ክፍል ፻፲፫
በመጋቢት ፲፰፻፴፰ (እ.አ.አ.)፣ በፋር ዌስት፣ ምዙሪ ወይም አካባቢ ስለ ኢሳይያስ ፅሁፎች አንዳንድ መልሶች በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰጠበት።
፩–፮፣ የእሴይ ግንድ፣ ከዚያም የሚመጣው በትር፣ እና የእሴይ ስርም ምን እንደሆኑ ተገልጸዋል፤ ፯–፲፣ በፅዮን የተበተኑት ቅሪቶች ለክህነት ስልጣን መብት አላቸው እና ወደ ጌታ እንዲመለሱም ተጠርተዋል።
፩ በኢሳይያስ ፲፩ኛ ምእራፍ በ፩ኛ፣ ፪ኛ፣ ፫ኛ፣ ፬ኝ፣ እና ፭ኛ አንቀጾች ውስጥ የተነገረለት የእሴይ ግንድ ማን ነው?
፪ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፥ ይህም ክርስቶስ ነው።
፫ በኢሳይያስ ፲፩ኛ ምእራፍ በአንደኛው አንቀፅ ውስጥ ከእሴይ ግንድ እንደሚመጣ የተነገረለት በትር ምንድን ነው?
፬ እነሆ፣ ጌታ እንዲህ ይላል፥ ይህም በከፊል የእሴይ ተወላጅ እና የኤፍሬም ወይም የዮሴፍ ቤት አባል የሆነው፣ በእርሱም ላይ ብዙ ሀይል ያረፈበት የክርስቶስ እጆች አገልጋይ የሆነው ነው።
፭ በኢሳይያስ ፲፩ኛ ምእራፍ ፲ኛ አንቀፅ ውስጥ የተነገረለት የእሴይ ስር ምንድን ነው?
፮ እነሆ፣ ጌታ እንዲህ ይላል፣ ይህም ለምልክት እና በመጨረሻዎቹ ቀናትም ህዝቤን ለመሰብሰብ፣ ክህነትና የመንግስት ቁልፎች በመብት የእርሱ የሆነው የእሴይ፣ እንዲሁም የዮሴፍ ዘር ነው።
፯ የኢላየስ ሂግቢ ጥያቄዎች፥ በኢሳይያስ ፶፪ኛ ምእራፍ ፩ኛ አንቀጽ ውስጥ ፅዮን ሆይ፣ ኃይልሽን ልበሺ የሚለው ትእዛዝ ምን ማለቱ ነው—እና ኢሳይያስስ የሚያመለክተው የትኞቹን ህዝቦች ነው?
፰ የሚጠቁመውም እግዚአብሔር በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚጠራቸው፣ ፅዮንን ዳግም ለማምጣትና እስራኤልን ለማዳን ክህነት መያዝ ስላለባቸው ስለእነርሱ ነው፤ እና ኃይሏን መልበሷም ፅዮን በዘር መብት ያላትን የክህነት ባለስልጣንነትን መልበሷ ሲሆን፤ ደግሞም ወደአጣችው ሀይል መመለሷ ነው።
፱ ፅዮን ከአንገት እስራት ስለመፈታቷ ምን እንረዳላን፤ ፪ኛው አንቀፅ?
፲ መረዳት ያለብን የቀሩት ተባእቶች ከወደቁበት ወደ ጌታ እንዲመለሱ በጥብቅ እንዲበረታቱ ነው፤ ይህንም ካደረጉ፣ የጌታ ቃል ኪዳንም እንደሚናገራቸው፣ ወይም ራዕይን እንደሚሰጣቸው ነው። ፮ኛ፣ ፯ኛ፣ እና ፰ኛ አንቀፅን ተመልከቱ። የአንገቷም እስራት ያለባት የእግዚአብሔር እርግማን፣ ወይም በአህዛብ መካከል የእስራኤል ቅሪቶች በመበተናቸው የደረሰባቸው ጉዳት ነው።