ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፯


ምዕራፍ ፳፯

ሞዛያ ስደትን ከለከለ፣ እናም እኩልነትን አዘዘ—ትንሹ አልማና አራቱ የሞዛያ ልጆች ቤተክርስቲያኗን ለማጥፋት ፈለጉ—መልአክ ታያቸው፣ እናም መጥፎ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ አዘዛቸው—አልማ በድንገት ዲዳ ሆነ—ሁሉም የሰው ዘር ደህንነትን እንዲያገኝ በድጋሚ መወለድ አለበት—አልማና የሞዛያ ልጆች የደስታ ምስራች አወጁ። ከ፻–፺፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ በቤተክርስቲያኗ እምነት በሌላቸው የተሰራጨው ስደት ታላቅ ሆኖ ቤተክርስቲያኗ ማጉረምረም ተጀመረ፣ እናም በቤተክርስቲያኗ ጉዳዩን በሚመለከት በከፍተኛ ሁኔታ ለመሪዎቻቸው አቤቱታ ማቅረብ ተጀመረ፤ አቤቱታቸውንም ለአልማ አቀረቡ። አልማም በንጉስ ሞዛያ ፊት ጉዳዩን አቀረበ። እናም ሞዛያ ከካህናቱ ጋር መከረበት።

እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ሞዛያ ማንም የማያምን የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን አባል የሆኑትን ማሳደድ እንደሌለበት በምድሪቱ ዙሪያ አዋጅን አሰራጨ።

እናም በቤተክርስቲያኗ ሁሉ መካከል ስደት መኖር እንደሌለበት፣ በሰዎች መካከል እኩልነት እንዲሆን ጥብቅ ትዕዛዝ ነበር፣

ምንም ኩራትና ብጥበጣ ሰላማቸውን ለማደፍረስ እንዲኖር አይፍቀዱ ዘንድ፤ ለራሳቸውም ድጋፍ በራሳቸው እጅ እየሰሩም፣ እያንዳንዱ ሰው ጎረቤቱን እንደራሱ ያክብሩ ዘንድ ጥብቅ ትዕዛዝ ነበር።

አዎን፣ እናም ካለህመም ወይም በድህነት ምክንያት በቀር፣ ሁሉም ካህናትና መምህራን ለራሳቸው በእጃቸው መስራት አለባቸው፤ እናም እነዚህን ነገሮች ሲያደርጉ ከመጠን ይልቅ በበለጠ በእግዚአብሔር ጸጋ ተሞሉ።

እናም እንደገና በምድሪቱ ታላቅ ሠላም መስፈን ጀመረ፤ ህዝቡም ብዙ መሆን ጀመሩ፤ እናም በምድር ገፅ ባሻገርም፣ አዎን በስተሰሜንና በደቡብም፣ በምስራቅና በምዕራብ፣ ታላላቅ ከተሞችንና መንደሮችን በሁሉም በምድሪቱ ክፍል በመገንባት መበተን ጀመሩ።

እናም ጌታ ጎበኛቸውና አበለፀጋቸው፣ እንዲሁም ታላቅና ሀብታም ህዝቦች ሆኑ።

አሁን የሞዛያ ልጆች ከማያምኑት ጋር የተቆጠሩ ነበሩ፤ እናም ደግሞ በአባቱ ስም አልማ ተብሎ የተጠራው ከአልማ ልጆችም አንዱ ከእነርሱ ጋር የተቆጠረ ነበር፤ ይሁን እንጂ፣ እርሱ እጅግ ኃጢአተኛና አመንዝራ ሰው ሆነ። እናም እርሱ በጣም ተናጋሪ ሰው ነበርና፣ ብዙ ሽንገላን ለህዝቡ ይናገር ነበር፤ ስለዚህም ብዙውን ህዝብ የእርሱን ክፋት እንዲከተሉ አደረገ።

