ምዕራፍ ፯
አሞን ሊምሂ ንጉሥ የሆነበትን፣ የሌሂ-ኔፊ ምድርን አገኘ—የሊምሂ ህዝብ በላማናውያን ባርነት ስር ናቸው—ሊምሂ ታሪካቸውን ዘገበ—ነቢዩ (አቢናዲ) ክርስቶስ የሁሉም ነገሮች አምላክና አባት መሆኑን መስክሯል—መጥፎ የዘሩ አውሎ ነፋስን ያጭዳሉ፣ እናም በጌታ እምነታቸውን ያደረጉ ይድናሉ። ፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ ንጉሥ ሞዛያ ለሦስት ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ ሠላምን ካገኘ በኋላ፣ በሌሂ-ኔፊ ምድር እንዲሁም በሌሂ-ኔፊ ከተማ ለመኖር የሄዱትን ሕዝቦች በተመለከተ ለማወቅ ፈለገ፤ ምክንያቱም ህዝቡ የዛራሄምላን ምድር ለቀው ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ምንም አልሰሙም ነበረ፤ ስለዚህ፣ በጥያቄያቸው ረበሹት።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ሌሂ-ኔፊ ምድር ወንድሞቻቸውን በተመለከተ ይጠይቁ ዘንድ ንጉሥ ቢንያም ከጠንካሮቹ አስራ ስድስቱ እንዲሄዱ አደረገ።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በማግስቱ የዛራሔምላ ትውልድ የሆነውንና ጠንካራና ኃይለኛ የሆነውን ሰው አሞንን ይዘው መሄድ ጀመሩ፤ እናም ደግሞ እርሱ መሪያቸው ነበር።
፬ እናም አሁን፣ ወደ ሌሂ-ኔፊ ምድር ለመሄድ በምድረበዳ ውስጥ መጓዝ ያለባቸውን መንገድ አላወቁትም፤ ስለዚህ፣ በምድረበዳ ውስጥ ለብዙ ቀናት ዞሩ፣ እንዲህም ለአርባ ቀናት ዞሩ።
፭ እናም አርባ ቀን ከዞሩ በኋላ ከሺሎም ምድር በስተሰሜን ወደነበረ አንድ ኮረብታ መጡና በዚያም ቦታ ድንኳናቸውን ተከሉ።
፮ እናም አሞን ሶስቱን ወንድሞቹን ወሰደ፣ እናም ስማቸውም አማሌቂ፣ ሔለምና፣ ሔም ነበር፣ እናም ወደ ኔፊ ምድር ወረዱ።
፯ እናም እነሆ፣ በኔፊ ምድርና፣ በሺሎም ምድር የነበሩትን ሰዎች ንጉሥ ተገናኙት፤ እናም እነርሱ በንጉሡ ጠባቂዎች ተከበቡና፣ ተወሰዱ፣ እንዲሁም ተያዙና ወደ ወህኒ ተጣሉ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ ለሁለት ቀናት በወህኒ በነበሩበት ጊዜ እንደገና በንጉሡ ፊት ቀርበው ነበር፣ እናም እስራታቸውም ተፈትቶላቸው ነበር፤ እናም በንጉሱ ፊት ቆሙና፣ እርሱ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች እንዲመልሱ ተፈቀደላቸው ወይም ታዘዙ።
፱ እናም እንዲህ አላቸው፥ እነሆ እኔ፣ ከዛራሔምላ ምድር የአባታቸው ምድር የነበረውን ይህንን ምድር ለመውረስ የመጣው፣ በህዝብ ድምፅ ንጉሥ የተደረገው የዜኒፍ ልጅ፣ የኖህ ልጅ ሊምሂ ነኝ።
፲ እናም አሁን፣ እኔ ከራሴ ጠባቂዎች ጋር ከግቢው ውጭ በነበርኩበት ጊዜ ወደ ከተማው ክልል ለመምጣት የደፈራችሁበትን ምክንያት ለማወቅ እፈልጋለሁ?
