ምዕራፍ ፳፰
የሞዛያ ልጆች ላማናውያንን ሊሰብኩ ሔዱ—ሁለቱን የባለራዕይ ድንጋዮች በመጠቀም ሞዛያ የያሬዳውያንን ሰሌዳዎች ተረጎመ። በ፺፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እንግዲህ እንዲህ ሆነ የሞዛያ ልጆች እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካደረጉ በኋላ ጥቂቶቹን ከእነርሱ ጋር ወሰዱ፣ እናም ወደ ንጉሱ አባታቸው ተመለሱ፤ እናም በዚህም እነርሱ ከመረጧቸው ጋር በመሆን፣ የሰሙአቸውን ነገሮች ይሰብኩ ዘንድ እናም የጌታን ቃላት ለወንድሞቻቸው ለላማናውያን ያካፍሉ ዘንድ ወደኔፊ ምድር እንዲሄዱ እንዲፈቅድላቸው ፈለጉ—
፪ ምናልባት ወደጌታ አምላካቸው እውቀት ያመጧቸው ዘንድ፣ እናም የአባቶቻቸውንም ክፋት እንዲያሳምኑአቸው፤ እናም ምናልባት ወደኔፋውያን ካላቸው ጥላቻ ያድኗቸው ዘንድ፣ በጌታ በአምላካቸውም ደግሞ ወደመደሰት ያመጧቸው ዘንድ፣ እርስ በራስም ወዳጅ ይሆን ዘንድ፣ እናም ጌታ አምላካቸውም በሰጣቸው ምድር ሁሉ ከእንግዲህ ጠብም እንዳይኖር ለማድረግ ይችሉ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ፈለጉ።
፫ አሁን ደህንነት ለሁሉም ፍጡር መታወጅ እንደሚገባው ፍላጎት ነበራቸው፣ የማንም የሰው ነፍስ መጥፋቱን ሊቀበሉት አልቻሉምና፤ አዎን ማንኛውም ነፍስ መጨረሻ የሌለውን ቅጣት የሚቀበል መሆኑ ማሰባቸውም እንዲንዘፈዘፉና እንዲንቀጠቀጡ ያደርጋቸዋል።
፬ እናም የጌታ መንፈስ በእነርሱ ላይ ሰርቶ ነበር፣ እነርሱ ከሁሉም በላይ መጥፎ የሆኑ ኃጢአተኞች ነበሩና። እናም ጌታ ማብቂያ በሌለው ምህረቱ እነርሱን ለማዳን አስፈላጊ መሆኑን ተረዳ፤ ይሁን እንጂ በክፋታቸው ምክንያት ብዙ የነፍስ ስቃይ ተሰቃዩ፣ እናም ለዘለዓለም እንጣላለን ብለው በመፍራታቸው የተነሳ ብዙ ተሰቃዩ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ኔፊ ምድር ይወጡ ዘንድ ከአባቶቻቸው ጋር ለብዙ ቀናት ተማፀኑ።
፮ እናም ንጉስ ሞዛያ ሄደና፣ ልጆቹ ከላማናውያን መካከል ሄደው ወንጌልን ለማስተማር ፍቃድ እንዲሰጣቸው እንደሚገባው ጌታን ጠየቀ።
፯ እናም ጌታ ለሞዛያ እንዲህ አለው፥ እንዲሄዱ ፍቀድላቸው፣ ብዙዎች በቃላቸው ያምናሉና፣ እናም ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖራቸዋል፤ እናም እኔ ወንድ ልጆቻችሁን ከላማናውያን እጅ አድናቸዋለሁ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ ሞዛያ በጠየቁትም መሰረትም እንዲሄዱና ያደርጉ ዘንድ ፈቀደላቸው።
