ምዕራፍ ፵፱
ወራሪ ላማናውያን የአሞኒሀንና የኖህን የምሽግ ከተማዎች ለመያዝ አልቻሉም—አማሊቅያ እግዚአብሔርን ረገመ፣ እናም የሞሮኒን ደም ለመጠጣት ማለ—ሔለማንና ወንድሞቹ ቤተክርስቲያኗን ማጠናከር ቀጠሉ። በ፸፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ በአስራ ዘጠነኛው ዓመት አስራ አንደኛ ወር፣ በወሩ አስረኛ ቀን፣ የላማናውያን ወታደሮች ወደ አሞኒሀ ምድር እንደቀረቡ ታዩ።
፪ እናም እነሆ፣ ከተማዋ በድጋሚ ተገንብታ ነበር፣ ሞሮኒም በከተማዋ ዳርቻ ሠራዊቱን አስፍሯል፣ እናም በዙሪያቸው ከላማናውያን ጦርና ድንጋይ የሚጋርዳቸውን አፈር ቆልለዋል፤ እነሆም፣ በድንጋይና በጦር ይዋጉ ነበርና።
፫ እነሆ የአሞኒሀ ከተማ ድጋሚ ተሰርታ ነበር ብያለሁ። እንዲህ እላችኋለሁ፤ አዎን፣ ግማሹ ክፍል በድጋሚ ተሰርቶ ነበር፤ እናም ላማናውያን ከህዝቡ ክፋት የተነሳ አንዴ አጥፍተውት ስለነበር በድጋሚ በቀላሉ የሚያዝ ነው በማለት ገምተው ነበር።
፬ ነገር ግን እነሆ፣ ቁጣቸው ምን ያህል ታላቅ ነበር፤ እነሆም፣ ኔፋውያን በዙሪያቸው ያለውን ተረተር ቆፍረው ቆለሉ፣ ይህም ትልቅ በመሆኑ ላማናውያን በዚህ ላይ ጥቃትን ይፈፅሙ ዘንድ ድንጋይ እናም ጦር ለመወርወር አልቻሉም፣ መግቢያቸው በኩል ካልሆነም በቀር በእነርሱ ላይ ለመምጣትም አልቻሉም ነበር።
፭ እንግዲህ በዚህ ጊዜ የላማናውያን ዋና ሻምበል፣ ኔፋውያን የስፍራቸውን ደህንነት ለማዘጋጀት ባደረጉት ጥበብ እጅግ ተደንቆ ነበር።
፮ እንግዲህ የላማናውያን መሪዎች በቁጥር ብዙ በመሆናቸው፣ አዎን ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት በእነርሱ ላይ ለመምጣት እድሉን ለመጠቀም እንችላለን ብለው ገምተው ነበር፤ አዎን፣ እናም ደግሞ በጋሻዎችና፣ በደረት ኪሶቻቸው እራሳቸውን አዘጋጅተው ነበር፤ እናም ደግሞ ከቆዳ በተሰሩ ልብሶች፣ አዎን፣ እርቃናቸውን በሚሸፍኑላቸው ወፍራም ልብሶች፣ እራሳቸውን አዘጋጅተው ነበር።
፯ እናም እንደዚህ በመዘጋጀታቸውም በቀላሉ ወንድሞቻቸውን እንደሚያሸንፉና በባርነት ቀንበር ስር እንደሚያደርጉ፣ ወይም እንደፍላጎታቸውም እንደሚገድሉአቸውና እንደሚጨፈጭፏቸው ገምተዋል።
፰ ነገር ግን እነሆ፣ በከፍተኛ ሁኔታ እስከሚገርማቸው ድረስ በሌሂ ልጆች መካከል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተዘጋጅተው ነበር። እንግዲህ በሞሮኒ ትዕዛዝም መሰረት ለጦርነቱ በላማናውያን ላይ ተዘጋጅተው ነበር።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን፣ ወይንም አማሊቅያውያን በአንደዚህ ዓይነቱ የጦርነት ዝግጅት እጅግ ተገርመው ነበር።
፲ እንግዲህ ንጉስ አማሊቅያ ከኔፊ ምድር ከሠራዊቱ ፊት የሚመጣ ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባት ላማናውያን የኔፋውያንን አሞኒሀ ከተማ እንዲያጠቁ ያደርግ ነበር፣ እነሆ እርሱ ለህዝቡ ደም ምንም ደንታ የለውምና።
