ምዕራፍ ፶
ሞሮኒ ለኔፋውያን ምድር ምሽግ አደረገ—ኔፋውያን ብዙ አዳዲስ ከተሞችን ሰሩ—በኔፋውያን ላይ በክፋታቸውና በእርኩሰታቸው ዘመን ጦርነትና ጥፋት አረፈባቸው—ሞሪያንተንና ተቃዋሚዎቹ በቴአንኩም ተሸነፉ—ኔፋአያህ ሞተ፣ እናም ልጁ ፓሆራን የፍርድ ወንበሩን ያዘ። ከ፸፪–፷፯ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ለጦርነት መዘጋጀቱንም ሆነ ህዝቡን ከላማናውያን መከላከሉን አላቆመም፤ በመሣፍንቱ ሀያኛ ዓመት የንግስና ዘመን መጀመሪያ ወታደሮቹ እንዲጀምሩ በማድረጉ፣ በኔፋውያን የተያዙትን ምድር ሁሉ የተቆለለውን አፈር በከተማው ዙሪያ መቆፈር እንዲጀምሩ አደረገ።
፪ እናም በተቆለለው አፈር በጫፉ ላይ ግንድ እንዲሆን አደረገ፤ አዎን፣ በከተማው ዙሪያ በሰው ቁመት የተሰራ የእንጨት አጥር እንዲሆን አደረገ።
፫ ከእንጨት በተሰራው ላይ በግንዱ ዙሪያ ሹል እንጨት እንዲሰራ አደረገ፤ እናም የሾለው እንጨት ጠንካራና ከፍ ያለ ነበር።
፬ እናም በሹል እንጨት የተሰሩትን እንዲከልሉ ምሶሶ እንዲቆም አደረገ፤ እናም የላማናውያን ድንጋይና ቀስቶች የሞሮኒን ወታደሮች መምታት እንዳይችሉ በማማዎቹ ላይ የጥበቃ ስፍራ እንዲሆን አደረገ።
፭ እናም ማማው እንደ ፍላጎታቸውና ብርታታቸው፣ በከተማዋ ግንብ ለመጠጋት የሞከሩትን ለመግደል ከላይ ሆነው ድንጋይ ለመወርወር እንዲችሉ ሆኖ ነበር የተዘጋጀው።
፮ በምድሪቱ ሁሉ ባሉት ከተሞች ዙሪያ ሞሮኒ ጠላቶችን ለመከላከል ጠንካራ ምሽግ እንደዚህ አዘጋጅቶ ነበር።
፯ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ወታደሮቹ በምድረበዳው ወደ ምስራቅ እንዲሄዱ አደረገ፤ አዎን፣ እናም በራሳቸው ምድር በስተምስራቅ በምድረበዳው የነበሩትን ላማናውያን ሁሉ በዛራሔምላ ምድር በስተደቡብ ወደነበረው ወደራሳቸው ምድር አስወጡአቸው።
፰ እናም የኔፊ ምድር ከምስራቅ ባህር እስከ ምዕራብ ባህር ድረስ በቀጥተኛ መንገድ የተቋቋመ ነበር።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ላማናውያንን በስተሰሜን ከነበረው ርስታቸው ሁሉ በምስራቅ በኩል ከምድረበዳው ባስወጣቸው ጊዜ፣ በዛራሔምላ ምድር የሚኖሩ ነዋሪዎችንና በምድሪቱ ዙሪያ ያሉትን በስተምስራቅ በምድረበዳው እስከ ባህሩ ዳርቻ ድረስም እንኳን እንዲጓዙ እናም ምድሪቱን እንዲወርሱ አደረገ።
፲ እናም ደግሞ በስተደቡብ በራሳቸው ምድር ዳርቻ ሠራዊቱን አስቀመጠና፣ ከጠላቶቻቸው እጅ ወታደሮቹንና ህዝቡን ይጠብቅ ዘንድ ምሽግ እንዲሰሩ አደረገ።
