ምዕራፍ ፮
ፃድቃን የሆኑት ላማናውያን ለኃጢአተኞቹ ኔፋውያን ሰበኩላቸው—ሁለቱም በሰላሙና በጥጋቡ ዘመን በለፀጉ—የኃጢያት ደራሲው፣ ሉሲፈር፣ የኃጢአተኞችን፣ እናም የጋድያንቶንን ዘራፊዎች በግድያና በክፋት ልባቸውን አነሳሳ—ዘራፊዎቹ የኔፋውያንን መንግስት ተቆጣጠሩ። ከ፳፱–፳፫ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ የመሣፍንቱ ስልሳ ሁለተኛው ዓመት የንግስና ዘመን በተፈፀመ ጊዜ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ሆኑ፣ እናም አብዛኞቹ ላማናውያን ፃድቃኖች ሆነው በእምነታቸው ብርታት እንዲሁም ፅኑነት ፅድቃቸው ከኔፋውያን ይበልጥ ነበር።
፪ እነሆም ብዙ ኔፋውያን ጠጣሮች፣ እንዲሁም ንስሃ የማይገቡ፣ እናም በአጠቃላይ ክፉዎች ነበሩ፤ በዚህም የተነሳ በመካከላቸው የመጡትን የእግዚአብሔርን ቃልና፣ ሁሉንም ስብከትና፣ ትንቢት አልተቀበሉም ነበር።
፫ ይሁን እንጂ፣ በላማናውያን መለወጥ የተነሳ፣ አዎን፣ በመካከላቸው በተቋቋመችው የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ምክንያት የቤተክርስቲያኗ ሰዎች ታላቅ ደስታ ነበራቸው። እናም እርስ በእርሳቸው በመተባበር፣ እናም አንደኛው ሌላኛውን አስደሰቱ፣ ታላቅ ደስታም ነበራቸው።
፬ እናም እንዲህ ሆነ ብዙ ላማናውያን ወደ ዛራሔምላ ምድር መጡና፣ ለኔፋውያን ሰዎች ስለመለወጣቸው ተናገሩ፣ እምነት እንዲኖራቸውም እንዲሁም ንስሃ እንዲገቡ አጥብቀው መከሯቸው።
፭ አዎን፣ እናም አብዛኛዎቹ ብዙዎቹን የእግዚአብሔርና የበጉ ትሁት ተከታዮች እንዲሆኑ ወደ ጥልቅ ትህትና ለማምጣት በታላቅ ኃይልና ስልጣን ሰበኩላቸው።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ብዙዎቹ ላማናውያን በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ተጓዙ፤ እናም ደግሞ ኔፊና ሌሂ ህዝቡን ለመስበክ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ተጓዙ። እናም ስልሳ ሦስተኛው ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ።
፯ እናም እነሆ በምድሪቱ ሁሉ ሰላም ሆነ፤ በዚህም የተነሳ ኔፋውያን ወደፈለጉት ማንኛውም ስፍራ፣ ከኔፋውያንም ሆነ ከላማናውያን ጋር ተጓዙ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያንም ደግሞ ከላማናውያንም መካከል ሆነ ከኔፋውያን መካከል መሄድ በፈለጉበት ስፍራ ሁሉ ሄዱ፤ እናም አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ለመግዛት እንዲሁም ለመሸጥ እንዲሁም እንደፍላጎታቸው ጥቅም ለማግኘት ነፃ ግንኙነት ነበራቸው።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያንም ሆኑ ኔፋውያን እጅግ ሀብታም ሆኑ፤ እናም በምድሪቱ በስተደቡብም ሆነ በስተሰሜን የተትረፈረፈ ወርቅና፣ ብር እንዲሁም የከበሩ ብረቶች በብዛት ነበሩአቸው።
