“የካቲት 10–16 (እ.አ.አ)፦ ‘ድል ታደርግ ዘንድ’፦ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10–11፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2025 (እ.አ.አ) [2025 (እ.አ.አ)]
“ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10–11፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለቤት እና ለቤተክርስቲያን፦ 2025 (እ.አ.አ)
የካቲት 10–16 (እ.አ.አ)፦ “ድል ታደርግ ዘንድ”
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10–11
የመፅሐፈ ሞርሞን የትርጉም ስራ መካሄድ እየቀጠለ ሲሄድ አንድ ጥያቄ ተነሳ፦ ጆሴፍ ስሚዝ እና ኦሊቨር ካውደሪ የጠፉትን የትርጉም ገጾች በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ምክንያታዊ የሆነው ነገር ወደኋላ ተመልሶ ያንን ክፍል እንደገና መተርጎም ነበር፣ ነገር ግን እነርሱ ማየት ያልቻሉትን ጌታ ተመልክቶ ነበር፦ ጠላቶቻቸው በእነዚያ ገጾች ላይ ያሉትን ቃላት በመቀየር በጆሴፍ በመንፈስ የተነሳሳ ሥራ ላይ ጥርጣሬ ለመዝራት እያሴሩ ነበር። እግዚአብሔር ያንን ችግር ለማስወገድ እንዲሁም ሥራው ወደፊት እንዲቀጥል እቅድ ነበረው። በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት አስቀድሞ፣ እግዚአብሔር “በብልህ ዓላማው” ኔፊ ያንኑ ተመሳሳይ ጊዜ የሚሸፍነውን ሁለተኛ መዝገብ እንዲጽፍ አነሳሳው (1 ኔፊ 9፥5)።
“ጥበቤ፣” አለ ጌታ ለጆሴፍ “ከአጋንንት ብልጠት የላቀ” ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥43)። ያም በተለይ በእኛ ጊዜ ጠላት እምነትን ለማዳከም የሚያደርገው ጥረቶቹን እያጠናከረ ባለበት ወቅት ማረጋገጫ የሚሰጥ መልዕክት ነው። እኛም እንደ ጆሴፍ እግዚአብሔር እንድንሰራው በጠራን ስራ “ታማኝ [ሆነን መቀጠል]” እንችላለን (ቁጥር 3)። ከዚያም “የሲዖል ደጆች [እንዳ]ይቋቋሙ[ን]” መንገድ እንዳዘጋጀ እንገነዘባለን (ቁጥር 69)።
ቅዱሳን፣ 1፥51–61ን ተመልከቱ።
በቤት እና በቤተክርስቲያን ለመማር የሚረዱ ሃሳቦች
እግዚአብሔር “ሠይጣን የክፋት ዕቅዱን እንዲያከናውን [አይፈቅድም]።”
ሰይጣን፣ መኖሩን እንድንረሳ —ወይንም ቢያንስ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን እየጣረ እንደሆነ ባናውቅ ይመርጣል (2 ኔፊ 28፥22–23 ተመልከቱ)። ነገር ግን በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10 ውስጥ ያሉት የጌታ ቃላት ሰይጣን እውን እንደሆነ—እንዲሁም የእግዚአብሔርን ስራ በንቃት እንደሚቃወም ያረጋግጣሉ። በቁጥር 1–33 ውስጥ፣ እግዚአብሔር ስለ ሰይጣን ጥረቶች ምን እንዳወቀ ለዩ (በተጨማሪም ቁጥር 62–63 ተመልከቱ)። ሰይጣን በምን አይነት መንገድ እየፈተናችሁ እንደሆነ ለማወቅ እንዲረዳችሁ ጌታን ልትጠይቁሙ ትችላላችሁ። ክፍል 10ን ስታነቡ የሰይጣንን ጥረቶች ለመቋቋም ጌታ እንዴት ሊረዳችሁ እንደሚችል አሰላስሉ።
የጌታ “[ጥበብ] ከአጋንንት ብልጠት የላቀ” ነው።
ኔፊ የህዝቡን ሁለት መዝገቦች ለምን ለመፃፍ እንደተነሳሳ አያውቅም ነበር። ሞርሞንም ሁለተኛ ሥብስቡን ለምን ከወርቅ ሰሌዳዎቹ ጋር ለማካተት እንደተነሳሳ አላወቀም። ሆኖም ሁለቱም ነቢያት እግዚአብሔር “ብልህ አላማ” እንደነበረው ያምኑ ነበር (1 ኔፊ 9፥5፤ የሞርሞን ቃላት 1፥7)። ዛሬ፣ ቢያንስ የዚያን ዓላማ የተወሰነ ክፍል እናውቃለን፦ ይኸውም የጠፉትን የመፅሐፈ ሞርሞን 116 ገፆች ለመተካት ነበር። ጌታ ከዚህ ሁሉ ምን እንድትማሩ የሚፈልግ ይመስላችኋል? ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥34–52ን ስታነቡ በዚህ ጥያቄ ላይ አሰላስሉ። ከእነዚህ ጥቅሶች ስለጌታ የተማራችኋቸውን እውነቶች ዝርዝር ልታዘጋጁም ትችላላችሁ። እነዚህ እውነቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁ ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው? 116 ገፆች በሚጠፉበት ጊዜ ስለሚሆነው ነገር ዝግጅት ለማድረግ ሲል ጌታ ስላሳየው ጥበብ እና የወደፊቱን ስለማየት ችሎታው ምን ያስደንቃችኋል?