፱ እናም በላማናውያን መካከል ቃሉን ለመስበክ ወደ ምድረበዳ ሄዱ፣ እናም ከዚህ በኋላ የታሪካቸውን ዘገባ እሰጣለሁ።
፲ አሁን ንጉስ ሞዛያ መንግስቱን የሚሰጥበት ማንም አልነበረውም፣ ምክንያቱም ከልጆቹም ማንም መንግስቱን የተቀበለ አልነበረም።
፲፩ ስለዚህ እናም ለንጉስ ሞዛያ በሊምሂ እጅ የተሰጡትን በሊምሂ ህዝብ የተገኙትን ወርቃማ ሠሌዳዎች ከተረጎመና በመዝገብ እንዲፃፍ ካደረገ በኋላ፣ በነሃስ ሰሌዳና፣ ደግሞም በኔፊ ሠሌዳዎች ላይ የተቀረፁትንና፣ ሁሉንም በእግዚአብሔር ትዕዛዝ መሰረት የተቀመጡትን እና የተጠበቁትን ነገሮች ወሰደ፤
፲፪ እናም ይህን ያደረገው በህዝቡ ታላቅ ጉጉት የተነሳ ነው፣ ምክንያቱም እነርሱ ስለጠፉት ሰዎች ለማወቅ ፍላጎታቸው ከልክ በላይ ነበርና።
፲፫ እናም አሁን በሁለቱ የቀስት ጫፎች ላይ በታሰሩት ድንጋዮች አማካኝነት ተረጎማቸው።
፲፬ አሁን እነዚህ ነገሮች ከመጀመሪያው ጀምሮ ተዘጋጅተዋል፣ እናም ቋንቋዎችን ለመተርጎም አላማም ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈዋል፤
፲፭ እናም የምድሪቱን ሰዎች ክፋትና እርኩሰት ማንኛውም ፍጡር ያገኘው ዘንድ፣ በጌታ እጅ ተጠብቀዋል፣ እናም ተቀምጠዋል፤
፲፮ እናም እነዚህን ነገሮች ያሏቸው ሁሉ እንደጥንት ጊዜ አይነት ባለራዕይ ይባላሉ።
፲፯ አሁን ሞዛያ እነዚህን ታሪኮች ተርጉሞ ከጨረሰ በኋላ፣ እነሆ፣ የጠፉትን ህዝቦች ከጠፉበት ጊዜ አንስቶ ታላቁ ግንብ እስከተገነባበት፣ ጌታ የህዝቡን ቋንቋ በቀለቀለበት ጊዜ እናም በምድር ገፅ ሁሉ እስከተበተኑበት፤ አዎን፣ እናም ከጥንት አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ጭምር የህዝቡን ታሪክ ሰጠ።
፲፰ አሁን ይህ ታሪክ የሞዛያ ህዝብ እጅግ እንዲያለቅስ አደረገ፤ አዎን በሀዘን ተሞልተው ነበር፣ ይሁን እንጂ ብዙ እውቀትን ሰጥቷቸዋል፣ በእርሱም ተደስተዋል።
፲፱ እናም ይህ ታሪክ ከዚህ በኋላ ይፃፋል፣ እነሆም፣ በዚህ መዝገብ የተፃፉትን ነገሮች ሁሉም ሰው ማወቁ አስፈላጊ ነውና።
፳ እናም አሁን፣ እኔ እንዳልኳችሁ፣ ንጉስ ሞዛያ እነዚህን ነገሮች ካደረገ በኋላ የነሃስ ሰሌዳዎቹን፣ እናም ያስቀመጣቸውን ሁሉንም ነገሮች ወሰደና፣ የአልማ ልጅ ለሆነው ለአልማ ሰጠው፤ አዎን፣ ሁሉንም መዛግብትና፣ ደግሞ መተርጎሚያውን፣ እናም ሁሉንም ለእርሱ ሰጠ፣ እንዲጠብቃቸውና እንዲያስቀምጣቸው፣ ደግሞም የህዝቡን ታሪክ እንዲያስቀምጥ፣ ልክ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ እንደተላለፈው፣ ከአንዱ ትውልድ ወደሌላኛው እንዲያስተላልፍ አዘዘው።