አስተዳደሪያዊ አዋጅ ፩
መፅሐፍ ቅዱስ እና መፅሐፈ ሞርሞን እንደሚያስተምሩት፣ እርሱ ካላወጀበት በስተቀር አንድ ሚስት ብቻ ማግባት የእግዚአብሔር መሰረታዊ መርሆ እንደሆነ ያስተምራሉ (፪ ሳሙኤል ፲፪፥፯–፰ እና ያዕቆብ ፪፥፳፯፣ ፴ ተመልከቱ)። ለጆሴፍ ስሚዝ ከተሰጠ ረዕይ በኋላ፣ የብዛት ሚስቶች ማግባት ልምድ በቤተክርስቲያኗ በ፲፰፻፵ (እ.አ.አ.) አመታት መጀመሪያ ላይ ተመስርቶ ነበር (ክፍል ፻፴፪ን ተመልከቱ)። ከ፲፰፻፷ እስከ ፲፰፻፹ (እ.አ.አ.) አመታት፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ይህን የሀይማኖት ልምድ ህገ ወጥ የሚያደርጉ ህግጋትን መሰረተ። በመጨረሻም ህግጋቱ ትክክለኛ እንደሆኑ የዩ.ኤስ. ከፍተኛ ፍርድ ቤት አረጋገጠ። ራዕይን ከተቀበሉ በኋላ፣ ፕሬዘደንት ዊልፈርድ ዉድረፍ የሚቀጥለውን መግለጫ ሰጡ፣ ይህም በቤተክርስቲያኗ እንደ ስልጣንና እንደሚያስተሳስር በጥቅምት ፮፣ ፲፰፻፺ (እ.አ.አ.) ተቀባይነትን አገኘ። ይህም ለቤተክርስቲያኗ የብዛት ሚስቶች የማግባት ልምድ መጨረሻ ሆነ።
ለሚመለከተው ሁሉ፥
የዩታ ኮሚሲዮን በቅርቡ በአገር ውስጥ ጸሀፊ መግለጫ ውስጥ የብዙ ጋብቻ ስርዓቶች እንደሚፈጸሙ እና ባለፈው ሰኔ ወይም ባለፈው አመት አርባ ተመሳሳይ ጋብቻዎች በዩታ ውስጥ እንደተደረጉ፣ ደግሞም በህዝባዊ ንግግሮች የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ካንድ ሚስት በላይ የማግባት ልምድ እንዲቀጥል አስተምረዋል፣ አበረታትተዋል፣ እና ገፋፍተዋል የሚል ለፖለቲካ አላማዎች በብዛት የታተሙ ወረቀቶች ከሶልት ሌክ ስቲ ተልከው ነበር—
እኔ፣ ስለዚህ፣ እንደ ኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፕሬዘደንት በአፅኖት፣ እነዚህ ክሶች ሀሰት እንደሆኑ እገልጻለሁ። ከአንድ ሚስት በላይ ማግባትን ወይም ጋብቻን ማብዛትን እያስተማርን ወይም ማንም ሰው ወደዚህ ልምድ እንዲገባም እየፈቀድን አይደለም፣ እና አርባ ወይም ማንኛቸውም የብዙ የጋብቻ ስርዓቶች በዚህ ጊዜ በቤተመቅደሳችን ውስጥ ወይም በግዛቱ ማንኛውም ስፍራ እየተከናወነ እንዳልሆነም እመሰክራለሁ።
