መፅሐፈ ሞዛያ
ምዕራፍ ፩
ንጉስ ቢንያም ለልጆቹ የአባቶቻቸውን ቋንቋ እና ትንቢት አስተማረ—ኃይማኖታቸውና ስልጣኔያቸው የተጠበቁት በተለያዩ ሠሌዳዎች ላይ በተጠበቁት መዝገቦች ምክንያት ነው—ሞዛያ ለንጉስነት ተመርጧል እናም መዛግብቱና ሌሎችም ነገሮች አደራ ተሰጥተውታል። ከ፻፴–፻፳፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን የንጉሥ ቢንያም ከሆኑት ህዝቦች ሁሉ መካከል በዛራሔምላ ምድር ሁሉ ከዚያ በኋላ ፀብ አልነበረም፣ ስለዚህ ንጉሥ ቢንያም በቀሪው ዘመኑ ሁሉ ዘላቂ ሠላም ነበረው።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እናም ስማቸውን ሞዛያና፣ ሔሎሩምና፣ ሔለማን ብሎ ጠራቸው። እናም አስተዋይ ሰዎች ይሆኑ ዘንድና፣ በጌታ እጅ የተሰጣቸውን በአባቶቻቸው አንደበት ስለተነገሩት ትንቢቶች ያውቁ ዘንድ በአባቶቻቸው ቋንቋ ሁሉ እንዲማሩ አደረገ።
፫ እናም ደግሞ በነሀስ ሠሌዳዎች ላይ የተቀረፀውን ታሪክ በተመለከተ እንዲህ ሲል አስተማራቸው፥ እነዚህን ታሪኮችና ትዕዛዛት የያዙት እነዚህ ሠሌዳዎች ባይኖሩ ኖሮ በአሁኑም ጊዜ እንኳን ቢሆን የእግዚአብሔርን ሚስጥር ባለማወቅ በድንቁርና እንደምንሰቃይ ልጆቼ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ።
፬ በእነዚህ ሠሌዳዎች እርዳታ ካልሆነ በቀር አባታችን ሌሂ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ለልጆቹ በማስታወስ ለማስተማር አይቻለውም ነበር፤ ምክንያቱም የግብፃውያንን ቋንቋ የተማረ ስለሆነ እነዚህን ፅሁፎች ለማንበብ ይቻለዋል፣ እናም ልጆቹ ልጆቻቸውን ማስተማር ይችሉ ዘንድ ይህንኑ ልጆቹን አስተማራቸው፣ እናም ስለዚህ እስከዚህ ጊዜም ድረስ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ይፈፅማሉ።
፭ ልጆቼ እንዲህ እላችኋለሁ፥ እኛ የእርሱን ሚስጥር አንብበን እንገነዘብ ዘንድ በእግዚአብሔር እጅ የተቀመጡትና የተጠበቁት እነዚህ ነገሮች፣ እንዲሁም ሁልጊዜም ከዐይናችን ስር ያሉት ትዕዛዛቱ ባይኖሩ ኖሮ አባቶቻችንም እንኳን ቢሆኑ እምነት አጥተው ይመነምኑ ነበር፣ እናም ስለእነዚህ ነገሮች ምንም እንደማያውቁት፣ ወይም በሚያስተምሩአቸው ጊዜም ስህተት በሆነው በአባቶቻቸው ወግ ምክንያት እንደማያምኑት ወንድሞቻችን እንደላማናውያን እንሆን ነበር።
፮ ልጆቼ ሆይ፣ እነዚህ አባባሎች እውነት መሆናቸውን፣ እናም ደግሞ እነዚህ መዛግብት እውነት እንደሆኑ እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ። እናም ኢየሩሳሌምን ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን የአባቶቻችንን አባባሎች መዛግብትን የያዙ የኔፊ ሰሌዳዎችን ደግሞ ተመልከቱ፣ እነርሱም እውነተኛ ናቸው፤ እናም እኛ የእነርሱን እርግጠኝነት እናውቃለን ምክንያቱም እነርሱ በዐይኖቻችን ፊት ቀርበዋል።
፯ እናም አሁን፣ ልጆቼ፣ እናንተ ትጠቀሙ ዘንድ እነርሱን በትጋት መፈተሽን አንድታስታውሱ እፈልጋለሁ፤ እናም ጌታ ለአባቶቻችን በገባው ቃል ኪዳን መሰረት በምድሪቱ ትበለፅጉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንድትጠብቁ እፈልጋለሁ።