፲፩ እናም አሁን፣ እናንተ እንድትጠበቁ ያደረኩበት ምክንያት እናንተን እጠይቅ ዘንድ ነው፣ አለበለዚያ ጠባቂዎቼ እንዲገድሉአችሁ አደርግ ነበር። እናንተም እንድትናገሩ ተፈቅዶላችኋል።
፲፪ እናም አሁን፣ አሞን ለመናገር እንደተፈቀደለት በተመለከተ ጊዜ፣ ሄደና በንጉሱ ፊት ሰገደ፤ እናም እንደገና ተነስቶ እንዲህ አለ፥ ንጉስ ሆይ፣ በዛሬ ቀን በህይወት በመኖሬና ለመናገር ስለተፈቀደልኝ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ አመሰግናለሁ፤ እናም በድፍረት ለመናገር እሞክራለሁ፤
፲፫ እኔን ብታውቀኝ ኖሮ ይህንን ማሰሪያ እንዳጠልቅ እንደማትፈቅድ እርግጠኛ ነበርኩ። እኔ አሞን ነኝ፣ እናም የዛራሔምላ ዘር ነኝ፣ እናም ዜኒፍ ከምድሪቱ ስላወጣቸው ስለወንድሞቻችን ለመጠየቅ ከዛራሔምላ ምድር መጥቻለሁ።
፲፬ እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ ሊምሂ የአሞንን ቃላት ከሰማ በኋላ እጅግ ተደሰተ፣ እናም እንዲህ አለ፥ አሁን፣ በዛራሔምላ ምድር የነበሩት ወንድሞቼ እስከአሁን በህይወት እንደሚኖሩ አውቃለሁ። እናም አሁን እደሰታለሁ፤ በማግስቱም ህዝቦቼ ደግሞ እንዲደሰቱ አደርጋለሁ።
፲፭ እነሆም፣ እኛ በላማናውያን ባርነት ስር ነን፣ እናም ልንሸከመው በማይቻል በታላቅ ቀረጥ እንቀረጣለን። እናም አሁን እነሆ፣ ወንድሞቻችን ከባርነት ወይም ከላማናውያን እጅ ያስለቅቁናል፣ እናም እኛ የእነርሱ ባሮች እንሆናለን፤ ለላማናውያን ግብር ከመክፈል ለኔፋውያን ባርያ መሆን ይሻላልና።
፲፮ እናም አሁን፣ ንጉስ ሊምሂ ለጠባቂዎቹ አሞንንም ሆነ ወንድሞቹን ከእንግዲህ እንዳያስሩአቸው አዘዘ፣ ነገር ግን በሼምሎን በስተሰሜን ወዳለው ኮረብታ እንዲሄዱና ወንድሞቻቸውን ወደ ከተማይቱ እንዲያመጡና በዛም ይመገቡና፣ ይጠጡ፣ እንዲሁም ከጉዞአቸውም ድካም እንዲያርፉ አደረገ፣ ምክንያቱም በብዙ ነገሮች ተሰቃይተዋል፣ በረሃብ በጥማትና በድካምም ተሰቃይተዋልና።
፲፯ እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ በማግስቱ ንጉሱ ሊምሂ በቤተመቅደስ በአንድነት እራሳቸውን ሰብስበው የሚያነጋግራቸውን ያደምጡ ዘንድ በህዝቡ ሁሉ መካከል አዋጅን ላከ።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ እራሳቸውን በአንድ ላይ በሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ በማለት ተናገራቸው፥ ህዝቤ ሆይ፣ ራሳችሁን አቅኑና ተፅናኑ፤ እነሆም ምንም እንኳን ከንቱ ከነበሩት ብዙ ትግሎቻችን ብንታገልም፣ በጠላቶቻችን ስር ከእንግዲህ የማንሆንበት ጊዜ መጥቷል፣ እና ሩቅ አይደለም፤ ነገር ግን የሚቀረው ትግላችን ወደፈለግነው ውጤት እንደሚያደርሰን አምናለሁ።
፲፱ ስለዚህ፣ ራሳችሁን አቅኑና፣ ተደሰቱ፣ እንዲሁም እምነታችሁን የአብርሃምና የይስሀቅ፣ እናም የያዕቆብ አምላክ በሆነው፣ ደግሞም፣ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ባወጣው አምላክና፣ በደረቅ ምድር በቀይ ባህር ውስጥ እንዲጓዙ ባደረገው፣ እናም በምድረበዳው ውስጥ እንዳይጠፉ መናን ከዚህ የበለጡ ብዙ ነገሮችን ባደረገላቸው በዚያ እግዚአብሔር እምነታችሁን አድርጉ።
፳ እናም እንደገና፣ ይኸው አምላክ አባቶቻችንን ከኢየሩሳሌም ምድር አውጥቷቸዋል፣ እናም እስከአሁን ድረስ ህዝቡን ጠብቋል እንዲሁም አስቀምጧል፤ እናም እነሆ፣ በኃጢአታችንና በእርኩሰታችንም የተነሳ ወደባርነት ወስዶናል።