እናም የህዝቡን ልብ በመስረቅ፣ በህዝቡ መካከል ብዙ ፀብ እንዲኖር በማድረግ፣ የእግዚአብሔር ጠላት ስልጣኑን በእነርሱ ላይ እንዲያሳይ እድል በመስጠት ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ዕድገት ታላቅ እንቅፋት ሆነ።

እናም አሁን እንዲህ ሆነ የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ለማጥፋት ወደተለያዩ ሥፍራዎች በሄደ ጊዜ፣ እናም ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ወይም ከንጉሱም እንኳን ተቃራኒ በሆነ መንገድ፣ የጌታን ህዝብ ወደተሳሳተው መንገድ ለመምራት ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ከሞዛያ ልጆች ጋር በሚስጥር ይሄድ ነበርና—

፲፩ እናም እንዳልኳችሁ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ እየሄዱ እያሉ፣ እነሆ፣ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ እናም በደመና ውስጥ እንደነበረ ወረደ፤ የቆሙበትንም ምድር እንዲንቀጠቀጥ በሚያደርግ ሁኔታ እንደነጎድጓድ ድምፅ ተናገረ፤

፲፪ እናም አድናቆታቸው እጅግ ታላቅ ሆኖ በመሬትም ላይ ወደቁ፣ እናም እርሱ የሚናገራቸውን ቃላት አልተረዱም ነበር።

፲፫ ይሁን እንጂ በድጋሚ እንዲህ ሲል ጮኸ፥ አልማ ተነስና፣ ቁም፣ የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ለምን ታሳድዳለህ? ጌታ እንዲህ ብሏልና፣ ይህች የእኔ ቤተክርስቲያን ናት፣ እናም አቋቁማታለሁ፤ ከህዝቤ መተላለፍ በስተቀር ምንም አይሽራትም።

፲፬ እናም በድጋሚ፣ መልአኩ አለ፥ እነሆ፣ ጌታ የዚህን ህዝብ ፀሎት፣ እናም ደግሞ የአባትህን የአልማን ፀሎት ሰምቷል። አንተ ወደ እውነት እውቀትም ትመጣ ዘንድ አንተን በተመለከተ በታላቅ እምነት ፀልዮአል፤ ስለዚህ፣ ለዚህ ዓላማ የእግዚአብሔርን ኃይልና ስልጣን ለማሳመን፣ በእምነታቸው መሰረት የአገልጋዮቹ ፀሎት መልስ ያገኝ ዘንድ ነው የመጣሁት።

፲፭ እናም አሁን እነሆ፣ የእግዚአብሔርን ኃይል መጠራጠር ትችላለህን? እነሆም ድምፄስ ምድርን አላንቀጠቀጠምን? እናም ከፊትህ ደግሞ እኔን ማየት አይቻልህምን? እኔም ከእግዚአብሔር ተልኬአለሁ።

፲፮ አሁን እንዲህ እልሃለሁ፥ ሂድ፣ እናም የአባቶችህን ምርኮ በሔላምና በኔፊ ምድር አስታውስ፣ እናም ለእነርሱ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገ አስታውስ፤ በባርነት ነበሩና እርሱ አድኖአቸዋልና። እናም አሁን አልማ እንዲህ እላለሁ፣ በመንገድህ ሂድ፣ ራስህን ለመጣል ብትፈልግም፣ ቤተክርስቲያኗን ለማጥፋት አትፈልግ፣ ምክንያቱም ፀሎታቸው ምላሽ ያገኛልና።

፲፯ እናም አሁን እንዲህ ሆነ እነዚህ መልአኩ ለአልማ የተናገረው የመጨረሻ ቃላት ነበሩ፣ እናም ሄደ።

፲፰ እናም አሁን አልማና ከእርሱ ጋር የነበሩት በምድር ላይ ወደቁ፣ መደነቃቸው ታላቅ ነበርና፤ በራሳቸው ዐይንም የጌታን መልአክ ተመልክተዋልና፤ እናም ድምፁ ምድርን እንደሚያንቀጠቅጥ ነጎድጓድ ነበር፣ እናም ከእግዚአብሔር ኃይል በቀር ምንም መሬትን እንደሚከፍል አይነት ምድርን ለማንቀጥቀጥ የሚችል እንደሌለ አወቁ።

