“የቤተሰባችሁን የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለማሻሻል የሚረዱ ሀሳቦች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 2021 (እ.አ.አ) [2020 (እ.አ.አ)]
“የቤተሰባችሁን የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለማሻሻል የሚረዱ ሀሳቦች፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ 2021 (እ.አ.አ)
የቤተሰባችሁን የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለማሻሻል የሚረዱ ሀሳቦች
መደበኛ የቤተሰብ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ቤተሰባችሁ ወንጌልን እንዲማሩ ለመርዳት ሀይለኛ መንገድ ነው። እንደ ቤተሰብ በየስንት ጊዜ እና ለምን ያህል ጊዜ ማንበባችሁ ያላሰለሰ ጥረት የማድረጋችሁን ያህል አስፈላጊ አይደለም። የቅዱሳት መጻህፍት ጥናትን የቤተሰባችሁ ህይወት አስፈላጊ ክፍል ስታደርጉት፣ የቤተሰባችሁ አባሎች እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡ እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀርቡ እና በቃሉ መሠረት ምስክርነታቸውን እንዲገነቡ ትረዷቸዋላችሁ።
የሚቀጥሉትን ጥያቄዎች አስቡባቸው፥
-
የቤተሰብ አባላትን በራሳቸው ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑ እንዴት ማበረታታት ትችላላችሁ?
-
የቤተሰብ አባላቶች የሚማሩትን እንዲያጋሩ ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
-
በትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ውስጥ የምትማሩትን መሰረታዊ መርሆዎች በዕለት ተዕለት ትምህርቶች ጊዜ እንዴት ማጉላት ትችላላችሁ?
ቤት ለወንጌል ትምህርት አመቺ ስፍራ መሆኑን አስታውሱ። በቤተክርስቲያን ክፍል ውስጥ በማይቻል መንገድ ወንጌልን በቤታችሁ ውስጥ መማር እና ማስተማር ትችላላችሁ። ቤተሰባችሁ ከቅዱሳት መጻህፍት እንዲማሩ ለመርዳት መንገዶችን ለመፍጠር አስቡ።
የተግባር ሃሳቦች
የቤተሰባችሁን የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለማጉላት የሚከተሉትን ሀሳቦች ተመልከቱ፥
ሙዚቃን ተጠቀሙ
በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የተማራችሁትን መሰረታዊ መርሆዎች የሚያጠናክሩ መዝሙሮች ዘምሩ። የተመረጡ መዝሙሮች ወይም የልጆች መዝሙር በእያንዳንዱ ሳምንታዊ ማውጫ ውስጥ ተዘርዝረዋል። በግጥሞቹ ውስጥ ስላሉት ቃላት ወይም ሐረጎች ጥያቄዎች መጠየቅ ትችላላችሁ። ከመዘመር በተጨማሪ፣ ቤተሰባችሁ ከመዝሙሮቹ ጋር የሚሄዱ ተግባሮችን ማከናወን ወይም ሌሎች ተግባሮችን በሚያከናውኑበት ጊዜ መዝሙሮቹን እንደ የበስተጀርባ ሙዚቃ ማዳመጥ ይችላሉ።
ትርጉም ያላቸው የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችን አጋሩ።
የቤተሰብ አባላት በግል ጥናታቸው ያገኟቸውን ለእነሱ ትርጉም የሰጧቸውን የቅዱሳት መጻህፍት ምንባቦች እንዲያካፍሉ ጊዜ ስጧቸው።
የራሳችሁን ቃላት ተጠቀሙ
ከምታጠኗቸው ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ምን እንደተማሩ በገዛ ቃላቸው እዲያብራሩ የቤተሰብ አባሎቻችሁን ጋብዟቸው።
ቅዱሳት መጻህፍትን ከሕይወታችሁ ጋር አመሳስሉ
