ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ)
ሚያዝያ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36፥ “ወንጌሌን እንድትሰብክ … ተጠርተሀል”


“ሚያዝያ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36፥ ‘ወንጌሌን እንድትሰብክ … ተጠርተሀል፣’” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ) [2020 (እ.አ.አ)]

“ሚያዝያ 5–11 (እ.አ.አ)። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ 2021 (እ.አ.አ)

ምስል
ቀደምት የቤተክርስቲያን ሚስዮናውያን

ሚያዝያ 5–11 (እ.አ.አ)

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36

“ወንጌሌን እንድትሰብክ … ተጠርተሀል”

በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ እኛ ላለንበት የተለየ ሁኔታ የሚሆን ጥልቅ ሃሳብ ልናገኝ እንችላለን። ለእናንተ የሚሆን መልእክትን በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36 ውስጥ ለማግኘት እንዲረዳችሁ ጌታን ጠይቁ።

ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ

ፓርሊ ፒ. ፕራት ጥሪ ደርሶት “ወደ ምድረበዳ” ሄዶ ወንጌልን እንዲሰብክ ሲጠየቅ ገና የአንድ ወር ገደማ የቤተክርስቲያን አባል ነበር (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 32፥2)። ቶማስ ቢ. ማርሽ “ተደሰት፣ የተልዕኮህ ሰዓት መጥቷልና” ተብሎ ሲነገረው ከዛም ላነሰ ጊዜ ነበር አባል የነበረው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 31፥3)። ኦርሰን ፕራት፣ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ፣ እናም ሌሎችም ብዙዎች እንደዚሁ የአገልግሎት ጥሪያቸውን ሲቀበሉ ገና የተጠመቁ አባላት ነበሩ። ምናልባትም ይህ ከወቅቱ አንጻር አስፈላጊ ነበር፤ በ1830 (እ.አ.አ) ክረምት ወቅት ከስድስት ወር በላይ የቤተክርስቲያኗ አባል የሆነ ማንም ሰው አልነበረም። ነገር ግን ከዚህ ሂደት ዛሬ ለእኛ የሚሆን ትምህርት አለ፥ በዳግም የተመለሰውን ወንጌል በጥምቀት ለመቀበል በቂ እውቀት ካላችሁ፣ ለሌሎችም ለማካፈል በቂ እውቀት አላችሁ። በእርግጥ ሁላችንም የወንጌል እውቀታችንን ለማሳደግ እንፈልጋለን፣ ነገር ግን እግዚአብሔር “ያልተማሩት” የእርሱን ወንጌል እንዲሰብኩ ለመጥራት አመንትቶ አያቅም (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 35፥13)። እንዲሁም እርሱ ሁላችንንም “ወንጌሌን ለማወጅ [አንደበታችሁን ክፈቱ]” በማለት ሁላችንንም ይጋብዛል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30፥5)። እናም ይህንንም በደንብ ተግባራዊ የምናደርገው በራሳችን ጥበብና ተሞክሮ ሳይሆን ነገር ግን “[በመንፈስ] ኃይል” ነው (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 35፥13).

እንዲሁም “The Faith and Fall of Thomas Marsh [የቶማስ ማርሽ እምነት እና ወድቀት]፣” “Ezra Thayer: From Skeptic to Believer [እዝራ ታየር፥ ከተጠራጣሪነት ወደ አማኝነት]፣” “Orson Pratt’s Call to Serve [የኦርሰን ፕራት አገልግሎት ጥሪ]፣” ራዕያት በአገባብ፣ 54–69 ይመልከቱ።

ምስል
የግል ጥናት ምልክት

ለግል የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ሃሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36

የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል እንድሰብክ ተጠርቻለሁ።

እንደ ሚስዮናዊ ጥሪ ቢኖራችሁም ባይኖራችሁም ጌታ ወንጌሉን እንድትካፈሉ ይሻል፣ እናም ለቀደምት የዚህ የዘመን ፍጻሜ ሚስዮናውያን የተናገራቸው ብዙዎቹ ቃሎቶቹ ለእናንተም ጭምር ናቸው። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30–36ን ስታነቡ፣ ወደወንጌል መስበክ ስለመጠራት የተማራችሁትን መዝግቡ። ጌታ ከሚስዮናውያኖቹ የጠየቃቸውን ነገሮች ለማስፈር አንድ ዝርዝርን (ለምሳሌ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30፥8ን ተመልከቱ) እናም ደግሞ ለገባላቸው ቃል ኪዳኖች ለማስፈር ሌላ ዝርዝርን ማዘጋጀት ትችልላችሁ (ለምሳሌ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30፥11ን ይመልከቱ)።

እነዚህ ጥቅሶች በምን አይነት መልኩ ወንጌልን በመስበክ ወይም የቤተክርስቲያን አገልግሎት ሚሲዮናዊ ለመሆን የሚዘጋጅን ወይንም እያገለገለ ያለን ሰው ሊያበረታቱት ይችላሉ? ወንጌልን እንድትካፈሉ የሚያበረታታችሁ ምን ታገኛላችሁ?

በተጨማሪም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 35፥13–15፤ ራስል ኤም. ኔልሰን እና ዌንዲይ ደብሊው. ኔልሰን “የእስራኤል ተስፋ” [የወጣቶች አለም አቀፍ ማነቃቂያ፣ ሰኔ 3፣ 2018 [እ.አ.አ)]፣ HopeofIsrael.ChurchofJesusChrist.org፣ ሲልቪአ ኤች. ኦልሬድ “ወደዛውም ሂዱ፣” ኤንዛይን ወይም ሊያሆና፣ ህዳር 2008 (እ.አ.አ)፣ 10–12ን ይመልከቱ።

ምስል
ሚስዮናውያን ሲያስተምሩ

ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሚስዮናውያን ነን።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 31፥1–2፣ 5–6፣ 9፣ 13

ጌታ ከቤተሰቦቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት ይረዳኛል።

በ1830 (እ.አ.አ) አመታት የነበሩ ቤተሰቦች አሁን ካሉ ቤተሰቦች ጋር ብዙ ተመሳሳይ ችግሮች ነበሩባቸው። ጌታ ለቶማስ ቢ. ማርሻል ስለቤተሰቡ ምን አይነት መመሪያ እና ቃል ኪዳንን ሰጠው? የእርሱ ቃል በቤተሰባችሁ ግንኙነት እንዴት ሊረዳችሁ ይችላል?

ስለ ቶማስ ማርሽ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቅዱሳን፣ 1፥79–80119–20ን ይመልከቱ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 3235

ወደላማናውያን የተደረገው ተልዕኮ ውጤት አልባ ነበርን?

ኦሊቨር ካውድሪ፣ ፒተር ዊትመር ዳግማዊ፣ ፓርሊ ፒ. ፕራት፣ እና ዚባ ፒተርሰን ወደ ምዕራብ ሚዙሪ ሄደው ለየአሜሪካ ህንዶች ወንጌልን ሲሰብኩ በመፅሐፈ ሞርሞን ላይ የተነገረውን በኋለኛው ቀናት ላማናውያን ወንጌልን ይቀበላሉ የሚለውን ትንቢት እየፈጸሙ እንደሆነ ያምኑ ነበር (ለምሳሌ 1 ኔፊ 13፥34–41ኢኖስ 1፥11–18ን ይመልከቱ)። እናም በተልዕኳቸው መጨረሻም፣ ምንም እንኳን ከአንዳንድ ቡድኖች ጋር መልካም የሆኑ ነገሮች ቢገጥማቸውም አንድም እንኳን የአሜሪካ ህንድን አላጠመቁም ነበር። ነገር ግን ወደ ሚዙሪ በሚሄዱበት ወቅት እግረ መንገዳቸውን አቁመው በነበረበት ከርትላንድ፣ ኦሃዮ ውስጥ ከመቶ በላይ ሰዎችን አጥምቀው ነበር። ከተለወጡት መሀከልም እንደ ሲድኒ ሪግደን አይነት ወደፊት ተጽዕኖ ፈጣሪ የቤተክርስቲያን መሪዎች የሆኑ ነበሩበት፣ እንዲሁም ከርትላንድ በኋላ ላይ ለቤተክርስቲያኗ እንደ ጠቃሚ መሰባሰቢያ ስፍራ ሆነች። ከዚህ ልምድ ጌታ ስራውን እንዴት እንደሚያከናውን ምን ተማራችሁ?