፳፩ እናም በዚህ ቀን ሁላችሁም ምስክሮች ናችሁ፣ ዜኒፍ በዚህ ህዝብ ላይ ንጉስ የተደረገው፣ የአባቶቹን ምድር ለመውረስ ጓጉቷልና፤ ስለዚህ በብልጥነትና በተንኮል በማታለል ከንጉስ ዜኒፍ ጋር ስምምነት የገባው ንጉስ ላማን የምድሪቷን ክፍል፣ ወይም እንዲሁም የሌሂ-ኔፊ ከተማንና፣ የሼምሎንን ከተማ፤ እንዲሁም በዙሪያዋ ያለውን ምድር ንብረት ወደ እጆቹ አሳልፎ ሰጠ—
፳፪ እናም ይህንን ሁሉ እርሱ ያደረገው፣ ይህን ህዝብ በቁጥጥሩ ስር ወይም በባርነት ስር ለማዋል ባለው ብቸኛ ዓላማ ነበር። እናም እነሆ፣ እኛ በዚህ ጊዜ፣ መጠኑም ከበቆሎአችንና ከገብሳችን እንዲሁም ከሁሉም አይነት ጥራጥሬዎቻችን ግማሹንና፣ ከከብት መንጋዎቻችን አንድ ሁለተኛውን በግብር ለላማናውያን ንጉስ እንከፍላለን፤ እና እንዲሁም ካሉን ንብረቶቻችንም አንድ ሁለተኛ እንኳን ወይም ህይወታችንን የላማናውያንን ንጉስ ይወስድብናል።
፳፫ እናም አሁን፣ ይህ ለመቋቋም አስቸጋሪ አይደለምን? እናም ይህስ ስቃያችን ታላቅ አይደለምን? አሁን እነሆ ለማዘንስ ምን ያህል ታላቅ ምክንያት ይኖረናል።
፳፬ አዎን፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ለሀዘናችን ምክንያቶቻችን ታላቅ ናቸው፤ እነሆም የተገደሉ እንዲሁም ደማቸው በከንቱ የፈሰሰው ወንድሞቻችን ምን ያህል ናቸው፣ እና ያም ሁሉ በክፋት ምክንያት።
፳፭ እነዚህ ሰዎች ወደመተላለፍ ባይወድቁ ኖሮ ጌታ ይህ ታላቅ ክፋት በእነርሱ ላይ እንዲሆን አይፈቅድም ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ እነርሱ ቃሉን አያደምጡም፣ ነገር ግን በመካከላቸውም ብዙ ደም መፋሰስ እስከሚሆን ድረስ፣ በመካከላቸው ጠብ ተነሳ።
፳፮ እናም አዎን በእግዚአብሔር የተመረጠውን ኃጢአታቸውን እናም እርኩሰታቸውን የነገራቸውንና ብዙ የሚመጡ ነገሮችን፣ አዎን፣ የክርስቶስንም መምጣት ቢሆን የተነበየውን የጌታን ነቢይ ገድለዋል።
፳፯ እናም እርሱ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን የሁሉም ነገር አባት መሆኑን በመናገሩም፣ የሰውንም መልክ በራሱ መውሰዱንና፣ ይህም ሰው ከመጀመሪያው ጀምሮ የተፈጠረበት አምሳል መሆኑን፤ ወይም በሌላ አነጋገር ሰው በአምላክ አምሳያ ተፈጥሯል፣ አምላክም በሰው ልጆች መካከል ይመጣል፣ እናም በራሱ ላይ ስጋና ደም ይለብሳል፣ እናም በምድር ገፅ ላይ ይሄዳል ስላለ—
፳፰ እናም አሁን፣ ይህንን በማለቱ፣ ገደሉት፤ እናም በራሳቸው ላይ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚያስከትሉ ከዚህ የበለጡ ብዙ ነገሮችን አደረጉ። ስለዚህ በታላቅ ስቃይ በመመታታቸውና፣ እነርሱ በመታሰራቸው ማን ይደነቃል?
፳፱ እነሆም፣ ጌታ እንዲህ ይላል፣ በመተላለፋቸው ቀን ህዝቤን አልረዳም፣ ነገር ግን እንዳይበለፅጉ መንገዱን እከላከላለሁ፤ እናም ስራቸው በፊታቸው የመሰናከያ አለት ይሆንባቸዋል።
፴ እናም እንደገና፣ እርሱ እንዲህ ይላል፥ ህዝቤ ቆሻሻን ከዘሩ በአውሎ ነፋስ ገለባን ይሰበስባሉ፤ እናም ውጤቱ መርዝ ነው።
፴፩ እናም እንደገና እርሱ እንዲህ ይላል፥ ህዝቤ ቆሻሻውን ከዘሩ ፈጣን የሆነ ጥፋት የሚያመጣውን የምስራቁን ንፋስ ያጭዳሉ።
፴፪ እናም አሁን፣ እነሆ፣ የጌታ ቃል ኪዳን ተፈፅሟል፣ እናም እናንተ ተመትታችኋል እንዲሁም ተሰቃይታችኋል።
፴፫ ነገር ግን በሙሉ የልባችሁ ዓላማ ወደ ጌታ የምትመለሱ ከሆነ፣ እናም እምነታችሁን በእርሱ ካደረጋችሁ፣ እናም በሙሉ ትጉህ ህሊናችሁ እርሱን ካገለገላችሁ፣ ይህንን ካደረጋችሁ በፈቃዱና በደስታው መሰረት ከባርነት ያወጣችኋል።