ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፴


ክፍል ፴

መስከረም ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በፈየት ኒው ዮርክ በነቢዩ ጆሴፍ አማካይነት ከሶስት ቀን ጉባዔ በኋላ፣ ግን የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ከመለያየታቸው በፊት፣ ለዴቪድ ዊትመር፣ ለፒተር ዊትመር ዳግማዊ፣ እና ለጆን ዊትመር የተሰጠ ራዕይ። ይህ ጽሁፍ በመጀመሪያ የታተመው እንደ ሶስት ራዕይዎች ነበር፣ ይህም በ፲፰፻፴፭ (እ.አ.አ.) ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ቅጂ ውስጥ በነቢዩ በአንድ ክፍል ውስጥ ተካትተው ነበር።

፩–፬፣ ዴቪድ ዊትመር በትጋት ባለመስራቱ ተገሰጸ፤ ፭–፰፣ ፒተር ዊትመር ዳግማዊ ከኦሊቨር ካውድሪ ጋር ወደላማናውያን ተልዕኮ ይሂድ፤ ፱–፲፩፣ ጆን ዊትመር ወንጌልን እንዲሰብክ ተጠራ።

እነሆ፣ ዴቪድ እንዲህ እልሀለሁ፣ ሰውን በመፍራት ለጥንካሬ በእኔ መደገፍ ያለብህን ያህል አልተደገፍክም።

ነገር ግን አዕምሮህ በእኔ በፈጣሪህ ነገር እንዲሁም በተጠራህበት አገልግሎት ላይ ከመሆን ይልቅ በምድር ነገሮች ላይ ሆኗል፤ እናም መንፈሴን እና ከአንተ በላይ ስልጣን የተሰጣቸውን አላደመጥክም፣ ነገር ግን እኔ ባላዘዝኳቸው ተወስደሀል።

ስለዚህ፣ ከእጄ ለራስህ እንድትጠይቅ ተትተሀል፣ እናም ስለተቀበልካቸውም ነገሮች አሰላስል

እናም ተጨማሪ ትእዛዛትን እስከምሰጥህ ድረስ መኖሪያህ በአባትህ ቤት ይሆናል። በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እናም በአለም ፊት እና በአካባቢው ባሉት ዙሪያዎች አገልግሎትን ትሰጣለህ። አሜን።

እነሆ ፒተር፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ከወንድምህ ከኦሊቨር ጋር ትጓዛለህ፤ ወንጌሌን ለማወጅ አንደበትህን ትከፍት ዘንድ ለእኔ አስፈላጊ የሚሆንበት ወቅት መጥቷል፤ ስለዚህ አትፍራ፣ ነገር ግን ወንድምህ የሚሰጥህን ምክር እና ቃላት አድምጥ

እናም በስቃዩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ሁን፣ ለአንተ እና ለእርሱ ደህንነት በጸሎት እና በእምነት ዘወትር ልብህን ወደ እኔ አንሳ፤ በላማናውያን መካከል ቤተክርስቲያኔን እንዲገነባ ኃይልን ሰጥቼዋለሁና፤

እናም ከወንድሙ፣ ከጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ በቀር በእርሱ ላይ ማንንም የቤተክርስቲያኗን ነገሮች በተመለከተ የእርሱ አማካሪ እንዲሆን አልሾምኩም።

ስለዚህ፣ እነዚህን ነገሮች አድምጥ እናም ትእዛዛቴን በመጠበቅ ትጋ፣ እናም በዘለአለማዊ ህይወት ትባረካለህ። አሜን።

እነሆ፣ አገልጋዬ ጆን እንዲህ እልሀለሁ እንደመለከት ድምጽ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ወንጌሌን ማወጅ ትጀምራለህ።

እናም አገልግሎትህም ከእዚያ እንድትሄድ ትእዛዝ እስክሰጠህ ድረስ በወንድምህ በፊልፕ በሮው ስፍራና በአካባቢው፣ አዎን፣ እንዲሁም ድምጽህ በሚሰማበት ስፍራ ሁሉ ይሆናል።

፲፩ እናም ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በሙሉ ነፍስህ አገልግሎትህ ሁሉ በፅዮን ይሆናል፤ አዎን፣ ሰው ሊያደርግ የሚችለውን ሳትፈራ ለእኔ ስራ ዘወትር አንደበትህን ትክፍታለህ፣ እኔም ዘወትር ከአንተ ጋር እሆናለሁና። አሜን።