ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፷፫


ምዕራፍ ፷፫

ሺብሎን እናም በኋላ ሔለማን ቅዱሳን መፃሕፍቶቹን ወሰዱ—በርካታ ኔፋውያን ወደ ሰሜኑ ምድር ተጓዙ—ሐጋዝ በባህሩም በስተምዕራብ በኩል የሔዱትን መርከቦች ሰራ—ሞሮኒሀ ላማናውያንን በውጊያ አሸነፋቸው። ከ፶፮–፶፪ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሰላሳ ስድስተኛ ዓመት የንግስና ዘመን በአልማ ለሔለማን የተሰጡትን ቅዱሳን ነገሮችን ሺብሎን ተረከባቸው።

ሺብሎንም ፃድቅ ሰው ነበር፣ እናም በእግዚአብሔር ፊትም በቅንነት ይራመድ ነበር፤ እናም ያለማቋረጥ እርሱም፣ ደግሞ ወንድሙም፣ መልካም ለመስራት የጌታ አምላካቸውን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ጥረት ያደርጉ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒም ሞተ። የመሣፍንቱ ሰላሳ ስድስተኛ የንግስና ዘመንም እንደዚህ ተፈፀመ።

እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሰላሳ ሰባተኛ የንግስና ዘመን ብዙ ሰዎች፣ እንዲሁም በአንድነት ወደ አምስት ሺህ አራት መቶ የሚጠጉ፣ ከሚስቶቻቸው እናም ከልጆቻቸው ጋር ከዛራሔምላ ምድር ወጥተው በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ ሀጋዝ፣ እጅግ ትጉህ ሰው ስለነበር፣ ስለዚህ ሄደና በወደመው ስፍራ በለጋስ ምድር ዳርቻ እጅግ ታላቅ የሆነ መርከብ ሰራ፤ እናም በቀጭኑ በምድሪቱ በስተሰሜን በሚያመራው መንገድ ወደ ምዕራብ ባህር ላከው።

እናም እነሆ፣ በውስጡ የገቡና ብዙ ስንቅ ይዘውም የተጓዙ ብዙ ኔፋውያን፣ እናም ሴቶችና ልጆች ነበሩ፣ ጉዞአቸውንም ወደ ሰሜን አቅጣጫ አደረጉ። እናም ሰላሳ ሰባተኛው ዓመት ተፈፀመ።

እናም በሰላሳ ስምንተኛው ዓመት ይህም ሰው ሌላ መርከቦችን ሰራ። እናም ደግሞ የመጀመሪያዋ መርከብ ተመለሰችና፣ ከዚህ የበለጡ ብዙ ሰዎችም ገቡባት፤ እናም እነርሱ ደግሞ ብዙ ስንቅ ያዙና፣ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል በድጋሚ ተላኩ።

እናም እንዲህ ሆነ ከዚህ በኋላ ስለእነርሱ ምንም አልተሰማም ነበር። በጥልቅ ባህሩ ውስጥ ሰጥመዋል ብለን ገምተንም ነበር። እናም እንዲህ ሆነ ሌላኛዋ መርከብም ሄደች፤ እርሷም የት እንደደረሰችም አላወቅንም ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ በዚህ ዓመት በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል የሄዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ። እናም ሰላሳ ስምንተኛው ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ።

እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሰላሳ ዘጠነኛ የንግስና ዘመን፣ ሺብሎንም ሞተ፣ እናም ወደዚያች ምድር ለሄዱት ሰዎች ስንቅ ለመውሰድ ቆሪያንቶን በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል በመርከብ ሄደ።

፲፩ ስለዚህ ሺብሎን ከመሞቱ በፊት ለሔለማን ልጅ፣ በአባቱ ስም ሔለማን ተብሎ ለሚጠራው፣ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች መስጠቱ አስፈላጊ ነበር።

፲፪ እናም እነሆ፣ በሔለማን እጅ የነበሩት የተቀረጹ ጽሑፎች ሁሉ ተፅፈው፣ እናም በአልማ እንዳይሄዱ ከታዘዙት በስተቀር፣ በምድሪቱ ሁሉ በሰው ልጆች መካከል ተልከዋል።

፲፫ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ነገሮች ቅዱስ ሆነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፣ እናም ከትውልድ እስከ ትውልድ መተላለፍ ይኖርባቸዋል፤ ስለዚህ በዚህ ዓመት ሺብሎን ከመሞቱ በፊት እነዚህ ነገሮች ለሔለማን ተሰጡት።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ደግሞም በዚህ ዓመት ጥቂት ወደ ላማናውያን የሄዱ ተገንጣዮች ነበሩ፤ እናም በኔፋውያን ላይ በድጋሚ ለቁጣ ተነሳስተው ነበር።

፲፭ እናም ደግሞ በዚሁ ዓመት ከሞሮኒሀ ሰዎች ጋር፣ እንዲሁም ከሞሮኒሀ ወታደሮች ጋር ለመዋጋት ከብዙ ወታደሮች ጋር በመሆን መጡ፤ ሆኖም ላማናውያን ተሸነፉና ወደራሳቸው ምድር በድጋሚ ተመልሰው ተባረሩና በብዙ ጥፋትም ተሰቃዩ።

፲፮ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ሰላሳ ዘጠነኛ የንግስና ዘመን እንደዚህ ተፈፀመ።

፲፯ እናም የአልማ ታሪክና፣ የልጁ የሔለማን፣ እንዲሁም ደግሞ የልጁ የሺብሎን ታሪክ በዚሁ ተፈፀመ።