የቅዱሳት መጻህፍትን ምንባብ ካነበባችሁ በኋላ፣ የቤተሰብ አባላት መልዕክቱ በህይወታቸው እንዴት ሊሰራ እንደሚችል እንዲያካፍሉ ጠይቋቸው።
ጥያቄ ጠይቁ
የቤተሰብ አባላት የወንጌልን ጥያቄ እንዲጠይቁ ጋብዙ፣ እናም ከዚያ ለጥያቄው መልስ ሊያግዙ የሚችሉ ጥቅሶችን በመፈለግ ጊዜአችሁን አሳልፉ።
የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅስ አሳዩ
ያገኛችሁትን ትርጉም ያለው ጥቅስ ምረጡ፣ እና የቤተሰብ አባላት ብዙውን ጊዜ በሚያዩበት ቦታ ላይ አስቀምጡት። ሌሎች የቤተሰብ አባላት አንድ የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅስ በመምረጥ በየተራ እንዲያሳዩ ጋብዙ።
የቅዱሳት መጻህፍት ዝርዝርን አዘጋጁ
እንደ ቤተሰብ በሚመጣው ሳምንት በጥልቀት መወያየት የምትፈልጉትን የተለያዩ ጥቅሶችን ምረጡ።
የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅሶችን በአዕምሮአችሁ በመያዝ አስታውሱ
ለቤተሰባችሁ ትርጉም ያለው የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብን ምረጡ፣ እና የቤተሰብ አባላቱ በየዕለቱ በመድገም ወይም የማስታወሻ ጨዋታ በመጫወት በአዕምሮአቸው በመያዝ እንዲያስታውሱ ጋብዙአቸው።
የምሳሌአዊ ነገሮችን ትምህርቶች አጋሩ
እንደ ቤተሰብ ከምታነቧቸው ምዕራፎች እና ጥቅሶች ጋር የሚዛመዱ ነገሮችን ፈልጉ። እያንዳንዱ ነገር በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ካሉት ትምህርቶች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ እንዲናገሩ የቤተሰብ አባላትን ጋብዙ።
ርዕሶችን ምረጡ
ቤተሰቡ አብሮ የሚያጠናውን ርዕስ የቤተሰብ አባላት ተራ በተራ እንዲመርጡ አድርጉ። በቅዱሳት መጻህፍት ምንባብ ውስጥ ስለ ርዕሶች መረዳጃ ለማግኘት፣ የርዕስ መመሪያን፣ የመፅሐፍ ቅዱስ መዝገብ ቃላትን፣ ወይም የቅዱሳት መጻህፍት መመሪያን (scriptures.ChurchofJesusChrist.org) ተጠቀሙ።
ስዕል ሳሉ
እንደ ቤተሰብ ጥቂት ጥቅሶችን አንድ ላይ አንብቡ፣ ከዚያ የቤተሰብ አባላቶች ካነበቡት ነገር ጋር የሚዛመድ አንድ ነገር እንዲስሉ ጊዜ ስጡአቸው። አንዳችሁ የሌላችሁን ስዕሎች ለመወያየት ጊዜ መድቡ።
ታሪኩን ተውኑ
አንድ ታሪክ ካነበባችሁ በኋላ የቤተሰብ አባላትን እንዲተውኑት ጋብዙ። ከዚያ በኋላ ታሪኩ በግል እና በቤተሰባችሁ ውስጥ ከሚገኙ ነገሮች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ተነጋገሩ።
ልጆችን ማስተማር
በቤተሰባችሁ ውስጥ ትትንሽ ልጆች ካሉ፣ እነሱን ለመማር የሚረዷቸው አንዳንድ ተግባራት እንደሚከተሉት ናቸው፥
ዘምሩ
በልጆች የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ያሉ መዝሙሮች እና ሙዚቃዎች ትምህርትን በኃይል ያስተምራሉ። በዚህ የጥናት ምንጭ ውስጥ ያሉ እያንዳንዱ ንድፍ የተጠቆሙ መዝሙሮችን ያካትታሉ። ከምታስተምሯቸው የወንጌል መሰረታዊ መርሆዎች ጋር የሚዛመዱ መዝሙሮችን የርዕሶች ማውጫን በልጆች የመዝሙር መጽሐፍ በስተጀርባ በማግኘት ለመጠቀም ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ የመዝሙሮቹን መልእክቶች በሕይወታቸው ላይ እንዲያዛምዱ እርዷቸው።
ታሪክን አድምጡ ወይም ተውኑ
