ኑ፣ ተከተሉኝ 2024 (እ.አ.አ)
ጥር 6–12 (እ.አ.አ)፦ “አድምጡ፣ እናንት ህዝብ ሆይ”፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1


“ጥር 6–12 (እ.አ.አ)፦ ‘አድምጡ፣ እናንት ህዝብ ሆይ’፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች፣” ኑ፤ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]

“ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)

ምስል
ቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍትን በአንድ ላይ ሲያነቡ

ጥር 6–12 (እ.አ.አ)፦ “አድምጡ፣ እናንት ህዝብ ሆይ”

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1

በህዳር 1831 (እ.አ.አ)፣ በዳግም የተመለሰችው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የአንድ አመት ተኩል ብቻ እድሜ ነበራት። ምንም እንኳን እያደገች የነበረች ብትሆንም፣ በሃያዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ በነበረ ነቢይ የምትመራና በአንጻራዊ ሁኔታ በትናንሽ ከተሞች የሚኖሩ በደንብ የማይታወቁ አማኞች የነበራት ቡድን ነበረች። ነገር ግን እግዚአብሔር እነዚህን አማኞች አገልጋዮቹና መልዕክተኞቹ አድርጎ ቆጠራቸው እንዲሁም እርሱ የሰጣቸው ራዕዮች ታትመው ለአለም እንዲደርሱ ፈለገ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1 ጌታ ለእነዚህ ራዕዮች የሰጠው መቅድም ወይም መግቢያ ነው። ምንም እንኳን የቤተክርስቲያኗ አባላት ቁጥር ትንሽ ቢሆንም እግዚአብሔር፣ አገልጋዮቹ እንዲያስተላልፉት የፈለገው መልእክት ግን ትንሽ እንዳልነበረ በግልፅ ያሳያል። ይህም ለሁሉም “የምድር ነዋሪዎች” እንዲማሩና ንስሃ እንዲገቡ እናም የእግዚአብሔርን “ዘለአለማዊ ቃል ኪዳን” እንዲመሰርቱ የሚያስተምር “የማስጠንቀቂያ ድምጽ” ነው (ቁጥር 4፣ 8፣ 22)። ይህንን መልእክት የሚሸከሙት አገልጋዮች “ደካሞችና ተራ ሰዎች” ናቸው። ነገር ግን እግዚአብሔር ያኔም ሆነ አሁን የእርሱን ቤተክርስቲያን “ከተደበቀችበት እና ከጨለማ” እንዲያወጡለት የሚፈልገው ትሁት አገልጋዮችን ነው (ቁጥር 23፣ 30)።

ምስል
የጥናት ምልክት

በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1

“አድምጡ፣ እናንት ህዝብ ሆይ።”

መቅድም መጽሃፍን ያስተዋውቃል። የመጽሃፉን ጭብጥና ዓላማዎች ይገልጻል እንዲሁም አንባቢዎች ለማንባብ እንዲዘጋጁ ይረዳል። ጌታ ለትምህርት እና ቃል ኪዳኖች “መቅድም” እንዲሆን ያዘጋጀውን ክፍል 1ን ስታነቡ (ቀጥር 6)፣ ጌታ ለራዕዮቹ የሰጠውን ጭብጥና ዓላማዎች ፈልጉ። በዚህ ዓመት ለምታደርጉት የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ጥናት የሚረዳችሁን ምን ትማራላችሁ? ለምሳሌ፣ በእነዚህ ራዕዮች ውስጥ “የጌታን ድምጽ [መስማት]” (ቁጥር 14) ወይንም “እነዚህን ትእዛዛት መርምሩ” (ቁጥር 37) ማለት ምን ማለት እንደሆነ ማሰላሰል ትችላላችሁ።

በተጨማሪም የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች መግቢያን ተመልከቱ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥4–6፣ 23–24፣ 37–39

ምስል
የሴሚናሪ ምልክት
ጌታ፣ የኋለኛው ቀን ነቢያትን ጨምሮ በአገልጋዮቹ በኩል ይናገራል።

ክፍል 1 የሚጀምረው እና የሚጨርሰው ጌታ በተመረጡ አገልጋዮቹ በኩል እንደሚናገር በሚያውጅበት ነው(ቁጥር 4–6፣ 23–24፣ 38 ተመልከቱ)። የሚከተሉትን በተመለከተ ከዚህ ራዕይ ምን እንደተማራችሁ ጻፉ።

  • ስለጌታ እና ስለድምፁ።

  • በዘመናችን ነቢያት የሚያስፈልጉት ለምን እንደሆነ።

ባገኟችኋቸው ነገሮች ምክንያት ምን ለማድረግ ፍላጎት እንዳሳደረባችሁ።

የጌታን ድምጽ በአገልጋዮቹ ድምጽ በኩል የሰማችሁት መቼ እንደሆነ (ቁጥር 38 ተመልከቱ)።

በህይወት ስላሉ ነቢያት የማያውቅ አንድ ጓደኛችሁ ክፍል 1ን ከእናንተ ጋር እያነበበ እንደሆነ ልታስቡም ትችላላችሁ። ጓደኛችሁ ምን ጥያቄዎች ሊኖረው እንደሚችል። በእኛ ዘመን ነቢያት ስላሉ ምን እንደሚሰማችሁ እንዲገነዘብ ወይም እንድትገነዘብ ለመርዳት ከጓደኛችሁ ጋር በየትኞቹን ጥቅሶች ላይ ለመወያየት ትፈልጉ ይሆናል?