በተጨማሪም “A Mission to the Lamanites [ተልዕኮ ወደ ላማናውያን]፣ ” ራዕያት በአገባብ፣ 45–49 ይመልከቱ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 33፥12–18

ህይወቴን በአዳኝ ወንጌል ላይ ከገነባሁ አልወድቅም።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 33 የተጻፈው ለኖርዝሮፕ ስዊት እና እዝራ ታይር ለተባሉ ሁለት አዳዲስ የተለወጡ አባላት ነበር። ኖርዝሮፕ ይህ ራእይ ከተሰጠ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ቤተክርስቲያኗን ለቆ ሄደ። እዝራም ለተወሰነ ጊዜ ታማኝ ሆኖ ቢያገለግልም፣ ነገር ግን እርሱም በመጨረሻም ተሰናከለ። ይህ በወንጌሉ “አለት ላይ” (ቁጥር 13) ምን ያህል ጠንካራ ሆናችሁ እንደተገነባችሁ እራሳችሁን ለመገምገም መልካም አጋጣሚ ሊሆንላችሁ ይችላል። ከእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የትኞቹ እውነታዎች በአዳኝ እንደታመናችሁ እንድትቀጥሉ ይረዷችኋል?

ምስል
የቤተሰብ ጥናት ምልክት

ለቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ሃሳቦች

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 30፥2እንደ ቤተሰብ ከ“ምድራዊ ነገሮች” ይልቅ የእግዚአብሔር ነገሮች ላይ በማተኮር እንዴት እያደረግን ነን?

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 31ጌታ ለቶማስ ማርሽ ስለቤተሰቡ የገባለትን ቃል ኪዳን ስታነቡ፣ በራሳችሁ ቤተሰብ ውስጥ በሚስዮናዊ አገልግሎት ምክንያት ስለመጡላችሁ በረከቶች መነጋገር ትችላላችሁ። ተዛማጅ የሆኑ እንደ “አንተ ወደፈለከው እሄዳለሁ” የሚሉ አይነት መዝሙሮችን መዘመርም ትችላላችሁ (መዝሙር ቁጥር 270)። ቤተሰባችሁ ወንጌልን ለሌሎች በማካፈል በምን መልኩ ተባርካችኋል?

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 33፥7–10ጌታ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ወንጌል ማካፈልን ለመግለጽ ምን አይነት ተምሳሌቶችን ተጠቅሟል? የእናንተስ ቤተሰብ ምን አይነት ተምሳሌዎችን ወይንም ዘይቤዎችን ሊያስብ ይችላል? ምናልባት እነዚህ ተምሳሌዎች ቤተሰባችሁ ወንጌልን የሚያካፍልበትን ዘዴ ለመፍጠር ይረዷችኋል። ከዚያም ይህ ውይይት ወንጌልን ለማካፈል እቅድን ወደማውጣት ሊመራ ይችላል። ሊከሰቱ በሚችሉ ሁኔታዎች ተራ በተራ መለማመድ ትችላላችሁ።

ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 34፥10ቁጥር 10 ላይ አንድ ሃረግን ምረጡ፣ እናም የቤተሰብ አባል በሹክሹክታ እንዲለው ጋብዙ። ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሃረጉ ምን እንደሆነ መገመት ይችላሉ። ከዚያም ከቤተሰቡ አባል አንዱ ሃረጉን ከፍ ባለ ድምጽ እንዲለው ጠይቁ። ይህ ልምምድ ጌታ “ድምጻችሁን ከፍ” አድርጉ ብሎ ለምን እንደሚያዘን እንድንረዳ እንዴት ሊረዳን ይችላል?

ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት፣ የዚህን ሳምንት ዝርዝርኑ፣ ተከተሉኝ—ለመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ይመልከቱ።

የሚመከር መዝሙር፥ “ወደሚስዮን እንደምጠራ ተስፋ አደርጋለሁ፣” የልጆች መዝሙር መጽሃፍ 169።

ምስል
በዳግም የመመለስ ድምጾች ምልክት

በዳግም የመመለስ ድምጾች

ቀደምት ተለዋጮች

ቤተክርስቲያኗ ከመቋቋሟ አስቀድሞ ጌታ እንዲህ ሲል አወጀ “እርሻው ነጥቷል አዝመራውም ዝግጁ ነው” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 4፥4)። ይህ አባባል በቀጣዮቹ ወራት ብዙ የእውነት ፈላጊዎች በእግዚአብሔር መንፈስ እየተመሩ በዳግም የተመለሰችውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለመፈለግ ሲመጡ እውነትነቱን አረጋግጧል።

እነዚህ ብዙዎቹ ቀደምት ተለዋጮች በዳግም የመመለስን መሰረት በመጣል ቁልፍ ሚና ነበራቸው፣ እንዲሁም ታሪካቸው እስከ ዛሬም ድረስ ለእኛ በጣም ጠቃሚ ነው። እነርሱ ያሳዩት እምነት እኛም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መለወጣችንን ለማሳየት የሚያስፈልገን አይነት እምነት ነው።

አቢጌል ካልኪንስ ሊዮናርድ

አቢጌል ካልኪንስ ሊዮናርድ በእድሜዋ ሰላሳ አጋማሽ ላይ ሳለች ከኃጢያቷ ለመሰረይ ፍላጎት ተሰማት። ብዙውን ጊዜ መፅሐፍ ቅዱስን ታነባለች፣ እናም የክርስቲያን ቤተክርስቲያኖች ወደቤቷ መጥተው ይጎበኟትም ነበር፣ ነገር ግን አንዱን ቤተክርስቲያን ከሌላው ምን እንደሚለየው ግራ ያጋባት ነበር። እንዲህም አለች፣ “በአንዱ ማለዳ መፅሐፍ ቅዱሴን ይዤ ወደ ጫካ ወርጄ በጉልበቴ ተንበረከኩ።” ከልቧ ወደ ጌታ ጸለየች። እንዲህም አለች፣ “በቅጽበትም ራዕይ በፊቴ ተገለጸ፣ የተለያዩ ተቋማትም ተራ በተራ በፊቴ አለፉ፣ እናም ድምጽም እንዲህ ሲል ተናገረኝ ‘እነዚህ ለትርፍ የተገነቡ ናቸው’ ከዚያም፣ ባሻገር፣ ታልቅ ብርሃንም ለማየት እችል ነበር፣ ድምጽም ከበላይ ‘ህዝብን አስነሳለሁ፣ እነርሱንም የእኔ ለማድረግ እና ለመባረክ እደሰታለሁ’ ሲል ተሰማኝ።” ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ አቢጌል ስለመፅሐፈ ሞርሞን ሰማች። ምንም እንኳን የመጽሃፉ ቅጂ በእጇ ባይኖርም፣ እርሷ “በመንፈስ ቅዱስ ስጦታና ሃይል የዚህን መጽሀፍ እውነትነት ለማወቅ” ፈለገች፣ እናም እርሷ “ወዲያውኑ መኖሩን ተገነዘበች።” በመጨረሻም መፅሐፈ ሞርሞንን ማንበብ ስትችል፣ እርሷ “ልትቀበለው ዝግጁ” ነበረች። እርሷና ባለቤቷ ላይማን በ1831 (እ.አ.አ) ተጠመቁ።1