፲፩ እናም በምድረበዳው በምስራቅ እናም ደግሞ በስተምዕራብ በኩል የላማናውያን ጠንካራ ምሽጎችን አጠፋ፣ አዎን፣ በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል፣ በዛራሔምላ ምድርና በኔፊ ምድር መካከል፣ ከባህሩ ከምዕራብ ጀምሮ እስከሲዶም ወንዝ ጫፍ መሸገ—ኔፋውያን በሰሜን በኩል ያለውን መሬት በሙሉ፣ አዎን፣ እንደፍላጎታቸውም ከለጋስ ምድር በስተሰሜን በኩል ያለውን ምድር በሙሉ ያዙ።
፲፪ ሞሮኒ በየቀኑ በቁጥር ከሚጨምሩት ሠራዊቶቹ ጋር፣ ስራው ለእነርሱ የጥበቃ ማረጋገጫ በመሆኑ፣ ላማናውያንን ከራሳቸው ምድር በምድራቸውም ባሉት ሀብቶቻቸው ላይ ስልጣን እንዳይኖራቸው ጉልበታቸውን፣ እናም ስልጣናቸውን ለማጥፋት ፈለገ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን የከተማዋን መሰረት ጀመሩና፣ የከተማዋንም ስም ሞሮኒ ብለው ጠሯት፤ እናም ይህ በባህሩ በስተምስራቅ በኩል ነበር፤ እናም በላማናውያን ይዞታ ሥር በሆነው በደቡብ ዳርቻ ነበር።
፲፬ እናም ደግሞ የአሮንንና የሞሮኒን ወሰን የሚያገናኘውን በሞሮኒና በአሮን ከተማ መካከል የከተማ መሰረትን ጀመሩ፤ እናም የከተማዋን ወይም የምድሪቱን ስም ኒፋአያህ ብለው ጠሯት።
፲፭ እናም ደግሞ በዚያው ዓመት በስተሰሜን በኩል ብዙ ከተሞችን መስራት ጀመሩ፣ አንድ በተለየ ሁኔታ የሰሩትን ሌሂ ብለው ጠሩት፣ ይህም በባህሩ ሰርጥ ዳርቻ በስተሰሜን በኩል ነበር።
፲፮ እናም ሀያኛው ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ።
፲፯ እናም በመሣፍንቱ ሀያ አንደኛ ዓመት መጀመሪያ የንግስና ዘመን ላይ የኔፊ ህዝብ በእንደዚህ ዓይነት ብልጽግና ላይ ነበር።
፲፰ እናም እጅግ በለፀጉ፣ እናም እጅግም ሀብታም ሆኑ፣ አዎን፣ እናም በምድሪቱ ላይ ተባዙና በረቱ።
፲፱ እናም ጌታ ለሰው ልጆች ያደረገውን ቃል በሙሉ ለመፈፀም እንዴት መሀሪና ፍትሀዊ እንደሆነ እንመለከታለን፤ አዎን፣ ለሌሂ በዚህ ጊዜም እንኳን ቢሆን፣ እንዲህ ብሎ የተናገራቸው ቃላት የተረጋገጡ መሆናቸውን ለመመልከት እንችላለን፥
፳ አንተ እና ልጆችህ የተባረካችሁ ናችሁ፤ እናም እነርሱ የተባረኩ ይሆናሉ፣ ትዕዛዛቴንም እስከጠበቁ ድረስ በምድሪቱ ላይ ይበለፅጋሉ። ነገር ግን ትዕዛዛቴን እስካልጠበቁ ድረስ ከጌታ ፊት እንደሚለዩ አስታውሱ።
፳፩ እናም እነዚህ ቃል ኪዳኖች ለኔፊ ህዝብ እውነትነታቸው እንደሚረጋገጥ እናያለን፤ ይህ በመካከላቸው የነበረው ፀብና ጥል፤ አዎን፣ ግድያቸውና፣ ዝርፊያቸው፣ ጣኦት አምላኪነታቸውና፣ እርኩሰታቸው በእነርሱም ላይ ጦርነትና ጥፋትን አምጥቶባቸው ነበርና።
፳፪ እናም በሺህ የሚቆጠሩ ኃጢአተኞች ወንድሞቻቸው በባርነት በተመደቡ፣ ወይም በጎራዴ በጠፉ፣ ወይም እምነት አጥተው በመነመኑ፣ እናም ከላማናውያን ጋር በተቀላቀሉ ጊዜ የጌታን ትዕዛዛት በመጠበቅ ታማኝ የነበሩት እነዚያ በሁሉም ጊዜ ድነዋል።
