ምዕራፍ ፳
ጌታ አሞንን የታሰሩትን ወንድሞቹን ከእስር እንዲያስለቅቅ ወደ ሚዶኒ ላከው—አሞንና ላሞኒ በምድሪቱ ላይ ንጉስ የሆነውን የላሞኒን አባት አገኙት—አሞን አዛውንቱን ንጉስ የወንድሞቹን መለቀቅ እንዲያፀድቅለት አስገደደው። በ፺ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ቤተክርስቲያንን ካቋቋሙ በኋላ፣ አሞንን ለአባቱ ለማሳየት ከእርሱ ጋር ወደ ኔፊ ምድር ይሄድ ዘንድ ንጉስ ላሞኒ ፈለገ።
፪ እናም የጌታ ድምፅ ወደ አሞን እንዲህ ሲል መጣ፥ እነሆም ንጉሱ ህይወትህን ሊያጠፋ ይፈልጋልና ከእርሱ ጋር ወደ ኔፊ ምድር አትሂድ፤ ነገር ግን ወደ ሚዶኒ ምድር ሂድ፤ እነሆ፣ ወንድምህ አሮን፣ ደግሞም ሙሎቂና አማ በወህኒ ቤት አሉና።
፫ እንግዲህ እንዲህ ሆነ አሞን ይህንን በሰማ ጊዜ፣ ለላሞኒ እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ ወንድሜ እናም ወንድሞቻችንን በሚዶኒ በወህኒ ናቸው፣ እናም ላስለቅቃቸው ወደዚያው እሄዳለሁ።
፬ አሁን ላሞኒ ለአሞን አለው፥ በጌታ ጥንካሬ ሁሉንም ነገሮች ማድረግ እንደምትችል አውቃለሁ። ነገር ግን እነሆ፣ ከአንተ ጋር ወደ ሚዶኒ ምድር እሄዳለሁ፤ አንቲዮምኖ የተባለው የሚዶኒ ንጉስ ጓደኛዬ ነውና፤ ስለዚህ ወደ ሚዶኒ ምድር እሄዳለሁ፣ ወንድሞችህን እንዲለቅ ንጉሱን አባብለዋለሁ። አሁን ላሞኒ እንዲህ አለው፥ ወንድሞችህ በወህኒ ቤት እንደሆኑ ማን ነገረህ?
፭ እናም አሞን እንዲህ አለው፥ ከእግዚአብሔር በቀር ማንም አልነገረኝም፣ እንዲህም አለኝ—ሂድና ወንድሞችህን አስለቅቅ፣ ምክንያቱም እነርሱ በሚዶኒ ምድር በወህኒ ናቸውና።
፮ እናም ላሞኒ ይህን በሰማ ጊዜ አገልጋዮቹ ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን እንዲያዘጋጁ አደረገ።
፯ እናም ለአሞን እንዲህ አለው፥ ና እኔ ወደ ሚዶኒ ምድር ከአንተ ጋር እሄዳለሁ እናም ንጉሱ ወንድሞችህን ከወህኒ እንዲለቃቸው እለምናለሁ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ አሞንና ላሞኒ ወደዚያ ቦታ በተጓዙ ጊዜ፣ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ንጉስ የሆነውን የላሞኒን አባት አገኙት።
፱ እናም እነሆ፣ የላሞኒ አባት እንዲህ አለው፥ ለልጆቼና ለህዝቤ በዓል በማደርግበት ታላቅ ቀን በዚያ በዓል ላይ ለምን አልመጣህም?
፲ እናም ደግሞ እንዲህ አለው፥ ከእዚህ ከሃሰተኛ ልጆች አንዱ ከሆነው ከኔፋዊ ጋር ወዴት ትሄዳለህ?
