ክፍል ፹፫
በሚያዝያ ፴፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በእንድፐንደንስ ሚዙሪ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህን ራዕይ የተቀበለው ነቢዩ ከወንድሞች ጋር ለመምከር እንደተቀመጠ ነው።
፩–፬፣ ሴቶች እና ልጆች በባሎቻቸው እና በአባቶቻቸው የመደገፍ መብት አላቸው፤ ፭–፮፣ ባልቴቶች እና የሙት ልጆች በቤተክርስቲያኗ ላይ የመደገፍ መብት አላቸው።
፩ በእውነትም፣ ስለሴቶች እና ስለልጆች፣ ባሎቻቸውን እና አባቶቻቸውን ስላጡት የቤተክርስቲያኗ አባላት፣ ቤተክርስቲያኗ ካላት ህግጋት በተጨማሪ ጌታ እንዲህ ይላል፥
፪ ሴቶች፣ ባሎቻቸው እስከሚወሰዱ ድረስ፣ በባሎቻቸው የመደገፍ መብት አላቸው፤ እናም የሚተላለፉ ሆነው እስካልተገኙ ድረስ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ህብረት ይኖራቸዋል።
፫ እናም ታማኝ ካልሆኑም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ህብረት አይኖራቸውም፣ ነገር ግን በምድር ህግ መሰረት በውርሳቸው ላይ ለመቆየት ይችላሉ።
፬ ለእድሜ እስኪደርሱ ድረስ ሁሉም ልጆች በወላጆቻቸው ላይ የመደገፍ መብት አላቸው።
፭ እናም ከዚያም በኋላ፣ ወላጆቻቸው ለውርስ የሚሰጧቸው ከሌላቸው፣ በቤተክርስቲያኗ ላይ፣ ወይም በሌላ አባባል በጌታ ጎተራ ላይ መብት አላቸው።
፮ እናም ጎተራውም በቤተክርስቲያኗ ቅድስና ይጠበቃል፤ እናም ባልቴቶች እና የሙት ልጆችም፣ እናም ድሆች፣ ይረዳሉ። አሜን።