የዜኒፍ መዝገብ—የዛራሔምላን ምድር ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ከላማናውያን እጅ እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ ያለው የህዝቡ ታሪክ።
ከምዕራፍ ፱ እስከ ምዕራፍ ፳፪ አጠቃሎ የያዘ።
ምዕራፍ ፱
ዜኒፍ የሌሂ-ኔፊን ምድር እንዲወርሱ ከዛራሔምላ ቡድንን መራ—የላማናውያን ንጉስ ምድሪቱን እንዲወርሱ ፈቀደላቸው—በላማናውያንና በዜኒፍ ህዝብ መካከል ጦርነት ሆነ። ፪፻–፻፹፯ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እኔ ዜኒፍ፣ በኔፋውያን ቋንቋዎች ሁሉ በመማሬ፣ እናም ስለኔፊ ምድር ወይም የመጀመሪያው የአባታችን የውርስ ምድር በማወቄ፣ እናም የእኛ ወታደሮች በእነርሱ ላይ መጥተው ያጠፏቸው ዘንድ ኃይላቸውን ለመሰለል በላማናውያን መካከል ሰላይ ሆኜ ተላኩ፣ ነገር ግን በእነርሱ መካከል ጥሩ የሆነን ነገር በተመለከትኩ ጊዜ እንዳይጠፉ ፈለግሁ።
፪ ስለዚህ፣ መሪያችን ከእነርሱ ጋር ስምምነት እንዲፈፅም በመፈለጌ በምድረበዳ ውስጥ ከወንድሞቼ ጋር ተከራከርኩ፤ ነገር ግን እርሱ ጨካኝና ደም የተጠማ ሰው በመሆኑ እንድገደል ወሰነብኝ፤ ነገር ግን በብዙ ደም መፋሰስ ዳንኩ፤ ምክንያቱም ብዙ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች በምድረበዳ እስከሚጠፉ ድረስ አባት ከአባት፣ እናም ወንድም ከወንድም ተዋግተዋልና፤ እናም እኛ የተረፍነው የሞቱትን ታሪክ ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው ለመተረክ ወደዛራሔምላ ምድር ተመለስን።
፫ እናም፣ የአባቶቻችንን ምድር ለመውረስ በጣም በመጓጓት፣ ምድሪቱን ለመውረስ የፈለጉት ሁሉ ሰበሰብኩኝ፣ እናም ወደ ምድሪቱ ለመሄድ ጉዞአችንን በድጋሚ ወደ ምድረበዳ ጀመርን፤ ነገር ግን በረሃብና በታላቅ ስቃይ ተመታን፣ ምክንያቱም ጌታ አምላካችንን ለማስታወስ ዘግይተናልና።
፬ ይሁን እንጂ፣ ብዙ ቀናት በምድረበዳ ውስጥ ከተዘዋወርን በኋላ፣ ለአባቶቻችን ምድር ቅርብ በሆነው ወንድሞቻችን በተገደሉበት ስፍራ ድንኳናችንን ተከልን።
፭ እናም እንዲህ ሆነ የንጉሱን ዓላማ አውቅ ዘንድ፣ እናም ከህዝቤ ጋር መሄድና፣ ምድሪቱን በሰላም መውረስ እንችል እንደሆነ አውቀው ዘንድ ከአራቱ ሰዎቼ ጋር በድጋሚ ወደከተማው፣ ወደንጉሱ ሄድኩኝ።
፮ እናም ወደ ንጉሱ ሔድኩ፣ እናም የሌሂ-ኔፊን ምድር እንዲሁም የሼምሎንን ምድር እይዘው ዘንድ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባ።
፯ እናም ደግሞ የእርሱ ህዝብ ምድሪቱን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው አዘዘ፣ እናም እኔና ህዝቤ ምድሪቱን ለመያዝ ሄድን።