ቶማስ ቢ. ማርሽ

ቶማስ ቢ. ማርሽ ወጣት ሳለ መፅሐፍ ቅዱስን አጠና እናም በክርስትያን ቤተክርስቲያንም ተቀላቀለ። ነገር ግን እርካታን ባለማግኘቱ ከሁሉም ቤተክርስቲያኖች ራቀ። እንዲህም አለ፣ “ጥልቅ የሆነ የትንቢት መንፈስ ነበረኝ፣ እናም ለአንድ [የሃይማኖት መሪ] አዲስ ቤተክርስቲያን እንደሚነሳ፣ ይህም እውነትንም በንጽህና የያዘ እንደሚሆን እንደምጠብቅ ነገርኩት።” ብዙም ሳይቆይ፣ ቶማስ ባደረበት መንፈሳዊ መነሳሳት ቦስተን ማሳቹሴትስ ያለውን ቤቱን ትቶ ወደ ምዕራብ መጓዝ እንዳለበት ተሰማው። ሶስት ወር ያህል በምዕራባዊ ኒውዮርክ ከቆየ በኋላ የሚፈልገውን ባለማግኘቱ ጉዞውን ወደቤቱ ጀመረ። በመንገድ ላይ ሳለ አንዲት ሴት ቶማስን “ጆሴፍ ስሚዝ የተባለ ወጣት ስላገኘው ወርቃማ መጽሃፍት” ሰምቶ እንደሆነ ጠየቀችው። በዚህ ሃሳብ ተውጦ ቶማስ ወዲያውኑ ወደ ፓልማይራ ተጉዞ፣ የመጀመሪያዎቹ 16 የመጽሐፈ ሞርሞን ገጾች እየታተሙ ሳለ፣ ማርቲን ሃሪስን በማተሚያ ቤት ውስጥ አገኘው። ቶማስም እነዚህን 16 ገጾች ይዞ እንዲሄድ ተፈቀደለት እናም በቤት ወደ ባለቤቱ ኤሊዛቤጥ ይዟቸው ሄደ። “የእግዚአብሄር ቃል እንደሆነ በማመንዋ” በመጽሃፉ “በጣም ተደስታ” ነበር ሲል ያስታውሳል። ቆይተውም ቶማስ እና ኤሊዛቤጥ ከልጆቻቸው ጋር ወደ ኒውዮርክ ተዛወሩ እና ተጠመቁ።2 (ስለ ቶማስ ማርሽ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት፣ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 31ን ይመልከቱ።)

ፓርሊ እና ታንክፉል ፕራት

ልክ እንደ ቶማስ ማርሽ፣ ፓርሊ እና ታንክፉል ፕራት በኦሃዮ ያለውን የተትረፈረፈ እርሻቸውን በመተው ከመፅሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ወንጌል መስበክ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ላደረባቸው የመንፈስ ግፊት ምላሽ ሰጡ። ፓርሊ ለወንድሙ እንደተናገረው፣ “የእነዚህ ነገሮች መንፈስ በአዕምሮዬ በጣም ከመስፈኑ የተነሳ ምንም እረፍት የለኝም።”3 ወደምስራቅ ኒው ዮርክ ሲደርሱ፣ ፓርሊ በዛ ስፍራ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት እንዳለበት ተሰማው። ታንክፉል ግን ብቻዋን ጉዞዋን መቀጠል እንዳለባት ተስማሙ። እንዲህ በማለት ፓርሊ ነገራት፣ “በዚህ ሃገር ክፍለግዛት ልሰራው የሚገባኝ ስራ አለኝ፣ እናም ምን እንደሆነ፣ ወይንም ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶ መሰራት እንዳለበት አላውቅም፤ ነገር ግን ይህ ሲፈጸም እመጣለሁ።”4 በዚህም ስፍራ ነበር ስለመፅሐፈ ሞርሞን ፓርሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው። “ስለመጽሀፉ ለየት ያለ ፍላጎት አደረብኝ” ብሏል።5 የመጽሃፉን ቅጂ ጠይቆ ለሊቱን ሙሉ አነበበ። በጠዋትም መጽሃፉ እውነት እንደሆነ “በአለም ካለው ሃብት ሁሉ የበለጠ” ዋጋ እንዳለው አወቀ።6 በጥቂት ቀናት ውስጥ ፓርሊ ተጠመቀ። ከዚያም ወደ ታንክፉል ተመለሰ፣ እርሷም ተጠመቀች። (ስለፓርሊ ፒ. ፕራት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 32ን ይመልከቱ።)