፲፩ ነገር ግን እነሆ፣ አማሊቅያ እራሱ ወደ ጦርነቱ አልመጣም። እናም እነሆ፣ ዋናው ሻምበሉ በአሞኒሀ ከተማ ኔፋውያንን ለማጥቃት አልደፈረም፤ ሞሮኒ በኔፋውያን የሚደረጉትን ጉዳዮች በመቀየሩ፣ ላማናውያን በአፈገፈጉበት ስፍራ ተቆጥተውና በእነርሱ ላይ ለመምጣት አልቻሉም ነበር።
፲፪ ስለዚህ ላማናውያን ወደ ምድረበዳው አፈገፈጉ፣ እናም የጦር ስፍራቸውን ወሰዱና፣ በሁለተኛ ደረጃ ኔፋውያንን ለማጥቃት የሚመች ጥሩ ስፍራ ብለው ወደ ገመቱት የኖህ ምድር ቀጠሉ።
፲፫ ላማናውያን ሞሮኒ ም ሆነ፣ የደህንነት ምሽግ በምድሪቱ ሁሉ ባሉት እያንዳንዱ ከተማ ዙሪያ መመሸጉን አላወቁም ነበር፤ ስለዚህ፣ በቆራጥ ውሳኔ ወደ ኖህ ምድር ዘመቱ፤ አዎን፣ የላማናውያን ዋና ሻምበል መጣ፣ እናም የከተማዋን ህዝብ ለማጥፋት መሃላ አደረገ።
፲፬ ነገር ግን እነሆ፣ በሚገርማቸው ሁኔታ፣ የኖህ ከተማ፣ ደካማ ስፍራ የነበረችው፣ አሁን፣ በሞሮኒ አማካኝነት፣ ጠንካራ ሆነች፣ አዎን፣ ከአሞኒሀም ከተማ እንኳን በመብለጥ ጠንካራ ሆነች።
፲፭ እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ ይህ በሞሮኒ የነበረ ብልህ ሁኔታ ነበር፤ ምክንያቱም እነርሱ በአሞኒሀ ከተማ ይፈራሉ፤ እናም እስከአሁን የኖህ ከተማ የምድሪቱ ደካማው ክፍል በመሆኑ፣ ስለዚህ በዚያ ስፍራ ለመዋጋት ይሄዳሉ ብሎ ገምቶ ነበር፣ ይህም ነገር የሆነው ሞሮኒ እንደተመኘው ነበር።
፲፮ እናም እነሆ፣ ሞሮኒ ሌሂን በከተማዋ ላይ ዋና ሻምበል በማድረግ ሾሞት ነበር፤ እናም በሲዶም ወንዝ በስተምስራቅ ባለው ሸለቆም ከላማናውያን ጋር የተዋጋው ይኸው ሌሂ ነበር።
፲፯ እናም እንግዲህ እነሆ እንዲህ ሆነ፣ ሌሂ ከተማዋን ማስተዳደሩን ላማናውያን ባወቁ ጊዜ በድጋሚ ተቆጡ፣ ምክንያቱም ሌሂን እጅግ ይፈሩት ነበር፤ ይሁን እንጂ ዋናው ሻምበላቸው ከተማዋን ለማጥቃት መሃላ ምሎ ነበር፤ ስለዚህ፣ እነርሱም ሠራዊታቸውን አምጥተው ነበር።
፲፰ እንግዲህ እነሆ፣ ላማናውያን የተገነባው ግንብ ረጅም በመሆኑ፣ እናም በዙሪያው የተቆፈረው ኩሬ ጥልቅ በመሆኑ በመግቢያው በኩል ካልሆነ በቀር ወደ ደህንነታቸው ምሽግ በሌላ መንገድ መግባት አልቻሉም።
፲፱ እናም ኔፋውያን ወደ ምሽጉ ላይ ድንጋይና ቀስቶቻቸውን በመጣል በማንኛውም መንገድ ለመውጣት የሚሞክሩ ሰዎችን ሁሉ ለማጥፋት ተዘጋጅተው ነበር።
፳ ስለዚህም፣ አዎን፣ ጠንካራ ሰዎቻቸውም፣ በጎራዴዎቻቸው እናም በወንጭፎቻቸው፣ በመግቢያው በኩል ወደ ደህንነት ቦታቸው ለመምጣት የሚሞክሩትን ሁሉ ለመምታት ተዘጋጅተው ነበር፤ እናም ከላማናውያን እራሳቸውን ለመከላከል እንደዚህ ተዘጋጅተው ነበር።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ሻምበሎች ወታደሮቻቸውን መግቢያው በር ድረስ አምጥተዋቸው ነበር፣ እናም ወደ ደህንነት ስፍራቸውን ለመግባት ከኔፋውያን ጋር መጣላት ጀመሩ፤ ነገር ግን እነሆ፣ በኃይል እስከሚገደሉም ድረስ በተደጋገመ ጊዜ ወደኋላ እንዲሸሹ ተደርገዋል።
