ ስለዚህ ለትዕዛዛቱ ታዛዥ የሆኑትን ሠራዊት መሪነትን ለአማሊቅያ ሰጠ፤ እናም እንዲሄድና የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንዲይዙ እንዲያስገድዳቸው አዘዘው።
፬ እናም እነሆ ይህ የአማሊቅያ ፍላጎት ነበር፣ ክፉ ነገርን ለማድረግ የረቀቀ ሰው ነበር፣ ስለዚህ የላማናውያን ንጉስን ከዙፋኑ ለማውረድ በልቡ አቀደ።
፭ እናም አሁን ንጉሱን በሚወዱት ላማናውያን ክፍል ተቀባይነትን አገኘ፤ እናም ታዛዥ ባልሆኑትም ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ፈለገ፤ ስለዚህ ኦኒዳ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራም ሄደ፤ ምክንያቱም ላማናውያን በሙሉ ወደዚያ ስፍራ ሸሽተው ነበርና፤ ወታደሮቹ መምጣታቸውን በማወቃቸው፣ እናም እነርሱን እንደሚያጠፉአቸው ስለገመቱ የጦር መሳሪያዎቹ ወዳሉበት ስፍራ፣ ወደ ኦኒዳ ሸሹ።
፮ እናም ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት እንደማይገደዱ ቁርጥ ውሳኔን በአዕምሮአቸው ስለቀረፁ አንድን ሰው በራሳቸው ላይ ንጉሳቸው እናም መሪያቸው አድርገው ሾሙ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ለጦርነቱ ለመዘጋጀት አንቲጳስ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ጫፍ እራሳቸውን በአንድ ላይ ሰበሰቡ።
፰ እንግዲህ እንደንጉሱ ትዕዛዝ መሰረት ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት የአማሊቅያ አስተሳሰብ አልነበረም፣ ነገር ግን እነሆ፣ እራሱን የበላይ በማድረግ ያስቀምጥ ዘንድ፣ እናም ንጉሱንም ከዙፋኑ ያወርደው ዘንድ እናም መንግስቱንም ይወስድ ዘንድ በላማናውያን ወታደሮች መወደድ የእርሱ ፍላጎት ነበር።
፱ እናም እነሆ፣ የእርሱም ሠራዊት በአንቲጳስ ተራራ አጠገብ ባለው ሸለቆ ድንኳን እንዲጥሉ አደረገ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ምሽት በሆነም ጊዜ ወደ አንቲጳስ ተራራ ስሙም ሌሆንቲ ወደ ተባለው መሪያቸው ከእርሱ ጋር መነጋገር በመፈለጉ ወደ ተራራው ግርጌ ይመጣ ዘንድ በሚስጥር መልዕክተኛ ላከ።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ሌሆንቲ መልዕክቱን በተቀበለ ጊዜ ወደ ተራራው ግርጌ መሄድ አልደፈረም ነበር። እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ እንዲመጣለት ስለፈለገ ለሁለተኛ ጊዜ መልዕክተኛ ላከ። እናም እንዲህ ሆነ ሌሆንቲ ግን አልመጣለትም፤ እናም በድጋሚ ለሶስተኛ ጊዜ መልዕክተኛ ላከ።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ሌሆንቲን ከተራራው ለማስወረድ አለመቻሉን ባወቀ ጊዜ፣ ወደ ሌሆንቲ የጦር ሰፈር በመጠጋት ወደ ተራራው ሄደ፤ እናም እንዲመጣ በመፈለጉ ሌሆንቲ ጠባቂዎቹን ከእርሱ ጋር ይዞ እንዲመጣ በድጋሚ ለአራተኛ ጊዜ መልዕክተኛን ላከ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ሌሆንቲ ከጠባቂዎቹ ጋር ወደ አማሊቅያ በመጣ ጊዜ፣ ሌሆንቲ አማሊቅያን በሠራዊቱ ላይ ሁለተኛ መሪ የሚያደርገው ከሆነ፣ ከወታደሮቹ ጋር በምሽት ጊዜ እንዲመጣና፣ በጦር ሰፈራቸው ያሉትን ንጉሱ ትዕዛዝ የሰጣቸውን ሰዎች እንዲከቡአቸው፣ እናም እነርሱንም በሌሆንቲን እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ፈልጎ ነበር።