“ሰኔ 26–ሐምሌ 2 (እ.አ.አ)። ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ ዮሐንስ 20–21፦ ‘ተነሥቶአል’” ኑ፣ ተከተሉኝን—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ አዲስ ኪዳን 2023 (እ.አ.አ) [2022 (እ.አ.አ)]
“ሰኔ 26–ሐምሌ 2 (እ.አ.አ)። ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ ዮሐንስ 20–21፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፦ 2023 (እ.አ.አ)
ሰኔ 26–ሐምሌ 2 (እ.አ.አ)
ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ ዮሐንስ 20–21
“ተነስቷል”
ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ እና ዮሐንስ20–21ን በጸሎት መንፈስ፣ በክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት ያላችሁን ደስታ በማሰላሰል አንብቡ። የዚህን ክስተት ምስክርነታችሁን በመስማት ማን ሊባረክ ይችላል?
ያሳደረባችሁን ስሜት መዝግቡ
ለብዙ ታዛቢዎች፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሞት የአስደናቂ ሕይወት አስቂኝ መጨረሻ መስሎ ሊታይ ይችላል። አልዓዛርን ከሞት ያስነሳው ይህ ሰው አልነበረም? እሱ በየጊዜው የፈሪሳውያን የግድያ ማስፈራሪያዎችን አልተቋቋመምን? እሱ ዓይነ ስውርነትን፣ የሥጋ ደዌን እና ሽባን የመፈወስ ኃይልን አሳይቷል። ነፋሱና ባሕሩ ታዘዙለት። እርሱ ግን “ተፈጸመ” (ዮሐንስ 19፥30) ብሎ በማወጅ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ እዚያው ነበር። በሹፈት ቃላቶች ውስጥ አንዳንድ ልባዊ መደነቆች ነበሩ “ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም” (ማቴዎስ 27፥42)። ነገር ግን የኢየሱስ ሞት የታሪኩ መጨረሻ እንዳልሆነ እናውቃለን። የመቃብሩ ዝምታ ጊዜያዊ፣ የክርስቶስ የማዳን ሥራ ገና መጀመሩን እናውቃለን። እርሱ ዛሬ በሕያዋን መካከል ነው እንጂ “ከሙታን መካከል” አይደለም (ሉቃስ 24፥5)። ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” (ማቴዎስ 28፥19–20) ሁልጊዜ ከእነሱ ጋር እንደሚሆን የገባውን ቃል በመተማመን “በአሕዛብ ሁሉ” ውስጥ ወንጌልን ስለሚሰብኩ ትምህርቶቹ ዝም ሊሰኙ አይችሉም።
ለግል የቅዱሳን መጻህፍት ጥናት ሃሳቦች
ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ ዮሐንስ 20
ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን አድርጓል።
በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ስለ አንድ በጣም አስፈላጊ ክስተት ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን ታነባላችሁ። በምታነቡበት ጊዜ፣ እራሳችሁን በትንሳኤ ዙሪያ ያሉትን ክስተቶች በተመለከቱ ሰዎች ቦታ አስቀምጡ። ከእነሱ ተሞክሮዎች ምን ትማራላችሁ?
እናንተ ስለ አዳኙ ትንሳኤ ስታነቡ ምን ይሰማችኋል? እንዴት ተጽዕኖ እንዳሳደረ አስቡ—ለሕይወት ያላችሁን አመለካከት፣ ግንኙነቶቻችሁን፣ በክርስቶስ እና በሌሎች የወንጌል እውነቶች ላይ ያላችሁን እምነት።
በተጨማሪም የመጽሃፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ትንሳኤ”፤ የወንጌል ርዕሶች፣ “ትንሳኤ፣” topics.ChurchofJesusChrist.orgን ተመልከቱ።
አዳኙ “ከእኔ ጋር [እንዲኖር]” መጋበዝ እችላለሁ።
ከሞት ከተነሳው አዳኝ ጋር የተገናኙትን ሁለቱ ተጓዥ ደቀ መዛሙርት ልምድን ስታነቡ፣ እንደ ክርስቶስ ተከታይነታችሁ ከልምዶቻችሁ ትይዩዎችን ፈልጉ። ዛሬ ከእሱ ጋር መራመድ እና ትንሽ “እንዲቆይ” መጋበዝ የምትችሉት እንዴት ነው? (ሉቃስ 24፥29)። በሕይወታችሁ ውስጥ የእርሱን መኖር እንዴት ታውቃላችሁ? የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊነት መንፈስ ቅዱስ በምን መንገድ ነው የመሰከርላችሁ?
