ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲


ምዕራፍ ፲

ንጉስ ላማን ሞተ—ህዝቡም አረመኔና የሚያስፈሩ እንዲሁም በሐሰት ባህል የሚያምኑ ነበሩ—ዜኒፍና ህዝቡ ድል አደረጉአቸው። ከ፻፹፯–፻፷ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ መንግስቱን መመስረት ጀመርን፣ እናም እንደገና ምድሪቱን በሰላም መውረስ ጀመርን። እናም ላማናውያን በድጋሚ ከህዝቤ ጋር ለመዋጋት በሚመጡበት ጊዜ ለህዝቤ መሳሪያ ይኖራቸው ዘንድ ከሁሉም ዓይነት የተሰሩ የጦር መሳሪያዎች እንዲኖራቸው አደረግሁ።

እናም ላማናውያን ሳናውቀው መጥተው እንዳያጠፉን በምድሪቱ ዙሪያ ጠባቂዎችን አስቀመጥሁ፤ እናም ህዝቤንና መንጋዎቼን እንደዚህ ጠበቅሁ፣ እናም በጠላቶቻችን እጅ እንዳይወድቁም ጠበቅኋቸው።

እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ዓመታት የአባቶቻችንን ምድር ወረስን፤ አዎን፣ እንዲሁም ለሀያ ሁለት ዓመታት።

እናም ሰዎች መሬቱን እንዲያርሱ፣ እናም ሁሉንም ዓይነት እህልና፣ ሁሉንም ዓይነት ፍራፍሬዎች እንዲያሳድጉ አደረግሁ።

እናም ሴቶች እንዲፈትሉ፣ እንዲደክሙም፣ እንዲሰሩም፣ እናም ሁሉንም ዓይነት ናይለን ጨርቅ፣ አዎን፣ ሁሉንም ዓይነት ልብሶች በመስራት እርቃናችንን እንሸፍንበት ዘንድ እንዲሰሩ አደረግሁ፤ እናም እንደዚህ በምድሪቱ ላይ በለፀግን—እንደዚህም በምድሪቱ ላይ ለሀያ ሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ ሰላምን አገኘን።

እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ላማን ሞተና፣ በቦታው ልጁ ነገሰ። እናም ህዝቡን ከህዝቤ ጋር በአመፅ ማወክ ጀመረ፤ ስለዚህ እነርሱ ለጦርነት መዘጋጀትና፣ ከህዝቤ ጋር ለመዋጋት መምጣት ጀመሩ።

ነገር ግን ዝግጅታቸውን እንዳውቅ፣ በህዝቤ ላይ እንዳይመጡና እንዳያጠፉአቸው ከእነርሱ እጠብቃቸው ዘንድ በሻምሎን ምድር ዙሪያ ሰላዮቼን ላክሁ።

እናም እንዲህ ሆነ በቀስትም፣ በጦርም፣ በሳንጃና ሻምላም፣ በድንጋይም፣ እንዲሁም በወንጭፍ በታጠቁ ብዙ ሰራዊቶቻቸው ከሼምሎን ምድር በስተሰሜን በኩል መጡ፤ እናም ራሳቸው በመላጨቱ ባዶ ነበር፣ እናም በወገባቸው ላይ የቆዳ መቀነት ታጥቀው ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ከህዝቤ ሴቶችና ህፃናት በምድረበዳው እንዲደበቁ አደረግሁ፤ እናም ደግሞ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው መምጣት የሚችሉ ሽማግሌዎች ሁሉና ደግሞ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው መምጣት የሚችሉ ወጣት ወንዶች ከላማናውያኖች ጋር ለመዋጋት በአንድ ላይ ራሳቸውን እንዲሰበስቡ አደረግሁ፤ እናም እያንዳንዱን ሰው እንደ ዕድሜው በደረጃው አሰለፍኳቸው።

እናም እንዲህ ሆነ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ሄድን፤ እናም እኔም እንኳን በእርጅና ዕድሜዬ፣ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ሄድኩ። እናም እንዲህ ሆነ በጌታ ጥንካሬ ለጦርነት ሄድን።

፲፩ አሁን፣ ላማናውያን የጌታንም ሆነ የጌታን ጥንካሬ በተመለከተ ምንም አያውቁም፣ ስለዚህ በራሳቸው ጥንካሬ ተመክተው ነበር። ይሁን እንጂ እንደሰዎች ጥንካሬ ጠንካራ ነበሩ።