በ1831 (እ.አ.አ) የሽማግሌዎች ምክር ቤት የጆሴፍ ስሚዝን ራዕዮች ስለማተም ለመነጋገር በተገናኘ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች ሀሳቡን ተቃውመዉት እንደነበር የማወቅ ፍላጎት ይኖራችሁ ይሆናል። ጆሴፍ የነበረው ደካማ የፅሁፍ ችሎታ አሳፍሯቸው ነበር፣ እንዲሁም ራዕዮቹን ማሳተም በቅዱሳን ላይ የበለጠ ችግር ሊያስከትል ይችላል በማለት ተጨንቀው ነበር (ቅዱሳን1፥140–43 ተመልከቱ)። የዚህ ምክር ቤት አባል የነበራችሁ ብትሆኑ ኖሮ እነዚህን ሥጋቶች እንዴት ታቃልሉ ነበር? በክፍል 1 ውስጥ ሊረዱ ይችሉ የነበሩ ምን ግንዛቤዎችን ታገኛላችሁ? (ለምሳሌ፣ ቁጥር 6፣ 24፣ 38 ተመልከቱ)።

በጥናታችሁ እና በአምልኳችሁ ውስጥ “ኑ፣ የነቢያትን ድምጽ ስሙ፣” (መዝሙር፣ ቁጥር 21) የመሰለ መዝሙርን ማካተት ግምት ውስጥ አስገቡ። በክፍል 1 ውስጥ ካሉት ጥቅሶች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ መርሆዎችን የሚያስተምሩ ሀረጎችን በመዝሙሩ ውስጥ ፈልጉ።

በተጨማሪም፣ ርዕሶች እና ጥያቄዎች፣ “ነቢያት፣” በየወንጌል ላይብረሪ ውስጥ ተመልከቱ።

ምስል
የቤተክርስቲያኗ አባላት በአጠቃላይ ጉባኤ ላይ መሪዎችን ሲደግፉ።

ጌታ አገልጋዮቹ በሆኑት በነቢያት በኩል ይናገራል።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥12–30፣ 34–36

ዳግም መመለሱ በኋለኛው ቀናት የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች እንድቋቋም ይረዳኛል።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ክፍል 1ውስጥ፣ ጌታ ወንጌሉን ለምን ዳግም እንደመለሰ ያብራራል። ቁጥር 12–23ን ስታነቡ ምን ያህል ምክንያቶችን መዘርዘር እንደምትችሉ ተመልከቱ። በእናንተ ተሞክሮ፣ የጌታ የዳግም መመለስ ዓላማዎች እንዴት እየተፈፀሙ ናቸው?

ጌታ የእኛ ዘመን ከባድ ፈተናዎች እንደሚኖሩት ያውቅ ነበር (ቁጥር 17ን ተመልከቱ)። በቁጥር 17–30፣ 34–36 ውስጥ ሰላም እና መተማመን እንዲሰማችሁ የሚረዷችሁ ምን ታገኛላችሁ?

በተጨማሪም ራስል ኤም. ኔልሰን “ወደፊትን በእምነት ተቀበሉ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2020 (እ.አ.አ)፣ 73–76ን ተመልከቱ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥19–28

ጌታ ዓላማውን ለማስፈፀም “ደካሞችና ተራ ሰዎችን” ይጠቀማል፡፡

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥19–28ን ስታነቡ፣ የጌታ አገልጋይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ልታሰላስሉ ትችላላችሁ። ጌታ የእርሱ አገልጋዮች ምን አይነት ባህርያት እንዲኖራቸው ይፈልጋል? ጌታ በእርሱ አገልጋዮች በኩል ምን እያስፈፀመ ነው? በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በመላው ዓለም እና በእናንተ ህይወት ውስጥ እንዴት እየተፈፀሙ ናቸው?