በተጨማሪም “ከእኔ ጋር ቆይ መሽቷል፣” “ከእኔ ጋር ቆይ!፣” መዝሙሮች፣ ቁጥር 165–66ን ተመልከቱ።
ትንሣኤ የመንፈስ ከሥጋ ጋር በቋሚነት መገናኘት ማለት ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ዘገባዎች ትንሳኤ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድትረዱ ይረዳሉ። ለምሳሌ ሉቃስ 24፥36–43 እና ዮሐንስ 20 ላይ ስለተነሱ አካላት ምን እውነቶች ታገኛላችሁ? እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ማሰስ ትችላላችሁ ለምሳሌ፤ 1 ቆሮንቶስ 15፥35–44፤ ፊልጵስዩስ 3፥20–21፤ 3 ኔፊ 11፥13–15፤ ትምህርት እና ቃልኪዳኖች 88፥27–31፤ 110፥2–3፤ 130፥1፣ 22።
“ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው።”
አንዳንድ ሰዎች “ካላየሁ … አላምንም” እንዳለው ቶማስ ሊሰማቸው ይችላል (ዮሐንስ 20፥25)። በእናንተ አመለካከት ሳያዩ ማመን ምን በረከት ሊሆን ይችላል? (ዮሐንስ 20፥29ን ተመልከቱ)። በማታዩአቸው ነገሮች በማመናችሁ እንዴት እንደተባረካችሁ አስቡ። እሱን ባታዩትም እንኳ በአዳኙ ላይ እምነት እንዲኖራችሁ የሚረዳችሁ ምንድን ነው? “እውነት ስለሆኑት እና ስለማይታዩ ነገሮች” ያላችሁን እምነት እንዴት ማጠናከር ትችላላችሁ? (አልማ 32፥16–21፤ ኤተር 12፥6ን ተመልከቱ)። በኢየሱስ ክርስቶስ እንድታምኑ የረዳችሁ ልምዶችን መመዝገብ ወይም ለምታውቁት ሰው ለማጋራት አስቡ።
አዳኙ በጎቹን እንድመግብ ይጋብዘኛል።
በዮሐንስ 21 ላይ የተመዘገበውን አዳኙ ከሐዋርያቱ ጋር የነበረውን ግንኙነት በሉቃስ 5፥1–11፣ ላይ መረባቸውን እንዲተው ለመጀመርያ ጊዜ ካዘዘበት ጋር ማወዳደር አስደሳች ሊሆን ይችላል። ምን ተመሳሳይነቶች እና ልዩነቶች ታገኛላችሁ? ስለ ደቀመዝሙርነት ምን ግንዛቤዎችን ታገኛላችሁ?