ትትንሽ ልጆች ከቅዱሳት መጻህፍት፣ ከህይወታችሁ፣ ከቤተክርስቲያን ታሪክ፣ ወይም ከቤተክርስቲያን መጽሔቶች ውስጥ የሚገኙ ታሪኮችን ይወዳሉ። በትረካው ውስጥ እነርሱን ለማሳተፍ መንገዶችን ፈልጉ። እነርሱ ስዕሎችን ወይም ዕቃዎችን መያዝ፣ የሚሰሙትን በስዕል መልክ መሳል፣ ታሪኩን መተወን፣ ወይም ታሪኩን በመናገር መርዳት ይችላሉ። በምታጋሯቸው ታሪኮች ውስጥ ልጆቻችሁ የወንጌል እውነቶችን እንዲገነዘቡ እርዷቸው።
ቅዱሳት መጻህፍትን አንብቡ
ትትንሽ ልጆች በጣም ብዙ ማንበብ አይችሉም ይሆናል፣ ነገር ግን ከቅዱሳት መጻህፍት በመማር እነርሱ እንዲሳተፉ ለማድረግ ትችላላችሁ። በአንድ ጥቅስ፣ ቁልፍ ሐረግ ወይም ቃል ላይ ማተኮር ያስፈልጋችሁ ይሆናል።
ፎቶግራፍ ተመልከቱ ወይም ቪዲዮ እዩ
ከምትወያዩአቸው የወንጌል መሰረታዊ መርሆች ጋር ስለሚዛመድ ስእል ወይም ቪዲዮ ጥያቄዎችን ጠይቁ። ለምሳሌ፣ እንደዚህ ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፣ “በዚህ ሥዕል ውስጥ ምን እየሆነ ነው? ምን ስሜት ይሰጣችኋል?” ስዕሎችን እና ቪዲዮዎችን ለመፈለግ፣ የወንጌል ቤተ መጻሕፍት አፕልኬሽን፣ የወንጌል ማህደረ መረጃ ቤተ መጻሕፍት በChurchofJesusChrist.org፣ እና children.ChurchofJesusChrist.org ጥሩ ቦታዎች ናቸው ።
ፍጠሩ
ልጆች ከሚማሩት ታሪክ ወይም መሠረታዊ መርሆ ጋር የሚዛመድ አንድ ነገር መገንባት፣ መሳል ወይም ቀለም መቀባት ይችላሉ።
በምሳሌአዊ ነገር ትምህርቶች ውስጥ መሳተፍ
ቀለል ያሉ ነገሮች ምሳሌአዊ ትምህርት ልጆቻችሁ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነውን የወንጌል መርህ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል። ምሳሌአዊ ነገር ትምህርቶችን በምትጠቀሙበት ጊዜ፣ ልጆቻችሁ እንዲሳተፉበት የሚያስችሏቸውን መንገዶች ፈልጉ። እነሱ ከመመልከት ብቻ ሳይሆን በተሳትፎ ተሞክሮ የበለጠ ይማራሉ።
ሚና-መጫወት
ልጆች በእውነተኛ ህይወት ውስጥ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉትን ሁኔታዎች በሚና ሲጫወቱ፣ የወንጌል መሰረታዊ መርሆች በህይወታቸው እንዴት እንደሚሠሩ የበለጠ ለመረዳት ይችላሉ።
ተግባሮችን ደጋግሙ
ትትንሽ ልጆች ፅንሰ ሀሳቦችን ለመረዳት ደጋግመው መስማት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ለምሳሌ፣ በተለያዩ መንገዶች፣ እንዲሁም ከቅዱሳት መጻህፍት በማንበብ፣ በራሳችሁ ቃላት በማሳጠር፣ ልጆች ታሪኩን ለመናገር እንዲረዷችሁ በመፍቀድ፣ ታሪኩን እንዲተውኑ በመጋበዝ እና በመሳሰሉ ነገሮች፣ አንድ የቅዱሳት መጻህፍትን ታሪክ ደጋግማችሁ ለመካፈል ትችላላችሁ።
ከግል የእድገት ግቦቻቸው ጋር ግንኙነቶችን ማድረግ
የቤተሰብ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለወጣቶች እና ልጆች ለመንፈሳዊ፣ አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ማህበራዊ ዕድገታቸው ግብ ለማውጣት መነሳሳትን ሊሰጥ ይችላል (ሉቃስ 2፥52 ይመልከቱ)።
ወጣቶችን ማስተማር
በቤተሰባችሁ ውስጥ ወጣቶች ካሉ፣ ለመማር የሚረዷቸው አንዳንድ ተግባራት እንደሚከተሉት ናቸው፥
እንዲያስተምሩ ጋብዟቸው
በተለምዶ አንድ ነገርን ስንሰማ ሳይሆን በምናስተምርበት ጊዜ ነው በደንብ የምንማረው። ወጣቶቻችሁ ስለቅዱሳት መጻህፍት የቤተሰብ ውይይትን እንዲመሩ እድል ስጧቸው።
ከሀይማኖት ትምህርት ቤት ጋር ግንኙነቶችን ማድረግ
በዚህ ዓመት የሀይማኖት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ትምህርት እና ቃል ኪዳኖችን ያጠናሉ። ወጣቶቻችሁ በሀይማኖት ትምህርት ቤት የሚያጠኑ ከሆኑ፣ እዚያ የሚማሩትን እንዲያካፍሉ ጋብዟቸው።