በጸደይ ፲፰፻፹፱ (እ.አ.አ.) በሶልት ሌክ ስቲ መንፈሳዊ ስጦታ ቤት ውስጥ ጋብቻ እንደተፈጸመ የሚባልበት አንድ ጉዳይ ተመዝግቦ ነበር፣ ነገር ግን ያንን ስነ ስርዓት ማን እንደፈጸመው ለማወቅ አልቻልኩም፤ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው ምንም ነገር እኔ በማላውቅበት ነበር። በመንፈሳዊ ስጦታ ቤት ውስጥ ተደረገ ስለተባለውም ያለመዘግየት በእኔ ትእዛዜ ፈርሷል።
እነዚህም ህግጋት በመጨረሻው አማራጭ ፍርድ ቤት ህገ መንግስታዊ እንደሆነ የፈረዱበት፣ ብዙ ሚስቶችን ስለማግባት ኮንግረሥ ባሳለፋቸው ህግጋት መሰረት፣ እነዚህን ህግጋት ለማክበርና በምመራቸው ከቤተክርስቲያኗ አባላት ጋር ያለኝን ተፅዕኖ በመጠቀም እንደእኔ እንዲያደርጉ ለማድረግ ያለኝን ፈቃድ በዚህ እገልጻለሁ።
በተጠቀሰው ጊዜ በቤተክርስቲያኗ እኔ ወይም አብሬአቸው ከምሰራው በምናስተምራቸው ውስጥ ብዙ ሚስቶችን ማግባትን የሚያበረታታ ወይም እንደሚያዳብር ሊተረጎም የሚችል ምንም የለም፤ እና የቤተክርስቲያኗ ማንም ሽማግሌ እንደዚህ አይነት ትምህርትን እንደሚሰጥ የሚመስል ቋንቋዎችን በተጠቀመ ጊዜ፣ ወዲያው ተገሰጿል። አሁንም ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን ምክሬ በምድር ህግ የተወገደውን ምንም ጋብቻ ውል ማስገባትን እንዲያቆሙ እንደሆነ በህዝብ ዘንድ አውጃለሁ።
ዊልፈርድ ዉድረፍ
የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ
ቤተክርስቲያን ፕሬዘደንት።
ፕሬዘደንት ሎሬንዞ ስኖው የሚቀጥሉትን አቀረቡ፥
“ዊልፈርድ ዉድረፍን እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ፕሬዘደንት፣ እና በዚህ ጊዜ የማተም ስነስርዓቶችን ቁልፎች በምድር ላይ እንደያዘ ሰው በመቀበል፣ በመስከረም ፳፬ ቀን ፲፰፻፺ (እ.አ.አ.) ቀን እንድንሰማው የተነበበውን ህዝባዊ መግለጫን ለመስጠት ሙሉ ስልጣን እንዳላቸው በመቀበል፣ በአጠቃላይ ጉባኤ እንደተሰበሰብነው ቤተክርስትያን ይህን ብዙ ሚስቶች ማግባትን በሚመለከት ያወጁት አስገዳጅ እና በስልጣን እንደሆነም እንቀበላለን።”
ሶልት ሌክ ስቲ፣ ዩታ፣ ጥቅምት ፮፣ ፲፰፻፺ (እ.አ.አ.)።
ከፕሬዘደንት ዊልፈርድ ዉድረፍ
ስለህዝባዊ መግለጫ ከሰጡት
ሶስት ንግግሮች የተወሰደ ምንባብ