በዮሐንስ 21፥15–17 ላይ አዳኙ ለጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት ለእናንተ እንዴት እንደሚሠሩ አስቡ። የጌታን በጎች ከማገልገል የሚያግዳችሁ ነገር አለን? ጌታ “ትወደኛለህ?” ብሎ ቢጠይቃችሁ ምላሻችሁምን ሊሆን ይችላል? ለጌታ ያላችሁን ፍቅር እንዴት ማሳየት እንደምትችሉ አስቡ።
በተጨማሪም 1 ጴጥሮስ 5፥2–4፣ 8፤ ጀፍሪ አር. ሆላንድ “የመጀመርያይቱ ታላቅ ትዕዛዝ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2012 (እ.አ.አ) 83–85ን ተመልከቱ።
ለቤተሰብ ቅዱሳን መጻህፍት ጥናትና ለቤተሰብ የቤት ምሽት ሃሳቦች
-
ሉቃስ 24፥5–6።ፕሬዝዳንት ቶማስ ኤስ. ሞንሰን ስለ ሉቃስ 24፥5–6፣ እንዲህ ብሏል፣ “በክርስትና ውስጥ ለእኔ የበለጠ ትርጉም ያለው ቃል የለም” (“ተነስቷል!፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2010 (እ.አ.አ)፣ 89)። እነዚህ ቃላት ለእናንተ እና ለቤተሰባችሁ ምን ማለት ናቸው?
-
ማቴዎስ 28፤ ማርቆስ 16፤ ሉቃስ 24፤ ዮሐንስ 20–21።ቤተሰባችሁ እነዚህን ምዕራፎች በሚያነብበት ጊዜ፣ በእያንዳንዱ ቁጥር ውስጥ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሰዎች ያስተውል። ለምሳሌ፣ የአዳኙን መቃብር ስለጎበኙ ሰዎች ምን ያስደንቃችኋል? ከሐዋርያት ቃል ወይም ድርጊት ወይም ከደቀ መዛሙርቱ የኤማሁስ መንገድ ምን ትማራላችሁ?
አብራችሁ መዘመርን አስቡ “በእርግጥ ኢየሱስ እንደገና ሕያው ነበር?” (የልጆች መዝሙር መፅሀፍ 64)። ቤተሰባችሁ ስለሚያውቀው የሞተው ሰው አውሩ እናም በዚህ መዝሙር ውስጥ ያሉት እውነቶች መጽናናትን እንዴት እንደሚያመጡ ተወያዩ።
-
ማቴዎስ 28፥16–20፤ ማርቆስ 16፥14–20፤ ሉቃስ 24፥44–53።በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፣ ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንዲያደርጉ የጠየቃቸው ምንድን ነው? ይህንን ሥራ ለማከናወን እንዴት መርዳት እንችላለን? የቤተሰብ አባላት ዓላማዎቹን ለመፈጸም “ጌታ ከእነርሱ ጋር [ሲሠራ]” የተሰማቸውን ልምዶች ማካፈል ይችላሉ (ማርቆስ 16፥20)።
-
ዮሐንስ 21፥15–17።አብራችሁ ስትበሉ እነዚህን ጥቅሶች ለማንበብ አስቡ። ይህ በአዳኙ “በጎቼን አሰማራ” በሚለው ቃል ላይ የተወሰነ ትርጉም ሊጨምር ይችላል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ኢየሱስ ስለ በጎች ባስተማረው መሠረት (ለምሳሌ ማቴዎስ 9፥35–36፤ 10፥5–6፤ 25፥31–46፤ ሉቃስ 15፥4–7፤ ዮሐንስ 10፥1–16ን ተመልከቱ) የእግዚአብሔርን ልጆች ማገልገልን ለመግለጽ በጎችን መመገብ ለምን ጥሩ መንገድ ነው? ይህ ምሳሌ የሰማይ አባት እና ኢየሱስ ስለ እኛ ምን እንደሚሰማቸው ያስተምራል?
ልጆችን ለማስተማር ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማግኘት የዚህን ሳምንት ዝርዝር በኑ፣ ተከተሉኝ—ለመጀመሪያ ክፍል ተመልከቱ።
በሃሳብ የሚቀርብ መዝሙር፦ “በእርግጥ ኢየሱስ እንደገና ሕያው ነበር?፣” የልጆች የመዝሙር መጽሃፍ፣ 64።