፳፪ እንግዲህ በመግቢያው በኩል በኔፋውያን ላይ ድል መቀዳጀት አለመቻላቸውን ባወቁ ጊዜ፣ ወደሰራዊታቸው መድረስ ይችሉ ዘንድ ለመዋጋትም እኩል እድል እንዲያገኙ ምሽጎቻቸውን ቆፈሩት፤ ነገር ግን እነሆ፣ በዚህ ሙከራቸው በላያቸው ላይ በተወረወረባቸው ድንጋይና የጦር ቀስት ተደመሰሱ፤ እናም አፈሩን በመግፋት ጉድጓዱን ከመሙላት ይልቅ በተወሰነ ደረጃ በቆሰሉና በሞቱ ሰዎች ጉድጓዱን ሞሉት።
፳፫ ኔፋውያን በጠላቶቻቸው ላይ ሁሉ እንዲህ ሀይል ነበራቸው፤ እናም ላማናውያን ዋና ሻምበሎቻቸው በሙሉ እስከሚገደሉ ድረስ ኔፋውያንን ለማጥፋት ሞከሩ፤ አዎን፣ እናም ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ላማናውያን ተገደሉ፤ በሌላ መልኩ፣ ከኔፋውያን አንድም ነፍስ እንኳን አልጠፋም ነበር።
፳፬ በመግቢያው በኩል ለላማናውያን ቀስቶች የተጋለጡ ሀምሳ የሚጠጉ ሰዎች ቆስለው ነበር፤ ነገር ግን በጋሻዎቻቸው፣ እናም በደረት ኪሶቻቸውና፣ በቆቦቻቸው ተከልለው ስለነበር፣ ቁስሎቻቸው ሁሉ በእግሮቻቸው ላይ ነበር፣ ብዙዎቹም በጣም ቆስለው ነበር።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ፣ ዋና ሻምበሎቻቸው በሙሉ መገደላቸውን ላማናውያን በተመለከቱ ጊዜ ሁሉም ወደ ምድረበዳው ሸሹ። እናም እንዲህ ሆነ፣ በትውልዱ ኔፋውያን ለሆነው አማሊቅያ ንጉሳቸው ስለታላቁ ሽንፈታቸው ለመናገር ወደ ኔፊ ምድር ተመለሱ።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም በኔፋውያን ላይ ፍላጎቱን ባለማግኘቱ በህዝቡ እጅግ ተቆጥቶ ነበር፤ እርሱም በባርነት ቀንበር ስር እንዲሆኑ አላደረጋቸውም ነበር።
፳፯ አዎን፣ እጅግ ተቆጥቶ ነበር፣ እናም እግዚአብሔርንና፣ ደግሞ ሞሮኒን ረገመ፣ ደሙንም እጠጣለሁ ብሎ መሃላ ፈፅሞ ነበር፤ እናም ይህም የሆነው ለህዝቡ ደህንነት ሲል ሞሮኒ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቁ ነበር።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ በሌላ መልኩ የኔፊ ህዝብ ወደር በሌለው ኃይሉ ከጠላቶቻቸው እጅ ስላስለቀቃቸው ጌታ አምላካቸውን አመሰገኑ።
፳፱ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ የአስራ ዘጠነኛው የንግስ ዘመን ተፈፀመ።
፴ አዎን፣ እናም በሔለማንና፣ በሺብሎን፣ እናም በቆሪያንቶንና፣ በአሞን እንዲሁም በወንድሞቹ፣ አዎን፣ እናም በንስሀ በመጠመቅና ከህዝቡ መካከል እንዲሰብኩ በተላኩት በቅዱሱ የእግዚአብሔር ስርዓት በተሾሙት ሁሉ የታወጁትን የእግዚአብሔር ቃላት በትህትና ስላዳመጡ በህዝብ መካከል የማያቋርጥ ሰላም፣ እናም በቤተክርስቲያኗ እጅግ ታላቅ ብልፅግና ነበር።