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ላሞኒ እርሱን ማበሳጨትን ፈርቶ ወዴት እንደሚሄድ በዝርዝር ነገረው።
፲፪ እናም ደግሞ በራሱ መንግስት የዘገየባቸውንና አባቱ ወደ አዘጋጀው በዓል ያልሄደበትን ምክንያቶች ሁሉ ነገረው።
፲፫ እናም አሁን ላሞኒ እነዚህን ሁሉ ነገሮች በዝርዝር በተናገረ ጊዜ፣ እነሆ፣ አባቱ በእርሱ ተቆጥቶ ስለነበር ተቆጣ፣ እናም እንዲህ አለ፥ ላሞኒ፣ እነዚህን የውሸት ልጆች የሆኑትን ኔፋውያን ልታስለቅቃቸው ነው። እነሆ፣ እነርሱ አባቶቻችንን ዘርፈዋል፤ እናም አሁን ልጆቹ በማታለልና፣ በውሸታቸው እኛን ለማጭበርበር ንብረታችንን በድጋሚ ለመዝረፍ መጥተዋል።
፲፬ አሁን የላሞኒ አባት አሞንን በጎራዴው እንዲገድለው ላሞኒን አዘዘው። እናም ወደ ሚዶኒ ምድርም ደግሞ እንዳይሄድ፣ ነገር ግን ከእርሱ ጋር ወደ እስማኤል ምድር እንዲመለስ አዞት ነበር።
፲፭ ነገር ግን ላሞኒም አለው፥ አሞንን አልገድለውም፣ ወደ እስማኤል ምድርም አልመለስም፣ ነገር ግን የአሞንን ወንድሞች ለማስለቀቅ ወደ ሚዶኒ ምድር እሄዳለሁ፣ ምክንያቱም እነርሱ ትክክለኛ ሰዎችና የእውነተኛው አምላክ ነቢያት እንደሆኑ አውቃለሁና።
፲፮ አሁን አባቱ እነዚህን ቃላት በሰማ ጊዜ ተቆጥቶት ነበር፣ እናም መሬት እስከሚወድቅ ድረስ ለመምታት ጎራዴውን መዘዘበት።
፲፯ ነገር ግን አሞን ወደፊት በመምጣት ቆመ፣ እናም እንዲህ አለው፥ እነሆ ልጅህን አትግደል፤ ይሁን እንጂ፣ ከአንተ ይልቅ እርሱ ቢወድቅ ይሻላል፣ ምክንያቱም እነሆ እርሱ ለኃጢአቱ ንስሃ ገብቷል፤ ነገር ግን በዚህን ጊዜ በቁጣህ አንተ ብትወድቅ ነፍስህ መዳን አትችልም።
፲፰ እናም በድጋሚ፣ ከማድረግ ብትቆጠብ መልካም ነው፤ ልጅህን ብትገድል፣ የንፁህ ልጅ ደም ከምድር ወደ ጌታ ወደ አምላኩ ለበቀል ይመጣ ዘንድ ይጮህ ነበር፤ እናም ምናልባትም በነፍስም ትሞታለህና።
፲፱ አሁን አሞን እነዚህን ቃላት በተናገረው ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰለት፥ ልጆቼን መግደል ካለብኝ የንፁሀን ደም ማፍሰሴን አውቃለሁ፤ እርሱን ለማጥፋት የፈለግኸው አንተ ነህና።
፳ እናም አሞንን ለመግደል እጁን ዘረጋ። ነገር ግን አሞን ምቱን ተቋቋመው፣ እናም ደግሞ መጠቀም እንዳይችል ክንዱን መታው።
፳፩ እንግዲህ አሞን ሊገድለው እንደሚችል ንጉሱ በተመለከተ ጊዜ፣ ህይወቱን እንዲያተርፍለት አሞንን ለመነው።
፳፪ ነገር ግን አሞን ጎራዴውን አነሳ፣ እናም አለ፥ እነሆ፣ ወንድሞቼ ከወህኒ ቤት እንዲወጡ አድርገህ ካልሰጠኸኝ እመታሀለሁ።