፲፪ እነርሱም አረመኔና የሚያስፈሩ እንዲሁም ደም የተጠሙ፣ ይህም በሆነው—ከኢየሩሳሌም ምድር በአባቶቻቸው ክፋት እንደወጡ፣ እናም በምድረበዳ በወንድሞቻቸው ክፉ እንደተደረገባቸው፣ እናም ደግሞ ባህሩን በሚያቋርጡበት ጊዜ ክፉ እንደተደረገባቸው በማመን፣ በአባቶቻቸው ባህል የሚያምኑ ነበሩ፤

፲፫ እናም በድጋሚ ባህሩን ከተሻገሩ በኋላ በመጀመሪያው የውርስ አገራቸው በነበሩ ጊዜ ክፉ ተደርጎባቸው ነበር፣ እና ይህ ሁሉ የሆነው ኔፊ ከሁሉም በበለጠ የጌታን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ታማኝ በመሆኑ—ስለዚህ እርሱ በጌታ የተደገፈ ነበር፣ ጌታም ፀሎቱን ሰምቶን መልስ ሰጥቶታልና፣ እናም በምድረበዳ ጉዞአቸው መሪነትን ወስዷልና።

፲፬ እናም ወንድሞቹ በእርሱ ተቆጡ፣ ምክንያቱም የጌታን አድራጎት አልተረዱምና፣ ውኃውንም ደግሞ ሲያቋርጡ ተቆጥተው ነበር፣ ምክንያቱም በጌታ ላይ ልባቸውን አጠጥረው ነበርና።

፲፭ እናም እንደገና፣ በቃል ኪዳኑ ምድር በደረሱበት ጊዜ የህዝቡን አገዛዝ ከእጃችን ወስዷል በማለትበእርሱ ተቆጥተው ነበር፤ እናም ሊገድሉት ፈለጉ።

፲፮ እናም እንደገና፣ ጌታ እንዳዘዘው ወደ ምድረበዳ በመሸሹ፣ እናም በነሃስ ሰሌዳዎች ላይ የተፃፉትን መዝገቦች በመውሰዱ ዘርፎናል በማለት ተቆጥተው ነበር።

፲፯ እናም እንደዚህ ልጆቻቸው እንዲጠሉአቸውና እንዲገድሉአቸው፣ እናም እንዲሰርቋቸውና እንዲዘርፏቸው፣ እናም እነርሱን ለማጥፋት የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አስተምረዋቸዋል፤ ስለዚህ በኔፊ ልጆች ላይ ዘለዓለማዊ ጥላቻ አላቸው።

፲፰ ለዚህም ዋና ምክንያት ንጉስ ላማን ህዝቤን ያጠፋቸው ዘንድ ወደዚህ ምድር እንዳመጣ በሚያባብል በውሸት ተንኮል እናም በመልካም ቃሉ አታለለኝ፤ አዎን፣ እናም በምድሪቱ ላይ ለብዙ ዓመታት ተሰቃየን።

፲፱ እናም አሁን፣ እኔ ዜኒፍ፣ ላማናውያንን በተመለከተ ለህዝቤ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከተናገርኩ በኋላ፣ እምነታቸውን በጌታ ጥለው ባላቸው ኃይል ወደ ጦርነቱ እንዲሄዱ አበረታታኋቸው፤ ስለዚህ ፊት ለፊት ከእነርሱ ጋር ተዋጋን።

እናም እንዲህ ሆነ በድጋሚ ከምድራችን አስወጣናቸው፣ እናም በከፍተኛ ግድያ ጨፈጨፍናቸው፤ እንዲያውም በጣም ብዙ ሆነው አልቆጠርናቸውም።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ራሳችን ምድር በድጋሚ ተመለስን፣ እናም ህዝባችን በድጋሚ መንጋዎቻቸውን መጠበቅና፣ መሬታቸውን ማረስ ጀመሩ።

፳፪ እናም አሁን፣ እኔ በማርጀቴ፣ መንግስቱን ከልጆቼ ለአንዱ ሰጠሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ምንም አልናገርም። እናም ጌታ ህዝቤን ይባርክ። አሜን።