ብሉይ ኪዳን 2022 (እ.አ.አ)
በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች፥ ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ


“በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች፥ ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ብሉይ ኪዳን 2022 (እ.አ.አ) [2021 (እ.አ.አ)]

“በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች፥ ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ፣” ኑ፣ ተከተሉኝ—ለግለሰቦች እና ለቤተሰቦች፥ ብሉይ ኪዳን 2022 (እ.አ.አ)

ምስል
የሀሳቦች ምልክት

በአእምሮ ሊያዝ የሚገቡ ሀሳቦች

ድንኳኑ እና መሰዋዕቱ

ብሉይ ኪዳንን ስናነብ፣ አንዳንድ ጊዜ ለጌታ በግልጽ አስፈላጊ ስለነበሩ ነገሮች ነገር ግን ለእኛ ዛሬ አስፈላጊነታቸው ወዲያው የማይታዩን ረጅም ምንባቦችን እናገኛለን። ዘጸአት 25–3035–40ዘሌዋውያን 1–916–17 ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ ምዕራፎች በምድረ በዳ የነበረውን የእስራኤልን ድንኳን እና እዚያ የሚከናወኑትን የእንስሳት መሥዋዕቶች በዝርዝር ይገልፃሉ።1 ድንኳኑም በህዝቡ መካከል የጌታ ማደሪያ የነበረው ተንቀሳቃሽ ቤተመቅደስ ነበር።

የእኛ የዘመኑ ቤተመቅደሶች ከእስራኤል ድንኳን ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፣ ነገር ግን በእርግጥ በዘፀአት ውስጥ ካለው መግለጫ ጋር አይመሳሰሉም። እናም እኛ በቤተመቅደሶቻችን ውስጥ እንስሳትን አንገድልም—የአዳኙ የኃጢያት ክፍያ ከ2 ሺህ ዓመታት በፊት የእንስሳት መስዋእትን አጠናቋል። ሆኖም እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ ዛሬ ስለ ጥንታዊ የእስራኤል አምልኮ ዓይነቶች ማንበብ ታላቅ ዋጋ አለው፣ በተለይም በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የሚናንብባቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንዳደረጉት የምናያቸው ከሆነ—ማለትም “በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ለማጠናከር” በማሰብ (አልማ 25፥16፤ በተጨማሪም ያዕቆብ 4፥5ጀሮም 1፥11ን ይመልከቱ)። የድንኳንን እና የእንስሳ መስዋእትን ምሳሌ ስንረዳ፣ በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩልን መንፈሳዊ ግንዛቤዎችን ማግኘት እንችላለን።

ምስል
ሰዎች ድንኳን ውስጥ ለካህናት በግ ሲያመጡ

እስራኤላዊያን ወደ ድንኳኑ በግ ሲያመጡ የሚያሳይ ስዕል፣ በሮበርት ቲ.ባሬት

ድንኳኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነትን ያጠነክራል

እግዚአብሔር ሙሴን በእስራኤላውያን ሰፈር ውስጥ ድንኳን እንዲሠራ ባዘዘው ጊዜ ዓላማው “በመካከላቸው አድር ዘንድ” እንደሆነ ተናግሯል (ዘጸአት 25፥8)። በድንኳኑ ውስጥ የእግዚአብሔር መገኘት በቃል ኪዳኑ ታቦት ይወከላል—ይህም በውስጡ እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን መዝገብን የያዘ በወርቅ የተሸፈነ የእንጨት ሳጥን ነው (ዘፀአት 25፥10–22 ይመልከቱ)። ታቦቱ ከድንኳኑ ሊሎች ክፍሎች በመጋረጃ በመለየት እጅግ በተቀደሰው ውስጠኛው ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ይህ መጋረጃ በመውደቁ ምክንያት ከእግዚአብሔር ፊት የመለየታችንን ምልክት ያሳያል።

ከሙሴ ሌላ ወደዚያ “በቅድስተ ቅዱሳን” (ዘጸአት 26፥34) ውስጥ ለመግባት የሚችል አንድ ሰው ብቻ ነው የምናውቀው—ሊቀ ካህናቱ። እንደ ሌሎቹ ካህናት፣ እሱ በመጀመሪያ መታጠብ እና መቀባት (ዘጸአት 40፥12–13ን ይመልከቱ) እና ሀላፊነቱን የሚያመለክቱ ቅዱስ ልብስ መልበስ ነበረበት (ዘጸአት 28ን ይመልከቱ)። በዓመት አንድ ጊዜ የሥርየት ቀን ተብሎ በሚጠራው ቀን ሊቀ ካህኑ ብቻውን ወደ ድንኳኑ ከመግባቱ በፊት ሰዎችን ወክሎ መሥዋዕትን ያቀርብ ነበር። በመጋረጃው ላይ ዕጣን ያጥናል (ዘሌዋውያን 16፥12ን ይመልከቱ)። ወደ ሰማይ ያረገው መዓዛ ያለው ጭስ ወደ እግዚአብሔር የሚያርግ የሰዎችን ጸሎት ይወክላል (መዝሙረ ዳዊት 141፥2፣ ይመልከቱ)። ከዚያ ሊቀ ካህኑ ከእንስሳ መስዋዕት የመጣን ደም ይዞ በመጋረጃው ውስጥ ያልፍ እና በቃል ኪዳኑ ታቦት ወደተመሰለውን የእግዚአብሔር ዙፋን ይጠጋል (ዘሌዋውያን 16፥14–15ን ይመልከቱ)።