፲ እንግዲህ የምድሪቱ ደቡቡ ክፍል ሌሂ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ እንዲሁም የምድሪቱ ሰሜኑ ክፍል በሴዴቅያስ ልጅ ስም ሙሌቅ ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ምክንያቱም ጌታ ሙሌቅን በምድሪቱ በሰሜን በኩል እንዲሁም ሌሂን በደቡብ በኩል አምጥቷቸዋልና።
፲፩ እናም እነሆ በእነዚህ በሁለቱም ቦታዎች ሁሉም ዓይነት ወርቅና፣ ከሁሉም ዓይነት ብር እንዲሁም የከበረ አፈር ነበር፤ እናም ደግሞ በጥንቃቄ የሚሰሩ፣ ሁሉንም ዓይነት አፈር የሚሰሩና የሚያጣሩ ነበሩ፤ ሀብታሞችም ሆኑ።
፲፪ እህልም በብዛት በስተሰሜን እንዲሁም በስተደቡብ አበቀሉ፤ እናም በደቡብም እንዲሁም በሰሜን በለፀጉ፤ እናም በምድሪቱ ተባዙ እንዲሁም እጅግ በረቱ። እናም ብዙ መንጋዎችንና ከብቶችን አዎን በብዛት ጠቦቶችን አረቡ።
፲፫ እነሆ ሴቶቻቸው ጥረዋልና፣ ፈትለዋል፣ እናም ሁሉንም የተፈተለ ጥሩ በፍታ ዓይነት ልብሶችና እርቃናቸውን ለመሸፈን ማንኛውንም ዓይነት ልብስ አዘጋጅተዋል። እናም ስልሳ አራተኛው ዓመት በሰላም እንደዚህ አለፈ።
፲፬ እናም በስልሳ አምስተኛውም ዓመት ደግሞ ታላቅ ደስታና ሰላም፣ አዎን ብዙ ስብከትና የሚመጣውን በተመለከተ ብዙ ትንቢቶች ነበሯቸው። እናም ስልሳ አምስተኛው ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ስልሳ ስድስተኛ ዓመት የንግስ ዘመን፣ እነሆ ሴዞራም ባልታወቀ ሰው በፍርድ ወንበሩ ተቀምጦ ሳለ ተገደለ። እናም እንዲህ ሆነ በዚሁ ዓመት፣ በእርሱ ምትክ በህዝቡ የተሾመው ወንድ ልጁ ደግሞ ተገደለ። ስልሳ ስድስተኛው ዓመትም እንደዚህ ተፈፀመ።
፲፮ እናም በስልሳ ሰባተኛው ዓመት መጀመሪያ ላይ ህዝቡ በኃጢያት እጅግ ማደግ ጀመረ።
፲፯ እነሆም ጌታ ለቁጣ፣ ለጦርነትም፣ ይሁን ለደም መፋሰስ እንዳይነሳሱ በምድራዊ ሀብት ለብዙ ጊዜ ባረካቸው፤ ስለዚህ ልባቸውን በሀብታቸው ላይ ማድረግ ጀመሩ፤ አዎን በድጋሚም አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እራሳቸውን ከፍ ለማድረግ ፈለጉ፤ ስለዚህ ያገኙም ዘንድ በድብቅ ግድያን፣ እናም ስርቆትን እንዲሁም ዝርፊያን መፈፀም ጀመሩ።
፲፰ እናም አሁን እነሆ የገዳዮቹና የዘራፊዎቹ ቡድን በቂሽቁመን እንዲሁም ጋድያንቶን የተቋቋሙት ነበሩ። እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ከጋድያንቶን ቡድን ከኔፋውያንም መካከል ብዙዎች ነበሩ። ነገር ግን እነሆ ኃጢአተኞች ከሆኑት ላማናውያን መካከል በቁጥር ብዙ ነበሩ። እናም የጋድያንቶን ሌቦች እንዲሁም ገዳዮች ተብለው ይጠሩ ነበር።
፲፱ እናም እነርሱ ናቸው ዋናውን ዳኛ ሴዞራምን እንዲሁም ልጁን በፍርድ ወንበሩ ላይ እንዳለ የገደሉት፤ እናም እነሆ፣ ማናቸውም አልተገኙም ነበር።
፳ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ላማናውያን በመካከላቸው ሌቦች እንዳሉ ባወቁ ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ እናም ከምድረ ገፅ እነርሱን ለማጥፋት በኃይላቸው ማንኛውንም መንገድ ተጠቀሙ።