ጌታ እኔን ወይም በዚህች ቤተክርስቲያን እንደ ፕሬዘደንት የሚቆም ማንንም ሰው እናንተን ወደ ስህተት እንዲመራ አይፈቅድም። ይህም በአላማው ውስጥ አይደለም። ይህም በእግዚአብሔር ልብ አይደለም። ይህን ብሞክር፣ ጌታ ከስፍራዬ ያስወጣኛል፣ እና የሰዎች ልጆችን ከእግዚአብሔር ቃላት እና ከሀላፊነታቸው እንዲሳሳቱ የሚጥረውንም እንዲሁ ያደርጋል። (የቤተክርስቲያኗ ሰላሳ አንደኛው የአጠቃላይ ጉባኤ፣ ጥቅምት ፮ ቀን ፲፰፻፺ [እ.አ.አ.]፣ ሶልት ሌክ ስቲ፣ ዩታ። በDeseret Evening News [ደዘረት የምሽት ኮኮብ ዜና] ሀተታ፣ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፲፰፻፺፣ ገፅ ፪።)
ማንም ይኑር ወይም ይሙት፣ ወይም ማንም ይህችን ቤተክርስቲያን ለመምራት መጠራቱ አስፈላጊ አይደለም፣ በሁሉም ገዢ እግዚአብሔር መነሳሳት መምራት አለባቸው። ይህን በዚህ መንገድ ባያደርጉ፣ ሊያደርጉትም አይችሉም…።
አንዳንድ፣ እና በጣም አስፈላጊ የሆኑትንም፣ ራዕዮችን ባለፉት ጊዜያት አግኝቻለሁ፣ እና ጌታ ምን እንዳለኝም እነግራችኋለሁ። ህዝባዊ መግለጫ ስለተባለው ታስቡበት ዘንድ ላድርግ…።
ጌታ የኋለኛውን ቀን ቅዱሳንን ጥያቄ እንድጠይቅ ነገረኝ፣ እና የምላቸውን ቢሰሙና የምጠይቃቸውንም ቢመልሱ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ እና ሀይል ሁሉም እንደ አንድ ይመልሳሉ፣ እና ስለዚህ ጉዳይም በአንድነት ያምናሉ በማለትም ነገረኝ።
ጥያቄውም ይህ ነው፥ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መከታተል ያለባቸው የጥበብ መንገድ የትኛው ነው—የቤተመቅደሶችን ሁሉ ማጣትን እና መወረስን፣ እና በእነርሱም ውስጥ ለህያው እና ለሙታን የሚደረጉትን ስርዓቶችን ማቆምን፣ እና የቤተክርስቲያኗ ቀዳሚ አመራርና አስራ ሑለት፣ እና የቤተሰብ መሪዎች መታሰርን፣ እና የህዝብ (ይህን ልምድ የሚያቆሙትን ሁሉ) የግለሰብ ንብረቶች መወሰድን ክፍያ በማድረግ የሀገር ህግጋትና ስልሳ ሚልዮን የሚቃወሙትን ብዙ ሚስት የማግባት ልምድን ለመቀጠል መሞከርን፤ ወይም ይህን መሰረታዊ መርሆ በማክበር ከደረሰብን እና ከተሰቃየናቸው በኋላ፣ በህጉ ታዛዥ በመሆን እና ይህን ልምድ በማቆም፣ እና ይህን በማድረግም ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ እና አባቶችን ህዝብን እንዲያስተምሩ እና የቤተክርስቲያኗን ሀላፊነታቸውን እንዲያከናውኑ በቤት በማቆየት፣ እና ደግሞም የወንጌልን ስርዓቶችን ለህያው እና ለሙታን ለማድረግ እንዲችሉ ቤተመቅደሶችን በቅዱሳን እጆች ውስጥ እንዲቀሩ በማድረግ ነውን?