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና በሰማይ አባት እቅድ ውስጥ ስላለው ሚና የምታውቁት እንዳለ ሆኖ፣ ድንኳኑ እንዴት ወደ አዳኙ እንደሚያመለክተን ማየት ትችላላችሁን? ልክ ድንኳኑ እና በውስጡ ያለው ታቦት በሕዝቡ መካከል የእግዚአብሔርን መገኘት እንደሚያመለክት፣ ኢየሱስ ክርስቶስም በሕዝቦቹ መካከል የእግዚአብሔር መገኛ ነበር ሁሉ (ዮሐንስ 1፥14ን ይመልከቱ)። እንደ ሊቀ ካህኑ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ እና በእግዚአብሔር አብ መካከል አማላጅ ነው። እርሱ ራሱ በከፈለው የመስዋእትነት ደም ስለ እኛ ሊያማልድልን በመጋረጃው በኩል አልፏል (ዕብራውያን 8–10ን ይመልከቱ)።

አንዳንድ የእስራኤል ድንኳኖች ገጽታ ለእናንተ አዲስ ላይሆኑ ይችላሉ፣ በተለይም የግል ስርዓቶቻችሁን ለመቀበል ወደ ቤተመቅደስ ሄዳችሁ የምታውቁ ከሆነ። ልክ እንደ ድንኳኑ እጅግ ቅዱስ ስፍራ፣ የቤተመቅደሱ ሰለስቲያል ክፍል የእግዚአብሔርን መገኘት ይወክላል። ለመግባት፣ መጀመሪያ መታጠብ እና መቀባት አለብን። ቅዱስ ልብሶችን እንለብሳለን። በመሰዊያው ላይ ወደ እግዚአብሔር የሚያርጉ ፀሎቶችን እንፀልያለን። እናም በመጨረሻ ወደ እግዚአብሔር ፊት ለመግባት በመጋረጃ ውስጥ እናልፋለን።

ምናልባትም በዘመናዊ ቤተመቅደሶች እና በጥንታዊ ድንኳን መካከል ያለው በጣም አስፈላጊ የሆነ ተመመሳሳይነት ቢኖር ሁለቱም፣ በትክክል ከተረዳነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክሩ እና ስለእርሱ ቤዛ መስዋእትነት በአድናቆት የሚሞሉ መሆናቸው ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ ሁሉ ወደ እርሱ እንዲገቡ ይፈልጋል፤ እርሱ የሴት ካህናት እና “የካህናት መንግሥት” ይፈልጋል (ዘጸአት 19፥6)። ነገር ግን ኃጢያቶቻችን ያንን በረከት እንዳናገኝ ያግዱናል፣ ምክንያቱም “ምንም እርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖር አይቻለውም” (1 ኔፊ 10፥21)። ስለዚህም አብ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን “ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ” ላከው (ዕብራውያን 9፥11)። እርሱ ለእኛ መጋረጃን ከፍቶ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ሁሉ “ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት [እንቀርብ]” (ዕብራዊያን 4፥16) ዘንድ ሀይል ሰጠ።

ዛሬ፣ የቤተመቅደሶች ዓላማ ለራሳችን ደህንነትን ከማግኘት የበለጠ ነው። የራሳችንን ስርዓት ከተቀበልን በኋላ፣ በእነርሱ ምትክ ስርአቶችን በወኪልነት ለመቀበል በቅድመ አያቶቻችን ምትክ መቆም እንችላለን። በአንድ መልኩ፣ ለሌሎች የእግዚአብሔርን መገኘትን መንገድ በመክፈት እኛም እንደጥንቱ ሊቀ ካህናት—እና እንደ ታላቁ ሊቀ ካህናት—ለመሆን እንችላለን።

መስዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እምነትን ያጠነክራል

ከሙሴ ሕግ ረጅም ጊዜ በፊት በነበረው የጥንት የእንስሳት መሥዋዕት ውስጥ የኃጢያት ክፍያና የዕርቅ መርሆዎች በሀይል ያስተምራሉ። በዳግም በተመለሰው ወንጌል ምክንያት፣ አዳምና ሔዋን መስዋእት እንዳቀረቡ፣ ይህም የአዳኙን መስዋእትነት ምሳሌያዊ አመላካች እንደሆነ እንደተገነዘቡ እና ይህን ለልጆቻቸው እንዳስተማሩ እናውቃለን ( ሙሴ 5፥4–12ን ይመልከቱ፤ በተጨማሪም ዘፍጥረት 4፥4ን ይመልከቱ)።

