ምዕራፍ ፳፭
የላማናውያን ወረራ ተስፋፋ—አቢናዲ እንደተነበየው የኖህ ካህናት ዝርያዎች ጠፉ—ብዙ ላማናውያን ተለወጡ፣ እናም ከአንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ሰዎችን ጋር ተቀላቀሉ—በክርስቶስ አመኑ እናም የሙሴን ህግ ጠበቁ። ከ፺–፸፯ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እነሆ፣ አሁን እንዲህ ሆነ ላማናውያን ወንድሞቻቸውን በመግደላቸው ይበልጥ ተናደዱ፤ ስለዚህ በኔፋውያን ላይ ለበቀል ማሉ፤ እናም በዚያን ጊዜ የአንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ሰዎችን ለመግደል ሙከራ አላደረጉም ነበር።
፪ ነገር ግን ወታደሮቻቸውን ወሰዱና፣ ወደ ዛራሔምላ ምድር ዳርቻ ሄዱ፣ እናም በአሞኒሀ ምድር ያሉትን ሰዎች አጠቁአቸው፣ እናም አጠፉቸው።
፫ እናም ከዚያን በኋላ ከኔፋውያን ጋር ብዙ ውጊያ ነበራቸው፣ በዚህም ተባረሩበትና ተገደሉበት።
፬ እናም ከተገደሉት ላማናውያን መካከል የአሙሎንና የወንድሞቹ ዘሮች፣ የኖህ ካህናት የነበሩት ናቸው፣ እናም በኔፋውያን እጅ ነበር የተገደሉት፤
፭ እናም ቀሪዎቹ፣ በስተምስራቅ በኩል በምድረበዳው ከሸሹ በኋላ፣ እናም በላማናውያን ላይ ኃይላቸውንና ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመያዛቸው፣ በርካታ ላማናውያን በእምነታቸው የተነሳ በእሳት እንዲጠፉ ተደረገ—
፮ ለብዙዎቹ፣ ብዙ ጥፋት ከደረሰባቸው እናም ከተሰቃዩ በኋላ፣ አሮንና ወንድሞቹ በምድራቸው የሰበኩትን ቃል ማስታወስ ጀመሩ፤ ስለዚህ የአባቶቻቸውንም ወግ አለማመንና፣ በጌታ በማመን፣ እናም ለኔፋውያን ታላቅ ኃይልን እንደሰጣቸው ማመን ጀመሩ፤ እናም እንደዚህ ብዙዎች በምድረበዳው ውስጥ ተለውጠው ነበር።
፯ እናም እንዲህ ሆነ የአሙሎን ልጆች ቅሪት የሆኑት ገዢዎች፣ እነርሱ፣ አዎን፣ በእነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚያምኑት እንዲገደሉ አደረጉ።
፰ እንግዲህ ይህ ሰማዕት ብዙዎች ወንድሞቻቸውን በቁጣ እንዲታወኩ አደረገ፤ እናም በምድረበዳው ፀብ ተጀመረ፤ ላማናውያንም የአሙሎንን ዘር ማደንና፣ መግደል ጀመሩ፤ እናም በምድረበዳው በስተምስራቅ በኩል ሸሹ።
፱ እናም እነሆ በዚህን ጊዜ እነርሱ በላማናውያን ታደኑ። ስለዚህ አቢናዲ በእሳት እንዲሞት ዘንድ ስላደረጉት የካህናቱ ዘሮች በተመለከተ የተናገረው ቃል ተፈፀመ።
፲ በእኔ ላይ የምታደርጉት ነገር ወደፊት ሊመጣ ያለው ነገር ምሳሌ ነው በማለት ተናግሮአቸው ነበርና።
፲፩ እናም እንግዲህ ለእግዚአብሔር ባለው እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሞትን በእሳት እንዲቀጣ የተደረገው አቢናዲ ነበር፤ አሁን እርሱ ይህን ማለቱ ነበር፣ እርሱ እንደተሰቃየው ብዙዎች በእሳት ሞት ይሰቃያሉ።
፲፪ እናም ለኖህ ካህናትም ዘሮቻቸው እርሱን እንዳደረጉት ብዙዎችን በእሳት እንደሚገድሉ፣ እናም ልክ እረኛ የሌላቸው በጎች እንደሚባረሩትና በዱር አውሬዎች እንደሚበሉት ወደሌላ ሀገርም እንደሚበታተኑና እንደሚገደሉ ነገራቸው፤ እናም አሁን እነሆ፣ ዘሮቻቸው በላማናውያን በመባረራቸው፣ በመታደናቸውና በመመታታቸው እነዚህ ቃላት ተረጋግጠው ነበር።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን ኔፋውያንን ማሸነፍ አለመቻላቸውን በተመለከቱ ጊዜ ወደራሳቸው ምድር ተመለሱ፤ እናም ብዙዎች በእስማኤል ምድርና በኔፊ ምድር ለመኖር ሄዱ፣ እናም አንቲ-ኔፊ-ሌሂዎች ከነበሩትም የእግዚአብሔር ሰዎች ጋር ተቀላቀሉ።
፲፬ እናም ወንድሞቻቸው እንዳደረጉት የጦር መሳሪያዎቻቸውን ቀበሩና፣ ፃድቃን ህዝብም መሆን ጀመሩ፤ እናም በጌታ ጎዳና ተራመዱና፣ ትዕዛዛቱንና ህግጋቱን ጠበቁ።
፲፭ አዎን፣ እናም የሙሴን ህግ ጠብቀዋል፤ በአሁኑም ጊዜ ሁሉም ስላልተፈፀመ የሙሴን ህግ መጠበቅ አስፈላጊ ነበርና። ነገር ግን የሙሴ ህግ ቢኖርም የክርስቶስን መምጣት ይጠባበቁ ነበር፣ ምክንያቱም የሙሴ ህግ የመምጣቱ ምልክት መሆኑን አስበው ስለነበር፣ እናም ክርስቶስም ለእነርሱ እስከሚገለጥ ድረስ የውጪአዊውን ሥርዓታቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ስለሚያምኑ ነው።
፲፮ እንግዲህ ደህንነትም በሙሴ ህግ እንደሚመጣ አልገመቱም፤ ነገር ግን የሙሴ ህግ በክርስቶስ ያላቸውን እምነት ያጠነክራል፤ እናም እነዚያ ነገሮች ይመጣሉ ብሎ በተናገረው በትንቢት መንፈስ ተስፋ በማድረግ፣ በእምነታቸው የዘለዓለማዊውን ደህንነት ተስፋ ያደርጋሉ።
፲፯ እናም አሁን እነሆ አሞንም፣ አሮንም፣ ኦምነርም፣ ሒምኒም፣ እናም ወንድሞቻቸው በላማናውያን መካከል ድልን ስላገኙ፣ ጌታም እንደፀሎታቸው ስለሰጣቸውና ቃሉን ደግሞ በዝርዝር ስላረጋገጠላቸው እጅግ ተደሰቱ።