፰ እናም በዚህ መፅሐፍ ያልተፃፉትን በጣም ብዙ ተጨማሪ ነገሮችን ንጉስ ቢንያም ለልጆቹ አስተማረ።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ቢንያም ልጆቹን ማስተማር ከጨረሰ በኋላ አረጀ፣ እናም በቅርቡ ምድር ሁሉ ወደሚሄዱበት መሄድ እንዳለበት ተመለከተ፤ ስለዚህ መንግስቱን ከልጆቹ ለአንደኛው ልጁ መስጠት ተገቢ መሆኑን አሰበ።
፲ ስለዚህ፣ ሞዛያን በፊቱ እንዲመጣ አደረገ፤ እናም እነዚህ ለእርሱ የተናገራቸው ቃላት ናቸው፥ ልጄ በዚህ ምድር ሁሉ በዚህ ህዝብ ሁሉ ወይም በዛራሔምላ ህዝብ እናም በምድሪቱ በሚኖሩት በሞዛያ ህዝብ መካከል በአንድ ላይ ይሰበሰቡ ዘንድ አዋጅን እንድታውጅ እፈልጋለሁ፤ በማግስቱም ጌታ እግዚአብሔር ለእኛ በሰጠን በዚህ ህዝብ ላይ አንተ ንጉስና ገዢ መሆንህን በራሴ አንደበት ለህዝቤ አስታውቃለሁ።
፲፩ እናም ከዚህ በተጨማሪ፣ ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ምድር ካወጣቸው ህዝቦች መካከል ይለዩ ዘንድ ለዚህ ህዝብ ስም እሰጣለሁ፤ እናም ይህንን የማደርገው እነርሱ የጌታን ትዕዛዛት በመጠበቅ ትጉህ ስለነበሩ ነው።
፲፪ እናም በመተላለፍ ካልሆነ በቀር ሊደመሰስ የማይችል ስም እሰጣቸዋለሁ።
፲፫ አዎን፣ እናም በተጨማሪ እልሀለሁ፥ እነዚህ እጅግ በጌታ የተወደዱ ሰዎች ወደ መተላለፍ ቢወድቁ፣ እናም ኃጢአተኞችና፣ ዝሙትን አድራጊዎች ቢሆኑ፤ ጌታ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፣ በዚህም እንደ ወንድሞቻቸውም ደካሞች ይሆናሉ፤ እናም ከዚህ ቀደም አባቶቻችንን እንዳዳናቸው ወደር በሌለውና ድንቅ ሃይሉ ከእንግዲህ አያድናቸውም።
፲፬ እንዲህም እልሀለሁ፣ ለአባቶቻችን ባደረገው ጥበቃ እጁን ባይዘረጋ ኖሮ እነርሱ በላማናውያን እጅ በወደቁ እናም በጥላቻቸው ተጎጂ በሆኑ ነበር።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ቢንያም ለልጁ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ፣ የንግስታቱን አገዛዝ የተመለከቱ ጉዳዮችን ሁሉ በኃላፊነት ሰጠው።
፲፮ እናም በተጨማሪ፣ ደግሞ በነሀስ ሰሌዳዎች ላይ የተፃፉትን ታሪኮች በተመለከተ፣ እናም ደግሞ የኔፊን ስሌዳዎች በተመለከተና፣ ደግሞ የላባንን ሳንጃ፣ እንዲሁም እያንዳንዳቸው ለእርሱ በሚሰጡት ትኩረትና ትጋት መሰረት ይመሩበት ዘንድ በጌታ እጅ የተዘጋጀውን አባቶቻቸውን ከምድረበዳ የመራውን ኳሱን ወይም መሪውን ኃላፊነት ሰጠው።
፲፯ ስለዚህ፣ እምነት ባጡበት ጊዜ በጉዞአቸው አልበለፀጉም ወይም እድገትንም አላገኙም ነበር፣ ነገር ግን ወደኋላ ተወስደው ነበር፣ እናም የእግዚአብሔርን መከፋት በእነርሱ ላይ አመጣባቸው፤ እናም ስለዚህ ሀላፊነታቸውን እንዲያስታውሱ ለማነሳሳት በረሃብና በቁስል መቅሰፍት ተመተው ነበር።
፲፰ እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ ሞዛያ ሔደና፣ አባቱ እንዳዘዘው አደረገ፤ እናም በዛራሔምላ ምድር ላሉት ህዝቦች ሁሉ ወደ ቤተ መቅደሱ በመሄድ አባቱ የሚናገረውን ቃላት እንዲያደምጡ በአንድ ላይ ይሰበሰቡ ዘንድ አወጀላቸው።