ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፫


ምዕራፍ ፫

የጋድያንቶን መሪ፣ ጊድያንሒ፣ ላኮኔዎስ እናም ኔፋውያን እራሳቸውን እንዲሁም ምድራቸውን እንዲያስረክቡ በማስገደድ ጠየቀ—ላኮኔዎስ የወታደሮቹ ዋና ሻምበል አድርጎ ጊድጊዶኒን ሾመው—ኔፋውያን በዛራሄምላ እናም በለጋሱ ምድር እራሳቸውን ለመከላከል በአንድነት ተሰበሰቡ። ፲፮–፲፰ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ክርስቶስ ከመጣ በአስራ ስድስተኛው ዓመት፣ የምድሪቱ ገዢ ላኮኔዎስ፣ ከዘራፊዎቹ ቡድን መሪና አስተዳዳሪ ከሆነው ደብዳቤን ተቀበለ፤ እናም የተፃፉት ቃላት እንዲህ የሚሉ ነበሩ፥

የምድሪቱ ልዑልና ዋና አስተዳዳሪ የሆንከው ላኮኔዎስ፤ እነሆ፣ ይህንን ደብዳቤ እጽፍልሃለሁ፤ እናም በጽኑነትህና፣ ደግሞ እናንተ መብታችንና ነፃነታችን ነው ብላችሁ የምትገምቱትን በመጠበቅ በህዝብህ ጽኑነት፣ ለአንተ እጅግ ታላቅ የሆነ ምስጋናን እሰጥሃለሁ፤ አዎን፣ ነፃነታችሁንና ንብረታችሁን እናም ሀገራችሁን ወይም እንደዚህ የምትጠሯቸውን ለመከላከል በአንድ በአምላክ የተረዳችሁ በመምሰል ፀንታችሁ ቆማችኋል።

እናም ልዑል ላኮኔዎስ፣ ለእኔ የሚያሳዝነኝ ቢኖር በእኔ ትዕዛዝ ስር ያሉትን፣ በአሁኑ ሰዓት የጦር መሳሪያቸውን ይዘው የቆሙትን ብዙ ጀግና ሰዎችን፣ በኔፋውያን ላይ ዝመቱና አጥፉአቸው የሚለውን ቃሉንም በታላቅ ጉጉት የሚጠብቁትን ለመቋቋም እንደምትችሉ በመገመትህ አንተ ሞኝ እንዲሁም ከንቱ በመሆንህ ያሳዝነኛል።

እናም እርሱንም በጦር ሜዳው በማረጋገጤ፣ የማይሸነፈውን መንፈሳቸውን አውቃለሁ፤ በእነርሱም ላይ ብዙ ስህተቶችን በመፈፀማችሁ በእናንተም ላይ ያለባቸውን ዘላለማዊ ጥላቻ ስለማውቅ፣ ስለዚህ በእናንተም ላይ የሚመጡ ከሆነ ፍፁም በሆነ ጥፋት ይጎበኙአችኋል።

ስለዚህ ለደህንነታችሁ በማሰብ፣ ትክክል ነው ብላችሁ በምታምኑበት ባላችሁ ፅኑነት እናም በጦር ሜዳው ባላችሁ የጅግንነት መንፈስ ምክንያት ይህንን ደብዳቤ ጽፌ በራሴ እጅ አሽጌዋለሁ።

ስለዚህ በጎራዴ ከሚጎበኙአችሁ፤ እናም ጥፋት በእናንተ ላይ ከሚመጣ ለህዝቦቼ ከተሞችህን፤ ምድራችሁን እናም ንብረቶችህን እንድትተው በመፈለጌ ይህንን ለአንተ ጽፌአለሁ።

ወይንም በሌላ አነጋገር፣ ራሳችሁን ለእኛ ስጡ፣ እናም ከእኛ ጋር አንድ ሁኑና ከሚስጥር ስራዎቻችን ጋር ተባበሩ፤ እናም እንደ እኛም ትሆኑ ዘንድ ወንድሞቻችን ሁኑ፣ አገልጋዮቻችን አትሁኑ፣ ነገር ግን ወንድሞቻችንና የሀብቶቻችን ሁሉ አጋር ሁኑ።

እናም እነሆ ይህንን የምታደርጉ ከሆናችሁ፣ የማትጠፉ መሆናችሁን በመሃላ አረጋግጥልሃለሁ፤ ነገር ግን ይህንን የማታደርጉ ከሆነ፣ በሚቀጥለው ወር ወታደሮቼ በአናንተ ላይ እንዲመጡና እጃቸውን ባለመመለስ እናም ህይወታችሁን እንዳያተርፉ፣ ነገር ግን እንዲገድሉአችሁ እናም ፈፅሞ እስከምትጠፉ ድረስ ጎራዴዎች በእናንተ ላይ እንዲያርፉ ማዘዜን በመሃላ አረጋግጣለሁ።

