“የዳግም መመለስ ድምጾች፦ የመፅሐፈ ሞርሞን ትርጉም፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“የመፅሐፈ ሞርሞን ትርጉም፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
የዳግም መመለስ ድምጾች
የመፅሐፈ ሞርሞን ትርጉም
የትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ክፍሎች 6–9 በተገለጡበት በ1829 (እ.አ.አ) ሚያዝያ ወር፣ የጆሴፍ ስሚዝ ዋና ስራ መፅሐፈ ሞርሞንን መተርጎም ነበር። ስለተአምራዊ የትርጉም ሂደቱ ብዙውን ዝርዝር አናውቅም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዘጋጀለት መሳሪያዎች፣ ኡሪም እና ቱሚም በሚባሉ ሁለት አንጸባራቂ ድንጋዮች እና ገላጭ ድንጋይ ተብሎ በሚጠራ ሌላ ተጨማሪ ድንጋይ፣ በመረዳት ጆሴፍ ስሚዝ ገላጭ እንደነበር እናውቃለን።
ከጊዜ በኋላ፣ ጆሴፍ ይህ መዝገብ እንዴት እንደተረጎመ ሲጠየቅም፣ “እያንዳንዱን ዝርዝር ለአለም መንገር አስፈላጊ አይደለም” ብሏል። አብዛኛውን ጊዜ ቀለል ባለ መልኩ “በእግዚአብሔር ስጦታና ሃይል” እንደተተረጎመ ይገልፅ ነበር።
ስለትርጉም ሂደቱ የአይን ምስክሮች የተናገሯቸው የሚከተሉት ቃላት ጆሴፍ የሰጠውን ምስክርነት ይደግፋሉ።
ኤማ ስሚዝ
“ባለቤቴ መፅሐፈ ሞርሞንን እየተረጎመ በነበረበት ወቅት፣ የተወሰነውን ክፍል እርሱ እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ቃል በቃል ሲናገር እኔ እጽፍ ነበር፤ እንዲሁም አንዳንድ ለመጥራት የሚያስቸግሩትን የሠዎች እና የቦታ ስሞች ወይም ረጅም ቃላት ሲያጋጥሙትም ፊደል እየቆጠረ ያነብ ነበር፤ እየፃፍኳቸው በነበረበት ወቅት የሆሄ አጻጻፍ ስህተት ከፈፀምኩኝም፣ ምንም እንኳን እንዴት እየጻፍኩኝ እንደነበረ ለማየት የማይችል የነበረ ቢሆንም ያስቆመኝና ስህተቴን ያርም ነበር። በመጀመሪያ ሳራ የሚለውን ቃል እንኳን መጥራት አይችልም ነበርና ፊደል እየቆጠረ ማንበብ ነበረበት፣ ከዚያም እኔ እንዴት እንደሚጠራ አሳየው ነበር።”
“ሰሌዳዎቹን ለመደበቅ የሚደረግ ምንም ጥረት ሳይኖር እንዲጠቀልልበት በሰጠሁት ትንሽ የላይነን ጨርቅ ተሸፍነው አብዛኛውን ጊዜ በጠረጴዛው ላይ ይቀመጡ ነበር። በአንድ ወቅት በጠረጴዛ ላይ እንዳሉ የሰሌዳዎቹን ጠርዝ እና ቅርፅ ዳስሻቸዋለሁ። ልክ እንደ ጠንካራ ወረቀት የሚተጣጠፉ ይመስሉ ነበር፣ እንዲሁም ልክ አንዳንዴ ሰዎች መጽሃፍን ከጠርዙ በጣት ሲገልጡ እንደሚሰማው አይነት ድምጽ በአውራ ጣት ከጠርዙ ሲገለጥ እንደ ብረት አይነት ድምፅ ይፈጥር ነበር። …
“የእኔ እምነት መፅሐፈ ሞርሞን እውነተኛ መለኮታዊ መሆኑን ነው—ስለዚህ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም። ማንም ሰው በመንፈሥ የተነሳሳ ካልሆነ በስተቀር ይህን ፅሁፉ ከራሱ ሃሳብ አመንጭቶ ሊናገር እንደማይችል ማወቄ ለእኔ ብቁ ነው፤ ምክንያቱም፣ እኔ እንደጸሃፊው ሆኜ ሳገለግል [ጆሴፍ] ለረጅም ሰዓታት የምጽፈውን በቃሉ ይናገር ነበር፤ እንዲሁም ከምግብ በኋላ ወይም በሌላ ምክንያት ከተፈጠረ መቋረጥ በኋላ ስንመለስ፣ ጹሁፉን ሳይመለከት ወይም ያቆመበት ክፍል ሳይነበብለት ወዲያው ካቆመበት ይቀጥል ነበር። ይህን ማድረግ ለእርሱ የተለመደ ነገር ነበር። ለተማረም ሰው ይህንን ማድረግ የሚቻል ነገር ላይሆን ይችላል፤ እንዲሁም በቀላሉ ለመናገር፣ አዋቂ ያልሆነ እና ያልተማረ ሰው ይሄንን ለማድረግ የማይቻል ነገር ነበር።”
ኦሊቨር ካውድሪ
“ሙሉውን መፅሐፈ ሞርሞን (ከጥቂት ገጾች በስተቀር)፣ በእግዚአብሔር ሥጦታ እና ሃይል በኡሪምና ቱሚም፣ ወይም በመጽሃፉ እንደተጠራው፣ በቅዱስ መተርጓሚዎች በመታገዝ እንደተረጎመው ከነቢዩ አፍ እንደወረደ በራሴ እስክርቢቶ ጽፌያለሁ። የተተረጎሙበትን የወርቅ ሰሌዳዎች በአይኖቼ አይቻለሁ እንዲሁም በእጆቼ ዳስሻለሁ። መተርጎሚያዎቹንም አይቻለሁ።”