፲፱ እናም አሁን የአልማ መደነቅ ታላቅ ስለነበር ዲዳ ሆነ፣ አፉንም መክፈት አልቻለም፤ አዎን፣ እና ደካማ ሆነ፣ እጁን እንኳ ማንቀሳቀስ እስኪያቅተው፤ ስለዚህ ከእርሱ ጋር በነበሩት ተወሰደና፣ በአባቱ ፊት እስከሚወድቅ ድረስ እራሱን መርዳት አቅቶት ተሸከሙት።

እናም ለአባቱ በእነርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ገለፁለት፣ እናም አባቱ የእግዚአብሔር ኃይል መሆኑን በማወቁ ተደሰተ።

፳፩ እናም ጌታ ለልጁና ደግሞ ከእርሱ ጋር ለነበሩት ያደረገውን ይመሰክሩ ዘንድ ብዙዎች በአንድነት እንዲሰበሰቡ አደረገ።

፳፪ እናም ካህናት እራሳቸውን በአንድነት እንዲሰበስቡ አደረገ፤ እናም የእግዚአብሔርን ክብርና ቸርነት ያውቁና፣ ይመለከቱ ዘንድ የህዝቡም ዐይን እንዲከፈት፣ ጌታ የአልማን አንደበት ይናገርበትም ዘንድ እንዲከፍት፤ እናም ደግሞ እጅና እግሮቹ ብርታትን ያገኙ ዘንድ ወደአምላካቸው መፀለይና መፆም ጀመሩ።

፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ለሁለት ቀናትና ሁለት ሌሊት ከፆሙና ከፀለዩ በኋላ የአልማ እግሮችና እጆች ብርታትን አገኙ፣ እናም ተነስቶ መናገር ጀመረ፣ መልካም መፅናናት እንዲሆንላቸውም ተናገረ።

፳፬ እንዲህ አለ፥ ለኃጢአቴ ንስሃ ገብቻለሁ፣ እናም በጌታ ድኜአለሁ፤ እነሆም ከመንፈስ ተወልጃለሁ።

፳፭ እናም ጌታ አለኝ፥ ሁሉም የሰው ዘር፣ አዎን፣ ወንዶችና ሴቶች፣ ሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብ በድጋሚ መወለድ ይገባቸዋልና አትደነቅ፤ አዎን ከእግዚአብሔር በመወለድ፣ ከስጋዊና ከወደቁበት ሁኔታ፣ ወደ ፃድቁ መንገድ በእግዚአብሔር በመዳን፣ የእርሱም ወንድና ሴት ልጆች በመሆን ይለወጣሉ

፳፮ እናም በዚህም አዲስ ፍጡራን ይሆናሉ፣ ይህንን ካላደረጉ፣ በምንም መንገድ የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉምና።

፳፯ እላችኋለሁ፣ ጉዳዩ ይህ ካልሆነ፣ መጣል አለባቸው፤ እናም ይህንን አውቃለሁ ምክንያቱም እኔ ልጣል ነበርና።

፳፰ ይሁን እንጂ፣ በብዙ መከራ ላይ ከተገፋሁ በኋላ ልሞት ስል፣ ንስሃ ገባሁ፣ ጌታም በምህረቱ ከዘለዓለማዊ ቃጠሎ እንድወጣ አደረገኝ፣ እናም እኔ ከአምላክ ተወለድኩ።

