ክፍል ፺፱
በነሀሴ ፳፱፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በሀይረም ኦሀዮ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ለጆን መርዶክ የተሰጠ ራዕይ። ባለቤቱ ጁሊያ ክላፕ በሚያዝያ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.) ከሞተች በኋላ፣ እናት የሌላቸው ልጆቹ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር እየኖሩ ሳሉ፣ ከአንድ አመት በላይ፣ ጆን መርዶክ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።
፩–፰፣ ጆን መርዶክ ወንጌልን እንዲሰብክ ተጠራ፣ እና እርሱን የሚቀበሉትም ጌታን ይቀበላሉ እና ምህረትንም ያገኛሉ።
፩ እነሆ፣ ለአገልጋዬ ጆን መርዶክ ጌታ እንዲህ ይላል—ወደ ምስራቅ ሀገሮች ከቤት ወደ ቤት፣ ከመንደር ወደ መንደር፣ እና ከከተማ ወደ ከተማ ዘለአለማዊ ወንጌሌን በዚያ ለሚኖሩት፣ በስደት እና በክፋት መካከል እያወጅህ እንድትሄድ ተጠርተሀል።
፪ እና የሚቀበልህም ይቀበለኛል፤ እና በእኔ ቅዱስ መንፈስ መገለጥ ቃሌን ለማወጅ ሀይል ይኖርሀል።
፫ እናማንም እንደ ትንሽ ልጅ የሚቀበልህም፣ መንግስቴን ይቀበላል፤ እነርሱም ብፁዓን ናቸው፥ ምህረት ያገኛሉና።
፬ እና ማንም አንተን የሚቃወም ከአባቴ እና ከቤቱ ይወገዳል፤ እና በእግረ መንገድህ በእነርሱም ላይ ምስክር ይሆን ዘንድ በተሰወሩ ስፍራዎች እግሮችህን ታጸዳለህ።
፭ እነሆ እና አስተውል፣ በመጽሐፍም ጥራዝ እንደ ተጻፈው፣ በእኔ ላይ ከፅድቅ በመራቅ ክፉ ሥራቸው ሁሉ እወቀሳቸው ዘንድ፣ ለፍርድ በቶሎ እመጣለሁ።
፮ አሁንም፣ እውነት እልሀለሁ፣ ልጆችህን እስክታስተዳድር እና በመልካም ወደ ፅዮን ኤጲስ ቆጶስ እስኪላኩ ድረስ እንድትሄድ ፍቃዴ አይደለም።
፯ እና ከጥቂት አመታት በኋላ፣ በእኔ የምትሻ ከሆነ፣ ውርስህን ለመቀበል ወደ መልካሚቱ ምድር መሄድ ትችላለህ፤
፰ አለበለዚያ እስከምትወሰድ ድረስ ወንጌሌን በማወጅ ትቀጥላለህ። አሜን።