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሌሆንቲ ከራሱ ሰዎች ጋር መጣና፣ የአማሊቅያን ሰዎች ከበቡአቸው፣ ስለዚህ ሌሊቱ ነግቶ ከመንቃታቸው በፊት በሌሆንቲ ወታደሮች ተከበው ነበር።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ መከበባቸውን በተመለከቱ ጊዜ እንዳይጠፉ ከወንድሞቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ይፈቅድላቸው ዘንድ አማሊቅያን ለመኑት። እናም ይህ አማሊቅያ የሚፈልገው ነገር ነበር።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ የራሱን ሰዎች ከንጉሱ ትዕዛዝ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ አሳልፎ ሰጣቸው። እናም ንጉሱን ከዙፋኑ ለማውረድ ያቀደው ይፈፀም ዘንድ አማሊቅያ የፈለገው ይህንን ነበር።
፲፯ እንግዲህ ዋናው መሪያቸው ከተገደለ ሁለተኛውን ዋና መሪ አድርጎ መሾም በላማናውያን መካከል የነበረ ልምድ ነበር።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ከአገልጋዮቹ አንዱ፣ ሌሆንቲ እንዲሞት ቀስ በቀስ መርዝ እንዲሰጠው አደረገ።
፲፱ እንግዲህ፣ ሌሆንቲ በሞተ ጊዜ፣ ላማናውያን አማሊቅያን መሪያቸው፣ እናም ዋና አዛዣቸው አድርገው ሾሙት።
፳ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ከወታደሮቹ ጋር (ፍላጎቱ ስለተፈፀመለት) ወደ ኔፊ ምድር፣ ወደ ኔፊ ከተማ፣ ዋና ከተማ ወደሆነችው ተንቀሳቀሰ።
፳፩ እናም ንጉሱ አማሊቅያ ትዕዛዙን ፈፅሟልና አማሊቅያ በርካታ ሠራዊቶቹ ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት እንዲሄዱ በአንድ ላይ ሰብስቧቸዋል ብሎ በመገመቱ ከጠባቂዎቹ ጋር እርሱን ለመገናኘት ሄደ።
፳፪ ነገር ግን እነሆ፣ ንጉሱ እርሱን ለማግኘት በሄደ ጊዜ፣ አማሊቅያ አገልጋዮቹ ንጉሱን እንዲያገኙት እንዲሄዱ አደረገ። እናም እነርሱ ሄዱና፣ በንጉሱ ፊት በታላቅነቱ ያከበሩት ለመምሰል ሰገዱለት።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱ ከኔፋውያን በወሰዱት ወግ ለሠላም ተምሣሌት እንደሆነው እንደላማናውያን ወግ እነርሱን ለማንሳት እጁን ዘረጋ።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱ የመጀመሪያውን ከመሬት ባነሳው ጊዜ፣ እነሆ ንጉሱን በልቡ ላይ ወጋው፤ እናም እርሱም በመሬት ላይ ወደቀ።
፳፭ እንግዲህ የንጉሱ አገልጋዮች ሸሹ፣ እናም የአማሊቅያ አገልጋዮች እንዲህ ሲሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ፥
፳፮ እነሆ፣ የንጉሱ አገልጋዮች ልቡን ወጉት፣ እናም እርሱ ወደቀ፣ እነርሱም ሸሹ፤ እነሆ፣ ኑና ተመልከቱ።