ምስል
ፓርሊ ፒ. ፕራት

የፓርሊ ፒ ፕራት ምስል በጀፍሪ ሄይን

ስድኒ እና ፊቢ ሪግደን

ከኒው ዮርክ ወደ ሚዙሪ ሚስዮን በመሄድ ላይ የነበረው ፓርሊ ፕራትና ሌሎች አገልጋይ ባልደረቦቹ ሜንቶር፣ ኦሃዮ ሲደርሱ፣ ፓርሊ ኦሃዮ በነበረ ወቅት ያውቃቸው ወደነበሩት፣ ወደ ስድኒ እና ፊቢ ሪግደን ቤት ጎራ አሉ። ስድኒ የክርስቲያንና ሰባኪ ነበር፣ እና ፓርሊም የእርሱ ቤተክርስቲያን ምዕመን የነበረ ሆኖ፣ እንደ መንፈሳዊ መካሪው ይመለከተው ነበር። ፓርሊ በአጽንኦት ስለመፅሐፈ ሞርሞንና በዳግም ስለተመለሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ለጓደኞቹ ነገራቸው። ምንም እንኳን ስለመፅሐፈ ሞርሞን ጥርጣሬ ቢገባውም፣ ስድኒ ራሱ ከአዲስ ኪዳን ላይ ስለተገለጸው የእውነተኛው ቤተክርስቲያን መመለስ ሲያጠና ነበር የቆየው። “ነገር ግን መጽሃፍህን አነበዋለሁ፣ እናም ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ራእይ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ለማወቅ እጥራለሁ” ብሎ ለጓደኛው ፓርሊ ነገረው።7 ከሁለት ሳምንት ጥናትና ጸሎት በኋላ፣ ሁለቱም እርሱና ፊቢ መጽሃፉ እውነት እንደሆነ አረጋገጡ። ነገር ግን በተጨማሪ በቤተክርስቲያኗ መቀላቀል ማለት ለቤተሰቡ ትልቅ መስዋዕትን እንደሚያስከፍል ስድኒ አውቆ ነበር። እናም እንደ ሰባኪ ያለውን ስራ፣ እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ስፍራ ያለጥርጥር ያጣል። እርሱና ፊቢ ስለእውነታዎቹ ሲነጋገሩ፣ ፊቢ እንዲህ በማለት ገለጸች፣ “የሚያስከፍለንን ዋጋ አስልቻለሁ፣ እናም … የእኔ ፍላጎት፣ ሞትም ይሁን ህይወት፣ የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለማድረግ ነው።”8

ማስታወሻዎች

  1. ኤድዋርድ ደብሊው. ቱሊጅ The Women of Mormondom [የሞርሞን ሴቶች] 1877(እ.አ.አ)፣ 160–63 ይመልከቱ።

  2. “የቶስ ቦልድዊን ማርሽ ታሪክ፣” ዴዘረት ኒውስ፣ መጋቢት 24፣ 1858 (እ.አ.አ)፣ 18።

  3. Autobiography of Parley P. Pratt [የፓርሊ ፒ. ፕራት የግል የህይወት ታሪክ] 1938(እ.አ.አ)፣ 34።

  4. Autobiography of Parley P. Pratt [የፓርሊ ፒ. ፕራት የግል የህይወት ታሪክ] 36።

  5. Autobiography of Parley P. Pratt [የፓርሊ ፒ. ፕራት የግል የህይወት ታሪክ] 37።

  6. Autobiography of Parley P. Pratt [የፓርሊ ፒ. ፕራት የግል የህይወት ታሪክ] 39፤ በተጨማሪም ቅዱሳን፣ 1፥92–94 ይመልከቱ።

  7. In History, 1838–56 [Manuscript History of the Church], volume A-1, 73, josephsmithpapers.org.

  8. In History, 1838–56 [Manuscript History of the Church], volume A-1, 75, josephsmithpapers.org.

ምስል
ሰዎች በበረዶ ላይ ሲራመዱ

ወደ ምድረበዳው ሂዱ በሮበርት ቲ. ባሬት

አትም