፳፫ ነገር ግን እነሆ እንደሞሮኒ ጊዜ አዎን፣ በመሣፍንቱ በሀያ አንደኛ የንግስና ዘመን በዚህ ጊዜም እንኳን፣ ከኔፊ ጊዜ ጀምሮ በኔፊ ሰዎች መካከል በጭራሽ እንዲህ ያለ ደስታ አልነበረም።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ የመሣፍንቱ ሀያ ሁለተኛ የንግስና ዘመንም እንዲህ በሰላም ተፈፀመ፤ አዎን፣ እናም ደግሞ ሀያ ሶስተኛው ዓመት።
፳፭ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሀያ አራተኛ የንግስና ዘመን መጀመሪያ ላይ፣ በሌሂ ምድር ዳርቻ ላይ ተገጣጥመው በነበሩት የሌሂን ምድር እና የሞሪያንተንን ምድር በተመለከተ በኔፊ ህዝብ መካከል በተፈጠረው ፀብ ባይሆን ኖሮ በኔፊ ህዝብ መካከል ሰላም በሆነ ነበር፤ ሁለቱም በባህሩ ሰርጥ ዳርቻ ነበሩ።
፳፮ እነሆም፣ የሞሪያንተንን ምድር የራሳቸው ያደረጉት ሰዎች ከሌሂ ምድር ትንሹን ክፍል ይገባናል ብለው ነበር፤ ስለዚህ የሞሪያንተን ህዝብ በወንድሞቻቸው ላይ ጦር እስኪያነሱ ድረስ በመካከላቸው የጋለ መጣላት ተጀምሮ ነበር፣ እናም በጎራዴዎቻቸው እነርሱን ለመግደል ቆርጠው ነበር።
፳፯ ነገር ግን እነሆ፣ የሌሂን ምድር የያዙት ሰዎች ወደ ሞሮኒ የጦር ሰፈር ሸሹ፣ እናም እርዳታን ለማግኘት ለእርሱ አቤት አሉ፤ እነሆ አልተሳሳቱም ነበርና።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ፣ ሞሪያንተን ተብሎ በሚጠራው ሰው የተመሩት የሞሪያንተን ህዝብ፣ የሌሂ ህዝብ ወደ ሞሮኒ የጦር ሰፈር መሸሻቸውን ባወቁ ጊዜ፣ የሞሮኒ ወታደሮች በእነርሱ ላይ እንደሚመጡ እናም እንዳያጠፉአቸው እጅግ ፈርተው ነበር።
፳፱ ስለዚህ፣ ሞሪያንተን ወደሰሜን በትልቅ ውኃ ወደተሸፈነው ስፍራ እንዲሸሹ እናም በስተሰሜን በኩል ያለውን መሬት እንዲይዙ ልባቸውን አነሳሳ።
፴ እናም እነሆ፣ ይህንን ዕቅድ (ለሃዘን ምክንያት ይሆን የነበረውን) እንዲፈፀም ማድረግ ይችሉ ነበር፣ ነገር ግን እነሆ፣ ሞሪያንተን ስሜታዊ ስለነበር፣ እነሆም በአንዲት ገረዱ ተቆጣ፣ እናም ክፉኛ መታት።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ እርሷ ሸሸችና፣ ወደ ሞሮኒ የጦር ሰፈር መጣች፣ እናም የሆነውን ሁሉ በተመለከተና፣ ደግሞ ወደ ሰሜን ለመሸሽ ያላቸውን ሙከራ ለሞሮኒ ነገረችው።
፴፪ እንግዲህ በለጋስ ወይም በሞሮኒ የነበሩ ሠዎች የሞሪያንተንን ቃል በመስማት እናም ከህዝቡም ጋር ይቀላቀላሉ፣ እናም ከኔፋውያን ጋር የከፋ ሁኔታን ሊያስከትል የሚችል የምድር ክፍሎችን ያገኛሉ፣ አዎን፣ ውጤቱም ለነፃነታቸው ውድቀት መንስኤ ሊሆን የሚችል ነው ብለው ፈርተው ነበር።