በህይወታችሁ ውስጥ የእርሱን ጥበብ እና የወደፊቱን የማየት ችሎታ ማስረጃ ለመፈለግ መነሳሳት ሊሰማችሁም ይችላል። በሽማግሌ ሮናልድ ኤ. ራዝባንድን መልእክት ውስጥ ያሉትን ዘገባዎች አንብቡ “By Divine Design [በመለኮታዊ ንድፍ]” —ምሳሌዎችን ወደ አዕምሯችሁ ሊያመጡ ይችላሉ (ሊያሆና፣ ህዳር 2017 (እ.አ.አ)፣ 55–57)። እነሱም እንደመጡላችሁ መጻፍን ወይም ለሌላ ሰው ማጋራትን አስቡ። ጌታ በህይወታችሁ እንዴት እየሰራ ነው? ለምሳሌ፣ ምን ዓይነት “የሁኔታዎች መገጣጠምን” አዘጋጅቷል? ለበረከቶቻችሁ ምን መሠረቶችን ጥሏል? የተቸገረን ሠው ወደማገልገል የመራችሁ መቼ ነው?
በተጨማሪም ሮሜ 8፥28፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 90፥24፤ ርዕሶች እና ጥያቄዎች፣ “የደህንነት ዕቅድ፣” የወንጌል ላይብረሪ፣ ተመልከቱ።
“[በጌታ] መንፈሥ ላይ እምነትህን [ማድረግ]”
የጆሴፍ ታላቅ ወንድም የሆነው ሃይረም ጌታ ለእርሱ ያለውን ፈቃድ ለማወቅ ጓጉቶ ነበር፣ ስለዚህም ጆሴፍ ስለእርሱ ራዕይ እንዲቀበልለት ጠየቀው። ነቢዩ ያንን ለማድረግ ደስተኛ ነበር፣ ነገር ግን በዚያ ራዕይ ውስጥ ከነበሩት ቢያንስ አንዱ መልዕክት (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11) ሃይረምም የራሱን ራዕይ መቀበል ይችላል የሚል ነበር። ስለዚህም “መልካም ፈቃድ ላላቸው፣ እናም በማጭዳቸው ለመሰብሰብ [የሚያጭዱ] ሁሉ ” ይችላሉ (ቁጥር 27)። ክፍል 11ን ስታነቡ፣ ጌታ ስለግል ራዕይ ምን እያስተማራችሁ ይመስላችኋል? ይህ በክፍል 6–9 ውስጥ ኦሊቨር ካውድሪንን ካስተማረው ነገር ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው? ለእናንተ ሌላ ምን መልዕክቶች አለው?
በተጨማሪም “መንፈስ ቅዱስ ይምራ፣” መዝሙር፣ ቁጥር 143 ተመልከቱ።
“[የእግዚአብሔርን ቃል] ለማግኘት” ስፈልግ፣ የእርሱን መንፈስና ሃይል እቀበላለሁ።
መፅሐፈ ሞርሞን ከመተርጎሙ በፊት እንኳን፣ ሃይረም ስሚዝ በዳግም መመለሱ ስራ ለመርዳት ጉጉት ነበረው። ጌታ ስለፍላጎቱ የነበረውን ምላሽ ስታነቡ ለእናንተ “ [የእግዚአብሔርን ቃል] ማግኘት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስቡ (ቁጥር 21)። የእግዚአብሔርን ቃል መቀበላችሁ በኃይል እንድታገለግሉት የሚረዳችሁ እንዴት ነው?