እናም እነሆ፣ እኔ ጊድያንሒ ነኝ፤ እናም የዚህ የጋድያንቶን ሚስጥራዊ ማህበረሰብ አስተዳዳሪ ነኝ፤ በዚያም ያለው ማህበረሰብ እንዲሁም ስራዎች መልካም መሆናቸውን አውቃለሁ፤ እናም እነርሱም በጥንት ጊዜ የነበሩ ናቸውና ለእኛ ተላልፈውልናል።

እናም ላኮኔዎስ፣ ይህንን ደብዳቤ ለአንተ እፅፋለሁ፤ እናም የመንግስታቸውን መብት ለመንጠቅ በነበረህ ክፋት የተነሳ ከአንተ የተገነጠሉትን ህዝቦቼን መብት፣ እንዲሁም ይህ ህዝቤ መንግስቱንና መብቱን ያለምንም ደም መፋሰስ ይመልስ ዘንድ ምድርህን እንዲሁም ሀብቶችህን እንደምትሰጠኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እናም ይህንን ካላደረግህ ስለተነፈጉት ነገሮቻቸው እበቀላለሁ። እኔ ጊድያንሒ ነኝ።

፲፩ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ ላኮኔዎስ ይህንን ደብዳቤ በተቀበለበት ጊዜ ጊድያንሒ የኔፋውያንን ምድር በድፍረት በመፈለጉና፣ ደግሞ ህዝቡንም በማስፈራራቱ፣ እናም ወደ ክፋቶቹና፣ ርኩሳኑ ዘራፊዎች እራሳቸውን በመገንጠል ስህተት ከመስራታቸው በስተቀር ስህተት ያልተቀበሉትን ስህተት እበቀላለሁ በማለቱ እጅግ ተገርሞ ነበር።

፲፪ እናም እነሆ፣ ይህ አስተዳዳሪው፣ ላኮኔዎስ፣ ፃድቅ ሰው ነበር፤ እናም በዘራፊው ፍላጎቶች እንዲሁም ማስፈራራት ሊፈራ አልቻለም፤ ስለዚህ የዘራፊዎቹ አስተዳዳሪ የሆነውን የጊድያንሒን ደብዳቤ አላደመጠም፣ ነገር ግን ዘራፊዎቹ ወደ እነርሱ በሚመጡበት ወቅት ህዝቡም እንዲበረቱ ወደ ጌታ እንዲጮህ አደረገ።

፲፫ አዎን፣ ከምድሪቱ በስተቀር ህዝቡም ሴቶቻቸውን፣ እናም ልጆቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና፣ መንጋዎቻቸውን እንዲሁም ሀብቶቻቸውን በሙሉ በአንድነት እንዲሰበስቡ ዘንድ በመካከላቸው አዋጅን ላከ።

፲፬ እናም በዙሪያቸው ምሽግ እንዲሰራና፣ ጥንካሬአቸውም እጅግ ታላቅ እንዲሆን አደረገ። እናም የኔፋውያንና የላማናውያን ወታደሮች፣ ወይም ከኔፋውያን መካከል የሚቆጠሩ ሁሉ እነርሱን እንዲጠብቁ፤ በዙሪያቸው ጠባቂ ሆነው እንዲቀመጡ፣ እናም በቀንና በምሽት ከዘራፊዎች እንዲጠብቁአቸው አደረገ።

፲፭ አዎን፣ እንዲህም አላቸው፥ ጌታ ህያው እንደሆነ፣ ለኃጢአቶቻችሁ ንሰሃ ካልገባችሁ፣ እናም ወደ ጌታ ካልጮሀችሁ በቀር፣ በየትኛውም መንገድ ቢሆን ከጋድያንቶን ዘራፊዎች አታመልጡም።

፲፮ እናም የላኮኔዎስ ቃላቶች እንዲሁም ትንቢቶች ታላቅ እንዲሁም አስገራሚ በመሆናቸው በህዝቡ ሁሉ ላይ ፍርሀት እንዲመጣ አደረገ፤ እናም እንደላኮኔዎስም ቃላት ለማድረግ እራሳቸው በኃይላቸው ጥረት አደረጉ።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ላኮኔዎስ ዘራፊዎቹ ከምድረበዳው ወጥተው ወደ እነርሱ በሚመጡበት ጊዜ እንዲያዙአቸው በኔፋውያን ወታደሮች ሁሉ ላይ ዋና ሻምበሎች ሾመ።