፳፱ ነፍሴ ከሞላው መራራ መርዝ፣ እና ከክፋት ሰንሰለት ተፈወሰች። እኔም በጨለማ አዘቅት ነበርኩ፤ ነገር ግን አሁን አስደናቂውን የአምላክ ብርሃን ተመለከትኩ። ነፍሴ በዘለአለማዊ ቅጣት ተሰቃየች፤ ነገር ግን እኔ ተነጥቄአለሁ፣ እናም ከእንግዲህ ነፍሴ ህመም የለባትም።

አዳኜን አልተቀበልኩትም፣ እናም በአባቶቻችን የተነገረውን ክጄአለሁ፤ ነገር ግን አሁን እንደሚመጣ፣ እናም ጌታ የፈጠረውን ማንኛውንም ፍጡር እንደሚያስታውስ አስቀድመው እንዲመለከቱ፣ እርሱም እራሱን ለሁሉም ይገልፃል።

፴፩ አዎን፣ ሁሉም ጉልበት ይንበረከካል፣ እናም የሁሉም አንደበት በፊቱ ይናዘዛል። አዎን፣ እንዲሁም በመጨረሻው ቀንም ሁሉም ሰው በእርሱ ለፍርድ በሚቆሙበት ጊዜ፣ ከዚያም እርሱ አምላክ መሆኑን ይናዘዛሉ፤ በዓለም ላይ ያለ እግዚአብሔር የሚኖሩትም የዘለአለማዊው ቅጣት በእነርሱ ላይ ትክክል መሆኑን ይናዘዛሉም፤ ይንዘፈዘፋሉም፣ ይንቀጠቀጣሉም፣ እናም ሁሉም በቅጽበት በሚያዩት ዐይኖች ፊት ይሸማቀቃሉ።

፴፪ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ህዝቡን ማስተማር ጀመረ፣ እናም መልአኩ በተገለፀላቸው በዚያን ጊዜ ከአልማ ጋር የነበሩት ስላዩትና ስለሰሙት ነገሮችም ለሁሉም ህዝብ በማወጅ፣ እናም በከፍተኛ መከራ፣ እምነት በሌላቸውም ታላቅ ስደትን እየተቀበሉ፣ በብዙዎችም እየተመቱ በምድሪቱ ዙሪያ ሁሉ እየተጓዙ የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ።

፴፫ ነገር ግን ይህ ሁሉ ቢሆንም፣ እምነታቸውን በማረጋገጥ፣ እናም የጌታን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ በትእግስት እና በብዙ ስቃይ በጥብቅ በማበረታታት ለቤተክርስቲያኑ ብዙ ማፅናኛ ሰጡ።

፴፬ እናም አራቱም የሞዛያ ልጆች ነበሩ፣ ስማቸውም አሞን፣ አሮን፣ ኦምነር፣ እናም ሒምኒ ነበሩ፣ እነዚህ የሞዛያ ወንድ ልጆች ስሞች ነበሩ።

፴፭ እናም በቤተክርስቲያኑ ላይ የፈፀሙትን በደል ሁሉ በቀናነት ለማደስ በቅንነት በመሞከር፣ ኃጢአታቸውን ሁሉ ለመናዘዝና፣ ያዩትን ነገሮች ሁሉ በማወጅ፣ እናም ትንቢትንና ቅዱሳን መፃህፍትን መስማት ለፈለጉ ሁሉ በመግለጽ፤ በዛራሔምላ ምድር ሁሉ፣ እናም በንጉስ ሞዛያ አገዛዝ ስር ከነበሩት ሰዎች መካከል ተጓዙ።

፴፮ እናም ብዙዎችን እውነትን እንዲያውቁ፣ አዎን ወደ አዳኛቸው እውቀት ለማምጣት እንደዚህም በጌታ እጅ መሳሪያ ነበሩ።

፴፯ እናም እነርሱ እንዴት የተባረኩ ናቸው! ሰላምን አውጀዋልና፤ መልካም የሆነውን የምስራች ዜና አውጀዋል፤ እናም ለህዝቡም ጌታ እንደሚነግስ አውጀዋል።