በጥንቷ እስራኤል የሥርየት ቀን (በዕብራይስጥ “ዮም ኪፐር”) የእንስሳ መስዋእትነት ተምሳሌትነት በተለይ ስሜት ቀስቃሽ ሆኖ ሊታይ ይችላል። የዚህ ዓመታዊ ሥነ ሥርዓት አስፈላጊነት በዘሌዋውያን 16፥30 ውስጥ ተገልጧል፥ “በዚህ ቀን ትነጹ ዘንድ ማስተሰረያ ይሆንላችኋልና፣ … በእግዚአብሔርም ፊት ከኃጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ።” ስለዚህ የእግዚአብሔር መኖር በሕዝቡ መካከል ሊቆይ ይችላል። ይህ ስርየት የተከናወነው በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ነበር። ከእነዚህ በአንዱ ውስጥ ፍየል ለሰዎች ኃጢአት መስዋእት ሆኖ ይሰዋል፣ እናም ሊቀ ካህኑ የፍየሉን ደም ወደ እጅግ ቅዱስ ስፍራ ይወስዳል። በኋላም ሊቀ ካህኑ እጆቹን ህይወት ባለው ፍየል ላይ ጭኖ የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት ይናዘዛል—በምሳሌያዊ ሁኔታ እነዚህን ኃጢአቶች ወደ ፍየል በማስተላለፍ። ከዚያም ፍየሉ ከእስራኤል ሰፈር ይወገዳል።

በዚህ ሥነ-ስርዓት ፍየሎች የኃጢአተኛ ሰዎችን ቦታ በመያዝ ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታሉ። ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት መፈቀድ የለበትም። ነገር ግን ኃጢአተኞቹን ከማጥፋት ወይም ከማስወገድ ይልቅ እግዚአብሔር ሌላ መንገድ አዘጋጀ—በምትኩ ፍየል ይገደላል ወይም ይወገዳል። “ፍየሉም ኃጢአታቸውን ሁሉ … ይሸከማል” (ዘሌዋውያን 16፥22)።

የእነዚህ ሥነ-ሥርዓቶች ተምሳሌትነት እግዚአብሔር ወደ እርሱ ፊት እንድንመለስ የሰጠንን መንገድ ያመለክታሉ—እነዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ እና የእርሱ የኃጢያት ክፍያ ናቸው። አዳኙ “ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፣” እንዲሁም “የሁላችንን በደል” (ኢሳይያስ 53፥4፣ 6)። እርሱ በእኛ ቦታ ቆመ፣ የኃጢአትን ቅጣት ለመክፈል ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ፣ እና ከዚያ በኋላም በትንሳኤው በኩል ሞትን ድል አደረገ (ሞዛያ 15፥8–9ን ይመልከቱ)። የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋእት “ታላቅ እና የመጨረሻ መስዋዕትነት፤ አዎን፣ የሰውም ሆነ የእንሥሳ … መስዋዕት አይደለም፣” ግን “መጨረሻ የሌለው እንዲሁም ዘለአለማዊ መስዋዕት” ነበር (አልማ 34፥10)። ወደ እርሱ የሚያመለክቱት የጥንት መስዋዕቶች ሁሉም ፍፃሜ ነበር።

በዚህ ምክንያት፣ መስዋዕቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ እንዲህ አለ፣ “ከእንግዲህ ደምን በማፍሰስ አታበርክቱልኝ፤ አዎን፣ መሥዋዕቶቻችሁ … ይቆማሉ። … እናም ለእኔም መስዋእት የተሰበረ ልብና የተዋረደ መንፈስ ታቀርባላችሁ” (3 ኔፊ 9፥19–20)።

ስለዚህ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መስዋዕቶች እና ስለ ድንኳኑ (ወይም በኋላ፣ ስለ መቅደሱ) ምንባቦችን ስታገኙ—እና ብዙዎቹን ታገኛላችሁ—የዚህ ሁሉ ዋና ዓላማ በመሲሁ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ ላይ ያላችሁን እምነት ለማጠናከር እንደሆነ አስታውሱ። ልባችሁ እና አዕምሮአችሁ ወደ እርሱ ይዙር። እርሱ ወደ እግዚአብሔር ፊት እናንተን ለመመለስ ምን እንዳደረገ እና እናንተ እርሱን ለመከተል ምን እንደምታደርጉ አሰላስሉ።

ማስታወሻ

  1. ዘጸአት 33፥7–11 ሙሴ ከጌታ ጋር የተገናኘበትን “የመገናኛውም ድንኳን” ይጠቅሳል፣ ነገር ግን በዘጸአት እና በዘሌዋውያን ውስጥ የተገለጹት የመሥዋዕቶች ስፍራ ይህ ቦታ አልነበረም። እነዚያ መሥዋዕቶች የተከናወኑት በዘፀአት 25–30 ውስጥ በተገለጸው፣ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲሠራ ባዘዘው እና የእስራኤል ልጆች በገነቡት ድንኳን ውስጥ ነበር (ዘፀአት 35–40ን ይመልከቱ)። አሮንና ወንዶች ልጆቹ የእንስሳት መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ይህ ድንኳን ብዙውን ጊዜ “የመገናኛው ድንኳን” ተብሎም ይጠራ ነበር (ለምሳሌ ዘጸአት 28፥4338፥30ዘሌዋውያን 1፥3ን ይመልከቱ)።

አትም