፳፩ ነገር ግን እነሆ ሰይጣን የአብዛኞቹን የኔፋውያን ልብ አነሳሳ፤ በዚህም የተነሳ ከሌቦቹ ቡድን ጋር በግድያቸው እንዲሁም በዝርፊያቸውና በስርቆታቸው እንዳይሰቃዩ፣ በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢቀመጡ እርስ በራስ እንዲረዳዱ፣ ከእነርሱ ጋር ተቀላቀሉ እናም ወደ እነርሱ ቃል ኪዳን እንዲሁም መሃላ ገቡ።
፳፪ እናም እንዲህ ሆነ የራሳቸው ምልክቶች ነበሩአቸው፤ አዎን፣ ሚስጥራዊ ምልክትና፣ ሚስጥራዊ ቃላት፤ እናም ይህንም ያደረጉት ወደ ቃል ኪዳኑ የገባውን ወንድም ይለዩበት ዘንድ፣ አባሉ ኃጢያት የሆነን ማንኛውንም ነገር ቢያደርግ ቃል ኪዳን በገባው በወንድሙም ሆነ በቡድኑ እንዳይጎዱ ዘንድ ነበር።
፳፫ እናም ከሀገራቸው ህግጋት እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር ህግጋት ጋር ተቃራኒ የሆኑትን ግድያዎችና፣ ዝርፊያዎች፣ እናም ስርቆትና፣ ዝሙትን እንዲሁም ሁሉንም ዓይነት ክፋት እንደዚህ ለመፈፀም ይችሉ ዘንድ።
፳፬ እናም ከእነርሱ ቡድን የሆነ ማንኛውም ሰው ለዓለም ኃጢአታቸውን እንዲሁም እርኩሰታቸውን ቢገልፅ፤ እንደ ሀገራቸው ህግ ሳይሆን በጋድያንቶን እና በቂሽቁመን በተሰጡት የክፋታቸው ህግጋት መሰረት ለፍርድ ይቀርባል።
፳፭ እናም እነሆ፣ ይህ ሚስጥራዊ መሃላና ቃል ኪዳን አልማ ለልጁ ህዝቦችን ወደ ጥፋት የሚወስድ ዘዴ እንዳይሆን በመፍራቱ ወደ ዓለም እንዳይሄድ ያዘዘበት ነው።
፳፮ እንግዲህ እነሆ እነዚህ ሚስጥራዊ መሃላዎችና ቃል ኪዳኖች ለሔለማን ከተሰጡት መዛግብት ለጋድያንቶን አልመጡም፤ ነገር ግን እነሆ፣ የተከለከለውን ፍሬ እንዲቀምሱ የመጀመሪያ ቤተሰቦቻችንን ያታለለው ያው ፍጡር እነዚህን በጋድያንቶን ልብ ውስጥ አስቀምጦ ስለነበር ነው—
፳፯ አዎን ወንድሙን አቤልን ቢገድለው ዓለም እንደማያውቀውም ከቃየን ጋር ያሴረው ይኸው ፍጡር ነበር። እናም እርሱም ከቃየንና ከተከታዮቹ ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሴረ።
፳፰ ደግሞም ረጅም ግንብ ገንብተው ሰማይ መድረስን በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ያደረገውይህ ፍጡር ነው። እናም እነዚያን ሰዎች ከግንቡ ወደዚህ ምድር የመጡትን የገፋፋቸው፤ ፍፁም ወደሆነ ጥፋት እናም ዘለዓለማዊ ወደሆነው ገሃነም እስከሚጎትታቸው ድረስ የጨለማን እንዲሁም የእርኩሰትን ስራ በምድር ገፅ እንዲበተን ያደረገውም ይኸው ፍጡር ነው።
፳፱ አዎን፣ አሁንም የጨለማውን ስራ እንዲሁም ሚስጥራዊ ግድያውን እንዲያደርግ በጋድያንቶን ልብ ውስጥ ያስገባውም ይህ ፍጡር ነው፤ እናም ከሰው ልጅ መፈጠር ጀምሮ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ይህን ያመጣው ይኸው ፍጡር ነው።
