ቅዱሳት መጻህፍት
የሶስቱ ምስክሮች ምስክርነት


የሶስቱ ምስክሮች ምስክርነት

ይህ ስራ ለሚደርሳቸው ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎች፣ እና ህዝቦች በሙሉ፥ እኛ በእግዚአብሔር አብና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ፣ ይህንን የኔፊ ህዝብ እናም ደግሞ የወንድሞቻቸውን የላማናውያንን፣ እናም ደግሞ ተነግሮበት ከነበረው ግንብ የመጡትን የያሬድ ህዝብ ታሪክ የያዘውን መዝገብ እንዳየን የታወቀ ይሁን። እናም እኛ ደግሞ በእግዚአብሔር ኃይልና ስጦታ እንደተተረጎሙ የእርሱ ድምፅ ነግሮናልና እናውቃለን፤ ስለዚህ ስራው እውነተኛ እንደሆነ በእርግጠኝነት እናውቃለን። እናም ደግሞ በሰሌዳዎቹ ላይ የነበሩትን የተቀረፁ ጽሑፎች እንዳየን እንመሰክራለን፤ እናም እነርሱ ለእኛ የታዩን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ኃይል ነው። እናም እኛ አንድ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ እናም በዐይኖቻችን ፊት እንዳስቀመጠው፣ በዚያ ላይ የነበሩትን ሰሌዳዎችና የተቀረፁትን እንደተመለከትንና እንዳየን በጥሞና ቃላት እንናገራለን፤ እናም እኛ እነዚህን ነገሮች አይተን እውነት እንደሆኑ የምንመዘግበው በእግዚአብሔር አብ እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋ እንደሆነ እናውቃለን። እናም በእኛ አመለካከት ይህ ድንቅ ነው። ይሁን እንጂ፣ የጌታ ድምፅ ስለዚህ ነገር ምስክርነት ቃል እንድንሰጥ አዞናል፤ ስለዚህ፣ ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ ለመታዘዝ፣ ስለእነዚህ ነገሮች ምስክርነት እንሰጣለን። እናም በክርስቶስ ታማኞች ከሆንን፣ ልብሶቻችንን ከሰዎች ሁሉ ደም በማንፃት፣ እናም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ያለ እንከን እንደምንገኝ እናውቃለን፣ እናም ከእርሱ ጋር በሰማያት ለዘለዓለም እንኖራለን። እናም አንድ አምላክ ለሆኑት ለአብ፣ እናም ለወልድ፣ እናም ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ይሁን። አሜን።

ኦሊቨር ካውድሪ

ዴቪድ ዊትመር

ማርቲን ሀርስ