ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፷፱


ክፍል ፷፱

ህዳር ፲፩፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በሀይረም ኦሀዮ ውስጥ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። በአጭር ጊዜ ለመታተም የታሰቡት የራዕይ ዝግጅቶች በህዳር ፩–፪ ልዩ ጉባኤ ላይ ጸድቀው ነበር። በህዳር ፫፣ በኋላም ተጨማሪ መግለጫ በመባል የታወቀው፣ በዚህ በክፍል ፻፴፫ ውስጥ ያለው ራዕይ ተጨምሮ ነበር። ኦሊቨር ካውድሪ የራዕዮች እና ትእዛዛት ዝግጅቶች ፅሁፎችን ወደ ኢንዲፔንደንስ ሚዙሪ ለመታተም እንዲወስድ ተመርጦ ነበር። የሚዙሪ ቤተክርስቲያንን ለመገንባት ተሰጥቶ የነበረውን ገንዘብም እንዲሁ መውሰድ ነበረበት። ይህም ራዕይ ጆን ዊትመር ከኦሊቨር ካውደሪ ጋር አብሮ እንዲሄድ መመሪያ ሰጥቷል እናም ዊትመር እንደ ቤተክርስቲያኗ የታሪክ ምሁር እና መዝጋቢ እንዲጓዝ እና ታሪካዊ ነገሮችን እንዲሰበስብ መመሪያ ሰጥቶ ነበር።

፩–፪፣ ጆን ዊትመር ኦሊቨር ካውድሪን ተከትሎ ወደ ሚዙሪ ይሂድ፤ ፫–፰፣ እርሱም ይስበክ፣ እና ታሪካዊ መረጃዎችን ይሰብስብ፣ እናም ይጻፍ።

ለአገልጋዬ ኦሊቨር ካውድሪ ጥቅምም አድምጡኝ፣ ይላል ጌታ አምላካችሁ። እውነተኛ እና ታማኝ የሆነ ከእርሱ ጋር ካልሄደ በስተቀር፣ ወደ ፅዮን ምድር ይዞ የሚሄዳቸውን ትእዛዛት እና ገንዘቦች ለእርሱ በአደራ መስጠቱ በእኔ ዘንድ ጥበብ አይደለም።

ስለዚህ፣ እኔ ጌታ አገልጋዬ ጆን ዊትመር ከአገልጋዬ ኦሊቨር ካውድሪ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፍቃዴ ነው፤

እና ደግሞም ስለቤተክርስቲያኔ የሚመለከታቸውን እና የሚያውቃቸውን አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ መጻፉን እና ታሪክንም መሰብሰቡን ይቀጥል፤

እና ደግሞም ከኦሊቨር ካውድሪ እና ከሌሎችም ምክርን እና እርዳታን ይቀበል።

እና ደግሞም፣ በአለም ያሉት አገልጋዮቼም የመጋቢነታቸውን መግለጫዎች ወደ ምድረ ፅዮን ይላኩ፤

ምድረ ፅዮንም የመቀበያ እና እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚደረጉባት ዋና ስፍራ ናትና።

ይሁን እንጂ፣ በቀላል እውቀትን እንዲያገኝ፣ አገልጋዬ ጆን ዊትመር፣ ከስፍራ ወደ ስፍራ፣ እናም ከቤተክርስቲያኗ ወደ ቤተክርስቲያኗ፣ ለብዙ ጊዜ ይጓዝ፣

እየሰበከ እና እያብራራ፣ ለቤተክርስቲያኗ ጥቅም እና በፅዮን ምድር ለሚያድጉት የሚቀጥሉት ትውልዶች እስከዘለአለም ይይዟቸው ዘንድ ከትውልድ ወደ ትውልድም ጥቅም እንዲሆንላቸው፣ ሁሉንም ነገሮች እያባዛ፣ እየመረጠ፣ እና እያገኘ ለብዙ ጊዜ ይጓዝ። አሜን።