ልጆችን ለማስተማር የሚረዱ ሀሳቦች
አዘወትሬ ስፀልይ ከእግዚአብሔር ብርታትን አገኛለሁ።
-
ይህንን ጥቅስ ለልጆቻችሁ ለማስተዋወቅ “አዘወትረው” ስለሚያደርጓቸው ነገሮች ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥5 ውስጥ ጌታ አዘወትረን እንድናደርግ ያዘዘው ምንድን ነው? ይህንን እንድናደርግ የሚፈልገው ለምንድን ነው?
-
ልጆቻችሁ አዘወትረው ለመጸለይ እንዲያስታውሱ እንዴት ለመርዳት ትችላላችሁ? ምናልባት ጥቂት ትናንሽ፣ ለስላሳ ድንጋዮችን ሊሰበስቡና በእነዚያ ላይ “ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥5” ወይም “ዘወትር ፀልይ” ብለው በቀለም ሊፅፉባቸው ይችላሉ። እንዲጸልዩ አስታዋሽ ማግኘት በሚፈልጉባቸው በተለያዩ ቦታዎች ለምሳሌ በአልጋቸው አጠገብ፣ በመጽሐፎቻቸው ወይም ምግብ በሚበሉበት ቦታ ድንጋዮቻቸውን ማስቀመጥ ይችላሉ። በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 10፥5 መሰረት፣ ጌታ በምንፀልይበት ጊዜ እንዴት ይባርከናል? ልጆቻችሁ እንደ “A Child’s Prayer [የልጅ ጸሎት]፣” (የልጆች መዝሙር መጽሃፍ፣ 13) ከተመሳሠሉ መዝሙሮች ተጨማሪ መልሶችን ማግኘት ይችላሉ።
መንፈስ ቅዱስ መልካም የሆነውን ወደ ማድረግ ይመራኛል።
-
ልጆች መንፈስ እያናገራቸው እንደሆነ ማወቅን ሊማሩ ይችላሉ። እነርሱን ለመርዳት አንድን አምፖል ወይም የእጅ ባትሪ እና የደስተኛ ፊት ምስልን በክፍሉ ውስጥ አንድ ቦታ ልትደብቁና ከዚያም ልጆቻችሁ እነዚህን ነገሮች እንዲፈልጉ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥13 አንብቡ፣ ከዚያም ልጆቻችሁ ካገኟቸው ነገሮች ጋር የሚዛመዱ ቃላቶችን እንዲለዩ እርዷቸው። እነዚህ ቃላት መንፈስ ቅዱስ እኛን ስለሚረዳበት መንገድ ምን ያስተምሩናል?
-
የራሳችሁን መንፈሳዊ ተሞክሮ ማካፈል ልጆቻችሁ በህይወታቸው የመንፈስን ተፅዕኖ እንዲያውቁ ሊረዳቸው ይችላል። እነርሱም ተሞክሮዎቻቸውን እንዲያካፍሉ ጠይቋቸው። መንፈስ ቅዱስ ሲመራን እንዴት ማወቅ እንደምንችል አብራችሁ በመፈለግ፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥12–13 በአንድነት ልታነቡም ትችላላችሁ። የሰማይ አባት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ሊመራን እንደሚፈልግ መስክሩ።
ሌሎች እውነትን እንዲያገኙ ለመርዳት እንድችል ወንጌሉን ማወቅ ይኖርብኛል።
-
ልክ እንደ ሃይረም ስሚዝ፣ ልጆቻችሁም ወንጌልን ለሌሎች የማካፈል ብዙ አጋጣሚዎችን ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 11፥21፣ 26ን በአንድነት ልታነቡ ትችላላችሁ ከዚያም ሃይረም ወንጌልን ማስተማር ይችል ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ጌታ የነገረውን እንዲፈልጉ ልጆቻችሁን ጠይቋቸው። የእግዚአብሔር ቃል “ማግኘት” ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን “የምናከማቸው” እንዴት ነው? ምናልባት ልጆቻችሁ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ወይም ስለመፅሐፈ ሞርሞን ለሌሎች ሲያካፍሉ የሚያሳይ ትወና ሊተውኑ ይችላሉ።