ቅዱሳት መጻህፍትን በራስ ማመሳሰል
አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ያሉት ትምህርት እና መርሆዎች ከህይወታቸው ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማየት ይቸግራቸዋል። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ያሉ ታሪኮች እና ትምህርቶች በቤት፣ በትምህርት ቤት ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ከሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንዲገነዘቡ እርዳታ ስጧቸው።
ማሰላሰልን የሚያበረታቱ ጥያቄዎችን መጠየቅ
ብዙ ወጣቶች ቅዱሳን መጻሕፍት የሚናገሩትን ደጋግሞ ከማለት ይልቅ ስለ ቅዱሳት መጻህፍት ሀሳባቸውን እና ስሜታቸውን እንዲገልጹ ለሚያስችሏቸው ጥያቄዎች ጥሩ ምላሽ ይሰጣሉ። ለምሳሌ፣ እንዲህ ለመጠየቅ ትችላላችሁ፣ “በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጌታ ምን ያስተምራችኋል?” ወይም “ይህ መገለጥ በ1830 (እ.አ.አ) አካባቢ ለነበሩት ቅዱሳን ትርጉም የነበረው ለምን ይመስላችኋል?”
ከግል የእድገት ግቦቻቸው ጋር ግንኙነቶችን ማድረግ
የቤተሰብ የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ለወጣቶች እና ልጆች ለመንፈሳዊ፣ አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና ማህበራዊ ዕድገታቸው ግብ ለማውጣት መነሳሳትን ሊሰጥ ይችላል (ይመልከቱ፥ ሉቃስ 2፥52)።
ጥያቄዎቻቸውን ተቀባይ ሁኑ
ከአንድ በወጣት የሚነሳ ጥያቄ እውነትን ለመጋራት እና ከልብ እርሱ ወይም እርሷ ለማወቅ በሚፈልገውንን ርዕስ ላይ መረዳትን ለማግኘት ውድ አጋጣሚ ነው። ምንም እንኳን ከውይይቱ ርዕስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባይመስሉም፣ ጥያቄዎችን አትፍሩ ወይም አታስወግዷቸው። ሁሉም መልሶች ባይኖሯችሁም ችግር የለውም። ቤት በጋራ መልስ ለማግኘት ምቹ ስፍራ ነው።
ግንዛቤያቸውን እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው
በቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ውስጥ አስተዋፅኦ ለማበርከት ወጣቶች ልዩ አመለካከቶች እና ግንዛቤዎች አሏቸው። መንፈስ ስለ ቅዱሳት መጻህፍት ስለሚያስተምራቸው ነገር ለማወቅ ፍላጎት እንዳላችሁ አሳውቋቸው። ከግል ጥናታቸው ግንዛቤዎችን እንዲያጋሩ መጠየቅም ትችላላችሁ።
መለወጥ የምትችሉ ሁኑ
በቤተሰብ ቅዱሳት መጻህፍት ጥናት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆነ ወጣት ካላችሁ፣ ከእርሱ ወይም ከእሷ ጋር ለመገናኘት ሌሎች መንገዶችን ፈልጉ። ለምሳሌ፣ በውይይቶቻችሁ ውስጥ የወንጌል ርዕስን ለማምጣት ትችላላችሁን ወይም ስብከት ወይም ከመጠን በላይ በማይመስል መንገድ ትርጉም ያለው የቅዱሳት መጻህፍት ጥቅስን ማጋራት ትችላላችሁን? የቅዱሳት መጻህፍት ጥናት በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አንድ አይነት መምሰል የለበትም። አንዳንድ ልጆች ቅዱሳት መጻሕፍትን አንድ በአንድ በማጥናት የተሻለ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ። የምትጸልዩ ሁኑ እና የመንፈስን ምሪትን ተከተሉ።