፳፫ እንግዲህ ንጉሱ ህይወቱን አጣለሁ ብሎ በመፍራቱ እንዲህ አለ፥ እኔን ካዳንኸኝ ከመንግስቴም እኩሌታውን እንኳን ቢሆን የጠየቅኸውን ሁሉ እሰጥሃለሁ።
፳፬ እንግዲህ አሞን እንደፍላጎቱ በሸመገለው ንጉስ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው በተመለከተ ጊዜ እንዲህ አለው፥ ወንድሞቼን ከወህኒ ለቀህ የምትሰጠኝ ከሆነ፣ እናም ደግሞ ላሞኒ መንግስቱን ባለበት ካቆየ፣ እናም አንተ በእርሱ የማትከፉ ከሆንክ፣ ነገር ግን በማንኛውም ነገር እንዳሰበው፣ እንደፍላጎቱ እንዲሰራ የምትሰጠው ከሆነ አድንሃለሁ፣ አለበለዚያ መትቼ በመሬት ላይ እጥልሃለሁ።
፳፭ አሁን አሞን እነዚህን ቃላት በሚናገርበት ጊዜ፣ ንጉሡ ህይወቱ በመትረፉ መደሰት ጀመረ።
፳፮ እናም አሞን እርሱን የማጥፋት ፍላጎት እንደሌለው በተመለከተ ጊዜና፣ ለልጁ ለላሞኒ ያለውን ታላቅ ፍቅርም ደግሞ በተመለከተ ጊዜ፣ እጅግ ተገረመ፣ እናም እንዲህ አለ፥ ይህ ሁሉ አንተ የፈለከው በመሆኑ፣ ወንድሞችህን እለቃለሁ፣ እናም ልጄ ላሞኒ መንግስቱን ይዞ እንዲቆይ እፈቅዳለሁ፤ እነሆ፣ ልጄ መንግስቱን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከዘለአለም እንዲያቆይ እፈቅድልሀለሁ፤ እናም ከእንግዲህ ወዲህ እኔ አላስተዳድረውም—
፳፯ እናም ደግሞ ወንድሞችህ ከወህኒ ቤት እንዲለቀቁ አደርጋለሁ፣ እናም አንተና ወንድሞችህ በመንግስቴ ወደ እኔ ለመምጣት ትችላላችሁ፤ ምክንያቱም አንተን ለመመልከት በሀይል እፈልጋለሁ። ንጉሱ አሞን በተናገራቸው ቃላትና ደግሞ ልጁ ላሞኒ በተናገራቸው ቃላት ተገረመ፣ ስለዚህ እነርሱን ለመረዳት ፈልጎ ነበር።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ አሞንና ላሞኒ ወደ ሚዶኒ ምድር ጉዞአቸውን ቀጠሉ። እናም ላሞኒ በምድሪቱ ንጉስ ፊት ሞገስን አገኘ፤ ስለዚህ የአሞን ወንድሞች ከወህኒ ቤት ወጡ።
፳፱ እናም አሞን ራቁታቸውን በመሆናቸው፣ በሲባጎ በጥብቅ በመታሰራቸው፣ ቆዳቸው ቆስሎ ባገኛቸው ጊዜ፣ እጅግ አዝኖ ነበር። እናም በረሃብ፣ በጥምና በሁሉም ዓይነት ስቃዮች ተሰቃይተዋል፤ ይሁን እንጂ፣ በስቃያቸው ሁሉ ትዕግስት ነበራቸው።
፴ እናም፣ ይህ በመሆኑ የበለጠ ጠጣርና አንገተ ደንዳና በሆኑ ሰዎች እጅ መውደቅ ዕድላቸው ነበር፤ ስለዚህ ቃላቸውን አላዳመጡም፣ ጣሉአቸውም፣ መቱአቸውም፣ እናም ወደ ሚዶኒ ምድር እስከሚደርሱም እንኳን ከየቤታቸው ወደቤትና፣ ከቦታ ቦታ አስወጡአቸው፤ ከእዚያም ተወሰዱና ወደ ወህኒ ቤት ተጣሉም፣ በጠንካራ ገመድ ታሰሩም፣ እናም ለብዙ ቀናት በወህኒ ቤት ቆዩና በላሞኒና በአሞን ተለቀቁ።