ምዕራፍ ፲
ጌታ ለኔፊ የማሰር ስልጣንን ሰጠው—በመሬትና በሰማይ እንዲያስር እናም እንዲፈታ ስልጣንን ሰጠው—ሰዎች ንስሃ እንዲገቡ አለበለዚያም እንዲጠፉ አዘዘ—መንፈስ ከብዙ ህዝብ ወደ ብዙ ህዝብ ወሰደው። ከ፳፩–፳ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ በህዝቡ መካከል መከፋፈል ተፈጠረ፤ ስለዚህ ወዲህና ወዲያ ተከፋፈሉ እናም ኔፊ በመካከላቸው ቆሞ ሳለ ብቻውን ጥለውት በተለያየ አቅጣጫ ሄዱ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊ ጌታ ያሳየውን ነገሮች በልቡ እያሰላሰለ ወደ ራሱ ቤት መንገዱን አቀና።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በሚያሰላስልበት ወቅት—በኔፊ ህዝብ የጨለማ ስራ፣ እንዲሁም ግድያና፣ ዝርፊያቸው፣ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት ክፋታቸው እጅግ በማዘኑ—እናም እንዲህ ሆነ በልቡ በሚያሰላስልበት ወቅት፣ እነሆ፣ ድምፅ እንዲህ ሲል ወደ እርሱ መጣ፥
፬ ኔፊ ባደረግሃቸው ነገሮች አንተ የተባረክህ ነህ፤ ምክንያቱም ለዚህ ህዝብ የሰጠሁህን ቃል በፅኑነት እንዴት እንዳወጅክ አይቻለሁና። እናም አልፈራሃቸውም፣ ለህይወትህም አልሰሰትህም፤ ነገር ግን የእኔን ፈቃድና ትዕዛዛቴን ለመጠበቅ ይህን አድርገሃልና።
፭ እናም አሁን በፅኑነት ይህንን በማድረግህ፣ እነሆ ለዘለዓለም እባርክሃለሁ፤ እናም በቃልህና በስራህ፣ በእምነትና በተግባርህም ብርቱ አደርግሃለሁ፤ አዎን ከፈቃዴ የሚቃረን ነገር ስለማትጠይቀኝ ሁሉም ነገሮች እንደቃልህ ይሆኑልሃል።
፮ እነሆ፣ አንተ ኔፊ ነህ፣ እኔም እግዚአብሔር ነኝ። እነሆ፣ በመላዕክቶቼ ፊት፣ በዚህ ህዝብ ላይ ስልጣን እንደሚኖርህና፣ እንደ ህዝቡ ክፋት ምድርን በረሃብና፣ በቸነፈር፣ እናም በጥፋት፣ ለመምታት እንደምትችል እገልፅልሃለሁ።
፯ እነሆ፣ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ እናም በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፤ እናም እንደዚህ በዚህ ህዝብ መካከልም ስልጣን ይኖርሃል።
፰ እናም ይህን ቤተመቅደስ ሁለት ቦታ ትከፈል የምትለው ከሆነ እንዲሁ ይሆናል።
፱ እናም ይህንን ተራራ ውደቅና ሜዳ ሁን ብትለው እንዲሁ ይሆናል።
፲ እናም እነሆ፣ እግዚአብሔር ይህን ህዝብ ይመታዋል የምትል ከሆነ እንዲሁ ይሆናል።
፲፩ እናም አሁን እነሆ፣ እንድትሄድና ሁሉን የሚገዛው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አለ ብለህ ለዚህ ህዝብ እንድታውጅ አዝሀለሁ፥ ንስሃ ካልገባችሁ እስክትጠፉ ድረስ ትመታላችሁ።
፲፪ እናም እነሆ አሁን እንዲህ ሆነ ጌታ እነዚህን ቃላት ለኔፊ በተናገረ ጊዜ፣ ኔፊ ቆመ፣ እናም ወደ ቤቱም አልሄደም፣ ነገር ግን በምድሪቱ ገፅ ላይ ተበታትነው ወደ ነበሩት ሰዎች ተመለሰ፤ እናም ንስሃ ካልገቡ መጥፋታቸውን በተመለከተ የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ጀመረ።
፲፫ እንግዲህ እነሆ፣ ስለዋናው ዳኛ ሞት ኔፊ ታላቁን አስደናቂ ነገር የተናገረ ቢሆንም ልባቸውን አጠጥረው ነበር፣ እናም የጌታን ቃላት አላዳመጡም።
፲፬ ስለዚህ ኔፊ የጌታን ቃል እንዲህ በማለት አወጀላቸው፥ ንስሃ ካልገባችሁ ይላል ጌታ፥ እስክትጠፉም ድረስ ትመታላችሁ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ኔፊ ቃሉን በተናገረ ጊዜ፣ እነሆ፣ ልባቸውን በማጠጠር ቀጠሉ፣ እናም ቃሉንም አላዳመጡትም ነበር፤ ስለዚህ ሰደቡትና፣ ወደ ወህኒ ቤት ይጥሉትም ዘንድ በእጃቸው ሊይዙት ፈለጉ።
፲፮ ነገር ግን እነሆ፣ የእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር ነበር፤ እናም እርሱን ይዘው ወህኒ ቤት ሊጥሉት አልቻሉም ነበር፣ ምክንያቱም በመንፈስ ተወሰደ፣ እናም ከመካከላቸውም ተወስዷል።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ለሁሉም እስከሚሰብክ ድረስ፣ ወይም በህዝቡ ሁሉ መካከል እስከሚልከው ድረስ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማወጅ፣ እንደዚህ ከህዝብ ወደህዝብ በመንፈስ ይሄድ ነበር።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ቃሉን አላዳመጡትም ነበር፤ እናም ፀብ ተጀመረ፣ ስለዚህ በመካከላቸው መከፋፈል ሆነና እርስ በእርሳቸው በጎራዴ መገዳደል ጀመሩ።
፲፱ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ሰባ አንደኛ የንግስ ዘመን በዚሁ ተፈፀመ።