፰ እናም ህንፃዎችን መገንባትና፣ የከተማውን ግንብ፣ አዎን፣ እንዲሁም የሌሂ-ኔፊ ከተማ ግንቦችንና የሼምሎንን ከተማ መጠገን ጀመርን።
፱ እናም አዎን፣ በሁሉም ዓይነት ዘሮች እንኳን፣ በበቆሎ ዘርና፣ በስንዴ፣ በገብስም፣ በኒአስም፣ በሺአምም፣ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት የፍራፍሬ ዘሮች ምድሪቱን ማረስ ጀመርን፤ እናም በምድሪቱ ላይ መራባትና መበልፀግ ጀመርን።
፲ አሁን ንጉስ ላማን ህዝቤን ወደ ባርነት ለማምጣት፣ እኛ የያዝነውን ምድር የሰጠው በጮሌነቱና በብልጠቱ ነው።
፲፩ ስለዚህ እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ላይ ለአስራ ሁለት ዓመታት ከኖርን በኋላ፣ ንጉስ ላማን መቁነጥነጥ ጀመረ፣ ይህም የሆነበት እንዳያይሉባቸው እናም ወደባርነት እንዳያመጡዋቸው ህዝቤ በምድሪቱ እየበረቱ በመሄዳቸው ነበር።
፲፪ አሁን እነርሱ ሰነፍና ጣዖት አምላኪ ነበሩ፣ ስለዚህ እኛ በእጆቻችን በሰራነው እራሳቸውን ያንደላቅቁ ዘንድ፣ አዎን፣ በሜዳችን መንጋዎች እራሳቸውን ይመግቡ ዘንድ፣ በባርነት ስር ሊያደርጉን ፈልገው ነበር።
፲፫ ስለዚህ እንዲህ ሆነ ንጉስ ላማን ህዝቡ ከህዝቤ ጋር ይከራከር ዘንድ ማወክ ጀመረ፤ ስለዚህ በምድሪቱ ጦርነትና ፀብ ተጀመረ።
፲፬ በኔፊ ምድር በአስራ ሶስተኛው የንግስና ዓመቴ፣ በሼምሎን የደቡብ ክፍል፣ ህዝቤ መንጋውን ውሃ ሲያጠጡና ሲመግቡ፣ እናም መሬታቸውን ሲያርሱ ብዙ ላማናውያን በአንድነት መጥተው እነርሱን መግደልና መንጋዎቻቸውንና በቅሎዎቻቸውንም መውሰድ ጀመሩ።
፲፭ አዎን፣ እናም እንዲህ ሆነ ያልተያዙት ሁሉ ወደ ኔፊ ከተማም ጭምር ሸሹ፣ እናም እኔ እንድከላከላቸውም ፈለጉኝ።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ በቀስትና፣ በወስፈንጥርና፣ በጎራዴ፣ እናም በሻሙላ፣ በቅስትና፣ በወንጭፍ፣ እንዲሁም መስራት በምንችለው በሁሉም ዓይነት መሳሪያዎች ሁሉ እንዲታጠቁ አደረኩኝ፣ እናም እኔና ህዝቤ ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ሄድን።
፲፯ አዎን፣ በጌታ ጥንካሬን ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት ሄድን፤ እኔና ህዝቤ ከጠላቶቻችን እጅ ያወጣን ዘንድ በኃይል ወደ ጌታ ጮህን፣ የአባቶቻችንን የዳኑበትን ለማስታወስ ነቅተናልና።
፲፰ እናም እግዚአብሔር ጩኸታችንን ሰማ፣ ለፀሎታችንም መልስ ሰጠ፤ እናም በኃይሉ ወደፊት ሄድን፣ አዎን፣ በላማናውያን ላይ ሄድን፣ እናም በአንድ ቀንና ሌሊት ሶስት ሺህ አርባ ሶስት ሰዎችን ገደልን፤ ከምድራችንም እስክናስወጣቸው ድረስ ገደልናቸው።
፲፱ እናም፣ እኔ፣ በራሴ እጅ ሙታኖቻቸውን ለመቅበር ረዳሁ። እናም እነሆ ሁለት መቶ ሰባ ዘጠኝ ወንድሞቻችን ስለተገደሉብን ሀዘናችንና ልቅሶአችን መሪር ነበር።