፳፯ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ወታደሮቹ ወደ ፊት እንዲጓዙና፣ ንጉሱ ምን እንደሆነ እንዲመለከቱ አዘዘ፤ እናም ወደ ስፍራው በመጡበት ጊዜ ንጉሱ ደምቶ ከመሬት ላይ ወድቆ ሲያገኙት፣ አማሊቅያ የተቆጣ አስመስሎ እንዲህ አለ፥ ንጉሱን የሚወድ ቢኖር፣ እንዲሄድ ይደረግና፣ የንጉሱንም አገልጋዮች አሳዶ ይግደላቸው።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ንጉሱን የሚወዱት በሙሉ፣ ይህንን ቃላት በሰሙ ጊዜ መጡ፣ እናም የንጉሱን አገልጋዮች ተከታተሉአቸው።
፳፱ እናም የንጉሱ አገልጋዮች ወታደሮቹ እንደተከታተሉአቸው በተመለከቱ ጊዜ በድጋሚ ፈርተው ነበር፣ እናም ወደ ምድረበዳው ሸሹና፣ ወደ ዛራሔምላ ምድር መጡና፣ ከአሞን ህዝብ ጋር ተቀላቀሉ።
፴ እናም የተከታተሉአቸው ወታደሮች በከንቱ ሁኔታ ከተከተሉአቸው በኋላ ተመለሱ፤ እናም አማሊቅያ እንደዚህ በማጭበርበር የህዝቡን ልብ አገኘ።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ በሚቀጥለው ቀንም ከሠራዊቱ ጋር ወደ ኔፊ ከተማ ገባ፣ እናም ከተማዋንም ተቆጣጠረ።
፴፪ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ንግስቲቱ ንጉሱ መገደሉን በሰማች ጊዜ—አማሊቅያ ለንግስቲቱ ንጉሱ በአገልጋዮቹ መገደሉን፣ እርሱም ከወታደሮቹ ጋር እንደተከተላቸው ነገር ግን ከንቱ እንደነበር፣ እናም እንዳመለጡአቸው መልዕክተኛ በመላክ አሳወቃት—
፴፫ ስለዚህ፣ ንግስቲቱ ይህንን መልዕክት በተቀበለች ጊዜ አማሊቅያ የከተማዋን ነዋሪዎች ህይወት እንዲያተርፍ እንደምትፈልግ ላከችበት፤ እናም ደግሞ እርሱ ወደ እርሷ እንዲመጣ ፈለገች፤ እናም ደግሞ የንጉሱን መሞት በተመለከተ ምስክሮችን ለመረጃ እንዲያመጣላት ፈለገች።
፴፬ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ንጉሱን የገደለውንና፣ ከእርሱ ጋር የነበሩትን አገልጋዮች በሙሉ ወሰደና፣ ንግስቲቱ በተቀመጠችበት ስፍራ ሄዱ፤ እናም የንጉሱ በራሱ አገልጋዮች መገደሉን ሁሉም መሰከሩላት፤ እናም ደግሞ እንዲህ አሉ፥ እነርሱም ሸሽተዋል፤ ይህ እራሱ በእነርሱ ላይ ምስክር አይሆንምን? የንጉሱን ሞት በተመለከተም እንደዚህ ንግስቲቱን አሳመኗት።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ የንግስቲቱን ድጋፍ ፈለገ፤ እናም አገባትና፣ በማጭበርበሩና፣ በብልጥ አገልጋዮቹ እርዳታ ግዛቱን እንደዚህ አገኘ፤ አዎን፣ በምድሪቱ ላይ ሁሉ ባሉ በላማናውያንና፣ በልሙኤላውያን፣ እናም በእስማኤላውያንና፣ ከኔፊ ንግስና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከኔፋውያን በተገነጠሉት ሁሉ መካከል ንጉስ መሆኑ ታወቀ።
፴፮ እንግዲህ እነዚህ ተገንጣዮች ከኔፋውያን አንድ ዓይነት ትምህርት እና መረጃ ነበራቸው፤ አዎን በዚሁ ዓይነት ሁኔታ ስለጌታ እውቀት ተምረው ነበር፤ ይሁን እንጂ ከመገንጠላቸው ብዙም ሳይቆይ፣ እንደ ላማናዊያን ባህል በመጠጣት፣ ለስንፍና፣ እናም ለሁሉም አይነትዝሙትነት ቦታ በመስጠት፣ አዎን፣ ጌታ አምላካቸውን ሙሉ በሙሉ ረሱት፣ ከላማናውያን የበለጠ ጠጣርና፣ ንስሃን የማይገቡ ስለመሆናቸው፤ እናም ኃጢአተኞችና፣ አስፈሪዎች ስለመሆናቸው ለመተረክ የሚያስገርም ነበር።