፴ እናም እነሆ የኃጢያት ሁሉ ደራሲው እርሱ ነው። እናም እነሆ፣ እርሱም የጨለማውን ስራ እንዲሁም ሚስጥራዊ ግድያውን ቀጥሎበታል፣ እንዲሁም በሰው ልጆች ልብ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ እስከቻለ ይህንን ሴራ፣ መሃላቸውንና ቃል ኪዳናቸውን እንዲሁም ይህንን አሰቃቂ የኃጢያት ዓላማ ከትውልድ እስከ ትውልድ ያስተላልፋል።
፴፩ እናም እንግዲህ እነሆ፣ በኔፋውያን ልብ ላይ ታላቅ የሆነ ተፅዕኖ አግኝቷል፤ አዎን፣ ስለዚህም እነርሱ እጅግ ኃጢአተኞች ሆነዋል፤ አዎን፣ ብዙዎቹም ከፅድቅ ጎዳና ርቀዋል፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በእግራቸው ስር ረግጠውታል፣ እናም በራሳቸው አመለካከት ሄደዋል፣ እናም ከወርቆቻቸው እንዲሁም ከብራቸው ለራሳቸው ጣኦቶችን ሰርተዋል።
፴፪ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህ ሁሉ ክፋቶች በእነርሱ ላይ የመጡት በረጅም ጊዜ ውስጥ አይደለም፤ ስለዚህ አብዛኛዎቹ ክፋቶች የሆኑት በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ስልሳ ሰባተኛ ዓመት የንግስና ዘመን ውስጥ ነበር።
፴፫ እናም ለፃድቃኖች ታላቅ ሀዘን እንዲሁም ለቅሶ፣ በስልሳ ስምንተኛው ዓመት ደግሞ በክፋታቸው ጨመሩ።
፴፬ እናም ላማናውያን በአምላካቸው እውቀት ማደግ፣ አዎን እነርሱ ስርዓቶችንና ትዕዛዛቱን መጠበቅ፣ እናም በፊቱም በእምነት እንዲሁም በቀጥታ መራመድ በጀመሩበት ጊዜ፣ ኔፋውያን እምነት አጥተው መመንመን እንዲሁም በክፋትና በእርኩሰት ማደግ መጀመራቸውን እንደዚህ እንመለከታለን።
፴፭ እናም በኃጢአታቸውና ልባቸውን በማጠጠራቸው የተነሳ የጌታ መንፈስ ከኔፋውያን መለየት እንደጀመረ እንመለከታለን።
፴፮ እናም ላማናውያን የማያስቸግሩና ቃሉን ለማመን ፈቃደኞች በመሆናቸው ጌታ ከመንፈሱ በላያቸው ላይ ማፍሰስ መጀመሩን ተመለከትን።
፴፯ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን የጋድያንቶንን የዘራፊዎች ቡድን አደኑ፤ እናም ይበልጥ ኃጢአተኞች በሆኑትም መካከል የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ስለዚህ እነዚህ የዘራፊዎች ቡድን ከላማናውያን መካከል ፈፅመው ጠፉ።
፴፰ እናም እንዲህ ሆነ በሌላ በኩል እጅግ ኃጢአተኛ ከሆኑት ጀምሮና ፃድቃን የሆኑት አብዛኞቹም በስራቸው እስከሚያምኑና፣ ከዘረፉት እስከሚካፈሉ፣ እናም በሚስጥራዊው ግድያቸውና፣ ቅንጅታቸው ከእነርሱ ጋር እስከሚገናኙ ድረስ በማባበል፣ ኔፋውያን እነርሱን አሳደጓቸውና ደገፏቸው።
፴፱ እናም እንደዚህ ብቸኛውን የመንግስት አስተዳደር አገኙ፤ በድሆች እንዲሁም በየዋሆች እንዲሁም ትሁት የእግዚአብሔር ተከታዮች ላይ ጀርባቸውን መለሱባቸው፣ በእግራቸውም ሥር ረገጡአቸው፣ እናም መቱአቸውና፣ አሰቃዩአቸው።
፵ እናም በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሁም ለዘለዓለማዊው ጥፋት መዳረሳቸውን ተመለከትን።
፵፩ እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ስልሳ ስምንተኛ ዓመት የንግስና ዘመን ተፈፀመ።