፲፰ አሁን ከዋና ሻምበሎች መካከል ዋና እናም ከኔፋውያን ሠራዊት ሁሉ ታላቁ አዛዥ የሆነ ተሹሞ ነበር፤ እናም ስሙም ጊድጊዶኒ ይባል ነበር።

፲፱ እንግዲህ በኔፋውያን ሁሉ መካከል (ክፋት በሚፈጽሙበት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር) የራዕይ እንዲሁም ደግሞ የትንቢት መንፈስ ያለቸውን ዋና ሻምበሎዎች የመሾም ባህል ነበር፤ ስለዚህ፣ ይህ ጊድጊዶኒ በእነርሱ መካከል ታላቅ ነቢይ ነበር፤ ደግሞም ዋና ዳኛም ነበር።

እንግዲህ ህዝቡም ለጊድጊዶኒ እንዲህ አለው፥ ወደጌታ ፀልይና፣ ዘራፊዎቹን እናጠቃቸው እናም በራሳቸው ምድር እናጠፋቸው ዘንድ ወደ ተራራው እናም ወደ ምድረበዳው እንሂድ።

፳፩ ነገር ግን ጊድጊዶኒ እንዲህ አላቸው፥ ጌታ ወደዘራፊዎቹ እንዳንሄድ ይከለክላል፤ ወደእነርሱ የምንሄድ ከሆነ ጌታ በእጃቸው እንድንወድቅ ያደርጋል፤ ስለዚህ በምድራችን እምብርት እራሳችንን እናዘጋጃለን፣ እናም ሠራዊታችንን በሙሉ በአንድ ላይ እንሰበስባለን፣ እናም በእነርሱ ላይ አንሄድም፤ ነገር ግን በእኛ ላይ እስከሚመጡ ድረስ እንጠብቃቸዋለን፤ ስለዚህ ጌታ ህያው እንደሆነ፣ ይህንን የምናደርግ ከሆነ እነርሱን በእጃችን ስር እንዲወድቁ ያደርጋል።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ በአስራ ሰባተኛው ዓመት፣ በዓመቱ በስተመጨረሻ፣ የላኮኔዎስ አዋጅ በምድሪቱ ገፅ ሁሉ ተዳረሰ፤ እናም ፈረሶቻቸውን፣ ሠረገላዎቻቸውንም፣ የቀንድ ከብቶቻቸውንም፣ እናም መንጋዎቻቸውን ሁሉና፣ ከብቶቻቸውን፣ እህሎቻቸውንም፣ እናም ንብረቶቻቸውን በሙሉ ወሰዱ፣ እናም በሺህዎችና፣ በአስር ሺህዎች፣ ከጠላቶቻቸው ለመከላከል ዘንድ አብረው እንዲሰበሰቡ ወደተመደቡላቸው ስፍራዎች እስከሚሄዱ ድረስ ዘመቱ።

፳፫ እናም የተመረጠችው ምድር የዛራሄምላ ምድር ነበረች፤ እናም ምድሪቱ በዛራሄምላ ምድርና በለጋስ ምድር መካከል ነበረች፤ አዎን፣ በለጋስ ምድርና በወደመው ምድር መካከል ባለው ወሰን።

፳፬ እናም ኔፋውያን ተብለው የሚጠሩ፤ በዚህች ምድር ላይ ራሳቸውን በአንድነት የሰበሰቡ ብዙ ሺህ ሰዎች ነበሩ። እንግዲህ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል በነበረው ታላቅ እርግማን የተነሳ ላኮኔዎስ በምድሪቱ በስተደቡብ እራሳቸውን በአንድ ላይ እንዲሰበስቡ አደረገ።

፳፭ እናም ከጠላቶቻቸው እራሳቸውን ሸሸጉ፤ እናም በአንድ ምድርና፣ በአንድነት ኖሩም፣ በላኮኔዎስ የተነገሩትንም ቃላት ፈሩ፤ በዚህም የተነሳ ለኃጢአቶቻቸው በሙሉ ንስሃ ገቡ፤ እናም ጠላቶቻቸው ሊዋጉአቸው በመጡ ጊዜ እንዲያድናቸው ዘንድ ወደ ጌታ አምላካቸው ፀለዩ።

፳፮ እናም በጠላቶቻቸው የተነሳ እጅግ አዝነው ነበር። እናም ጊድጊዶኒ ከሁሉም ዐይነት የጦር መሳሪያዎችን እንዲሰሩና፣ በትዕዛዙ መሠረት በጦር መሳሪያ፤ እናም ጋሻና፣ ዘለበት እንዲጠናከሩ አደረገ።