፴፫ ስለዚህ ሞሮኒ፣ ከጦር ሰፈራቸው፣ የሞሪያንተንን ሰዎች እርምጃ ለማቋረጥ፣ ወደ ሰሜን ክፍል እንዳይሸሹም ለማቆም ወታደር ላከ።
፴፬ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ወደመው ምድር ወሰን እስከሚመጡ ድረስ አላቋረጧቸውም ነበር፤ እናም በምድሪቱ ሰሜን በኩል በቀጭኑ የባህሩ ማለፊያ በኩል አዎን፣ በባህሩ በኩል በስተምዕራብና በስተምስራቅ በኩል እርምጃቸውን አቋረጡ።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ በሞሮኒ የተላኩት ሠራዊቶች፣ ቴአንኩም ተብሎ በሚጠራ ሰው የተመሩት፣ የሞሪያንተንን ህዝብ አገኙ፤ እናም የሞሪያንተንም ህዝብ ግትር ነበር፣ በእርሱ (በኃጢአተኛና በሸንጋይ ቃላቱ በመቀስቀሳቸው የተነሳ) ጦርነቱም በመካከላቸው ሆነ፣ በዚያም ቴአንኩም ሞሪያንተንን ገደለውና፣ ወታደሮቹን አሸነፈ፣ እናም በምርኮም ወሰዱአቸውና፣ ወደ ሞሮኒ የጦር ሰፈር ተመለሱ። እናም በዚሁ የመሣፍንቱ ሀያ አራተኛው የንግስና ዘመን በኔፊ ህዝብ ላይ ተፈፀመ።
፴፮ እናም የሞሪያንተንን ህዝብ እንደዚህ ነበር የተመለሱት። እናም ሰላሙን ለመጠበቅ ቃል ኪዳን ከገቡ በኋላ ወደ ሞሪያንተን ምድር ተመለሱና፣ በእነርሱና በሌሂ ህዝብ መካከል አንድነት ሆነ፤ እናም ደግሞ የሌሂ ህዝብ ወደራሳቸው ምድር ተመለሱ።
፴፯ እናም እንዲህ ሆነ የኔፊ ህዝብ ሰላምን መልሰው በመሰረቱበት በዚሁ ዓመት፣ በእግዚአብሔር ፊት ፍፁም ትክክል በሆነ ሁኔታ የፍርድ ወንበሩን ቦታ ይዞ የነበረው ሁለተኛው ዋና ዳኛም ኒፋአያህ ሞተ።
፴፰ ይሁን እንጂ፣ እናም በአልማና በአባቱ ከሁሉም ነገር በላይ ቅዱስ ተደርገው የተገመቱትን መዝገቦች ከአልማ አልቀበልም ብሎ ነበር፤ ስለዚህ አልማ እነዚህን ነገሮች ለልጁ ሔለማን ሰጠው።
፴፱ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ የኒፋአያህ ልጅ በአባቱ ቦታ የፍርድ ወንበሩን እንዲይዝ ተመደበ፤ አዎን በትክክል እንዲፈርድና፣ ሰላምንና፣ የህዝቡን ነፃነት እንዲጠብቅ፣ እናም ጌታ አምላካቸውን ለማምለክ ቅዱስ የሆነውን ልዩ መብታቸውን እንዲፈቅድላቸው፣ አዎን፣ በጊዜው ሁሉ እግዚአብሔርን ምክንያት እንዲደግፍና እንዲከላከል፣ እናም ኃጢአተኞችን እንደወንጀላቸው ወደ ፍርድ ለማምጣት፣ በመሀላና፣ በቅዱስ ስርዓት ዋና ዳኛ በመሆንና፣ በህዝቡ ላይ ገዢ ሆኖ ተሹሞ ነበር።
፵ እንግዲህ እነሆ፣ ስሙም ፓሆራን ተብሎ ይጠራ ነበር። እናም ፓሆራን የአባቱን ወንበር ያዘና፣ በሀያ አራተኛ ዓመት መጨረሻም በኔፊ ህዝብ ላይ የንግስናውን ዘመን ጀመረ።