ጌታ በመግለጫ እና በራዕይ ይህን ልምድ ባናቆም ምን እንደሚደርስ አሳይቶኛል። ይህንን ካላቆምን፣ ማናችሁም በዚህ በሎጋን ቤተመቅደስ ላሉት ለማንኛውም ሰው ምንም ጥቅም ባልሰጣችሁ ነበር፤ በፅዮን ምድር ውስጥ ሁሉም ስነ ስርዓቶች በቆሙ ነበር። በእስራኤልም ግራ መግባት በነገሰ ነበር፣ እና ብዙ ሰዎችም እስረኞች በሆኑ ነበር። ይህም ችግር በቤተክርስቲያኗ ሙላት ላይ ይመጣ ነበር፣ እና ይህን ልምድ ለማቆምም እንገደድ ነበር። አሁን፣ ጥያቄውም በዚህ መንገድ ይቁም፣ ወይስ ጌታ በገለጸልን መንገድ፣ እና ነብያቶቻችንን እና ሐዋሪያቶቻችንን እና አባቶችን በነጻነት እንተዋቸው እና ሙታን እንዲድኑም ቤተመቅደሳችንን በህዝብ እጆች ውስጥ እንተዋቸው ነው። በዚህ ህዝብ አማካይነት በመንፈስ አለም ውስጥ ካለው የእስር ቤት ታላቅ ቁጥር ያላቸው ድነዋል፣ እና ስራው ይቀጥል ወይስ ይቁም? ይህን ጥያቄ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን ፊት አስቀምጣለሁ። ለራሳችሁ መፍረድ አለባችሁ። ለራሳችሁ እንድትመልሱበት እፈልጋችኋለሁ። እኔ አልመልሰውም፤ ነገር ግን የወሰድነውን መንገድ ባንወስድ ኖሮ ይህም እንደ ህዝብ ልንገኝበት የምንችልበት ሁኔታ ነው እላችኋለሁ።
…አንድ ነገር ባይደረግ ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችልም አይቼ ነበር። ይህም መንፈስ በእኔ ላይ ለረዥም ጊዜ ኖሮኝም ነበር። ነገር ግን ይህን ለማለት እፈልጋለሁ፥ የእግዚአብሔር ሰማይ ያደረግሁትን እንዳደርግ ባያዘኝ ኖሮ፣ ቤተመቅደሶችን ሁሉ ከእጆቻችን አስወጣ ነበር፤ ራሴም ወደ እስር ቤት፣ እና እያንዳንዱንም ሰው ወደዚያ እንዲሄድ አደርግ ነበር፤ እና ያን እንዳደርግ የታዘዝኩበት ሰዓት ሲመጣ፣ ይህም ለእኔ ግልፅ ነበር። ከጌታም ፊት ሄድኩ፣ እና ጌታ እንድፅፍ የነገረኝን ጻፍኩ…።
ይህን ከእናንተው ዘንድ የምተወው እናንት እንድታሰላስሉበት እና እንድታስቡበት ነው። ጌታ ከእኛ ጋር እየሰራ ነው። [ካሽ ካስማ ጉባኤ፣ ሎገን፣ ዩታ፣ እሁድ፣ ህዳር ፩ ቀን ፲፰፻፺፩ (እ.አ.አ.)። በDeseret Weekly [የደዘረት ሳምንታዊ ዜና] ሀተታ ውስጥ፣ ህዳር ፲፬ ቀን ፲፰፻፺፩ (እ.አ.አ.)።]
አሁን የተገለጸልኝን እና በዚህ ነገር የእግዚአብሔር ልጅ ምን እንደፈጸመ እነግራችኋለሁ…። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ፣ ህዝባዊ መግለጫው ባይሰጥ ኖሮ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በሆኑ ነበር። ስለዚህ፣ በአዕምሮው ውስጥ ላሉት አላማዎች የእግዚአብሔር ልጅ ያንን ነገር ለቤተክርስቲያኗ እና ለአለም እንዲቀርቡ ፈቃዱ ነበር። ጌታ የፅዮንን መመስረት አውጇል። የዚህ ቤተመቅደስ መፈጸምን አውጇል። የህያው እና የሙታን ደህንነት በእነዚህ ተራሮች ሸለቆዎችም ውስጥ መሰጠት እንዳለባቸውም አውጇል። እና ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ያወጀውን ዲያብሎስ ሊያሰናክል አይችልም። ያንን ለመረዳት ከቻላችሁ፣ ያም ለዚህ ቁልፍ ነው። (በሚያዝያ ፲፰፻፺፫ [እ.አ.አ.] በሶልት ሌክ ቤተመቅደስ መመረቂያ ስድስተኛ ስብሰባ ላይ ከተሰጠው ንግግር። የመመረቂያው ስብሰባ የተተነበየበት ፅሑፍ፣ ፅሑፋዊ ሰነዶች፣ የቤተክርስቲያን ታሪክ ዲፓርትመንት፣ ሶልት ሌክ ስቲ፣ ዩታ።)