ኢየሱስ ክርስቶስን ፈልጉ። የቅዱሳት መጻህፍት አላማ ስለአዳኙ እና ስለወንጌሉ መመስከር ነው። ትምህርትና ቃል ኪዳኖች 1ን ስታነቡ ስለኢየሱስ ከርስቶስ በሚያስተምራችሁ ጥቅሶች ላይ ማስታወሻ መፃፍን ወይም ምልክት ማድረግን አስቡ።

ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ወር የሊያሆና እና የለወጣቶች ጥንካሬ መጽሄቶች ዕትሞችን ተመልከቱ።

ምስል
የልጆች ክፍል ምልክት 02

ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥4፣ 37–39

ጌታ በነቢያቱ በኩል ስለመንፈሳዊ አደጋዎች ያስጠነቅቀኛል።

  • ከጌታ የሚመጡ ማስጠንቀቂያዎችን የተመለከተ ውይይት ለመጀመር፣ ማየት ስለማንችላቸው ከሌሎች ስለምንቀበላቸው የአደጋዎች ማስጠንቀቂያዎች በመነጋገር መጀመር ትችላላችሁ። አንዳንድ ምሳሌዎች አንሸራታች ወለልን፣ እየመጣ ያለ አውሎ ነፋስን ወይንም እየመጣ ያለ መኪናን ሊያካትቱ ይችላሉ። ምናልባት እናንተ እና ልጆቻችሁ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ምሳሌዎችን ልትመለከቱና እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ጌታ ከሚሰጠን ማስጠንቀቂዎች ጋር ማወዳደር ትችላላችሁ። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥4–6፣ 37–39 መሰረት፣ ጌታ የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? በቅርቡ ስለምን አስጠንቅቆናል? ምናልባት በቅርብ የተደረጉ የአጠቃላይ ጉባኤ መልዕክቶች ክፍሎችን ማንበብና የእግዚአብሔርን “ማስጠንቀቂያ ድምጽ” ምሳሌዎች መፈለግ ትችላላችሁ።

  • እንደ “Follow the Prophet [ነቢዩን ተከተሉ]” (የልጆች የመዝሙር መጽሐፍ፣ 111) የመጨረሻ ስንኝ የመሰሉ ስለነቢያት የተዘመረ መዝሙር በህብረት ዘምሩ። ነቢዩ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚናገር ምስክርነታችሁን አካፍሉ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥17

ዳግም መመለስ በኋለኛው ቀናት የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች እንድቋቋም ይረዳኛል።

  • ስለ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥17 የሚደረግን ውይይት ለማበረታታት እናንተ እና ልጆቿችሁ ጉዞ ለመሄድ እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ ልታስቡ ትችላላችሁ። ምን በመጫን ትይዛላችሁ? ዝናብ እንደሚጥል ወይም መኪናችሁ ወይም የምትሳፈሩበት አውቶቡስ ጎማ እንደሚተነፍስ አስቀድማችሁ አውቃችሁ ቢሆን ኖሮ ለጉዞው ትዘጋጁበት በነበረው መንገድ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረው ነበር? ቁጥር 17ን አብራችሁ አንብቡ ከዚያም ጌታ እኛ ላይ እንደሚሆን ያውቅ የነበረውን ተነጋገሩ። ለዚያ እንዴት ተዘጋጀ? (አስፈላጊ ከሆነ፣ “ጥፋት” የተፈጥሮ አደጋ ወይም እጀግ አስፈሪ ነገር መሆኑን አስረዱ።) የእግዚአብሔር ትዕዛዛት የዘመናችንን ፈተናዎች እንድንቋቋም እንዴት ይረዱናል?

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥17፣ 29

ጆሴፍ ስሚዝ ነቢይ እንዲሆን ጌታ ጠራው።

  • ጆሴፍ ስሚዝ የአዳኙን ወንጌል ዳግም በመመለስ ረገድ ስለነበረው ሚና ለማወቅ፣ እናንተ እና ልጆቿችሁ የአዳኙን ምስል እና የጆሴፍ ስሚዝን ምስል (ምስሎቹን በዚህ መዘርዝር ውስጥ ተመልከቱ) መመልከት እና አዳኙ በጆሴፍ ስሚዝ በኩል ምን እንደሰጠን መነጋገር ትችላላችሁ። ልጆቿችሁ በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥17፣ 29 ውስጥ ምሳሌዎችን ሊፈልጉ ይችላሉ። እግዚአብሔር “አገልጋዩን ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊን [እንደጠራው] (ቁጥር 17) እንዴት እንዳወቃችሁ ለልጆቿችሁ ንገሯቸው።

ምስል
የጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ ፎቶ

© 1998 David Lindsley

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥30

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የጌታ “እውነተኛ እና ህያው ቤተከርስቲያን” ናት።

  • ቤተክርስቲያኗ “እውነተኛ እና ህያው” ናት ሲባል ምን ማለት ነው? ልጆቻችሁ ስለዚህ ጥያቄ እንዲያስቡ ለማድረግ ምናልባትም ህይወት ያለውን ተክል እና የደረቀ ተክልን የመሰሉ ህይወት ያላቸው እና ህይወት የሌላቸው ነገሮችን ልታሳዩአቸው ትችላላችሁ። አንድ ነገር ህይወት እንዳለው እንዴት ማወቅ እንችላለን? ከዚያም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥30ን ልታነቡ እና ቤተክርስቲያኗ “እውነተኛ እና ህያው” ናት ማለት ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል ልትነጋገሩ ትችላላችሁ።

ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ወር የጓደኛ መጽሄት ዕትም ተመልከቱ።

አትም