ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፮


ክፍል ፻፮

በህዳር ፳፭፣ ፲፰፻፴፬ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህ ለኦሊቨር ካውድሪ ታላቅ ወንድም ለሆነው ለዋረን ካውድሪ የተሰጠ ራዕይ ነው።

፩–፫፣ ዋረን ኤ ካውድሪ በሚኖርበት አካባቢ ቀዳሚ መሪ እንዲሆን ተጠርቷል፤ ፬–፭፣ ዳግም ምፅዓት የብርሀን ልጆችን እንደ ሌባ አይደርስባቸውም፤ ፮–፰፣ የቤተክርስቲያኗ ታማኝ አገልጋይነት ታላቅ በረከቶች ይከተሉታል።

አገልጋዬ ዋረን ኤ ካውድሪ በፍሪደም እና በአካባቢዋ ምድር ውስጥ በቤተክርስቲያኔ እንደ ሊቀ ካህናት አመራር እንዲመደብ እና እንዲሾም ፍቃዴ ነው።

ዘለዓለማዊ ወንጌሌንም ይስበክ፣ እና በራሱ ስፍራ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠገቡ በሚገኙት የግዛት ክፍሎችም ድምጹን ከፍ ያድርግና ህዝብን ያስጠንቅቅ፤

እና መንግስተ ሰማያትንና ፅድቁንም በትህትና በመፈለግ፣ በምሰጠው በዚህ ከፍተኛ እና ቅዱስ ጥሪም ጊዜውን ሁሉ መስዋዕት ያድርግ፣ እና አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ይጨመሩለታል፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና።

ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ የጌታ መምጣት ቀርቦአል፣ እና ሌባ በሌሊት እንደሚመጣም በአለም ላይ ይደርስል—

ስለዚህ፣ የብርሀን ልጆች ትሆኑ ዘንድም ወገባችሁን አጥብቁ፣ እና ያም ቀን በሌሊት እንደ ሌባ አይደርስባችሁም

ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ዋረን ለመንግስቴ በትር ሲሰግድና እራሱን ከተንኮለኞች ሰዎች ሲለይ በሰማይ ደስታ ነበር።

ስለዚህ፣ አገልጋዬ ዋረን የተባረከ ነው፣ ምህረት እሰጠዋለሁና፤ እና ልቡ ግብዝነት ቢኖርበትም፣ በፊቴ ትሁት እስከሆነ ድረስ ከፍ አደርገዋለሁ።

የሚቆምበትም ጸጋ እና ማረጋገጫም እሰጠዋለሁ፤ ታማኝ ምስክርና ለቤተክርስቲያኗም ብርሀን ሆኖ ቢቀጥል በአባቴ ቤት አክሊል አዘጋጅቼለታለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።