ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፰


ምዕራፍ ፰

ላማናውያን ኔፋውያንን አሳደዱአቸውና አጠፉአቸው—መፅሐፈ ሞርሞን በእግዚአብሔር ኃይል ይመጣል—ቁጣን ለሚናገሩ እናም ከጌታ ሥራ ጋር ለሚጣሉ ዋይታ ታውጆባቸዋል—የኔፋውያን መዛግብት በኃጢያት፣ በክፋትና በክህደት ዘመን ይመጣል። ከ፬፻–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።

እነሆ እኔ ሞሮኒ፣ የአባቴ የሞርሞንን ታሪክ እፈፅማለሁ። እነሆ፣ የምፅፋቸው ጥቂት ነገሮች ብቻ ነው ያሉኝ፣ እነዚህም ነገሮች አባቴ ያዘዘኝ ናቸው።

እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ በከሞራ ከነበረው ታላቅና ከፍተኛ ጦርነት በኋላ፣ እነሆ፣ በሃገሪቱ በስተደቡብ በኩል የሸሹት ኔፋውያን ሁሉም እስከሚጠፉ ድረስ በላማናውያን ታድነው ነበር።

እናም አባቴ ደግሞ በእነርሱ ተገደለና፣ የሕዝቤን አሳዛኝ የሆነ ታሪክ ለመጻፍ እንኳ ብቻዬን ቀረሁ። ነገር ግን፣ እነሆ እነርሱ አልፈዋል፣ እናም እኔ የአባቴን ትዕዛዝ እፈፅማለሁ። እናም ይግደሉኝ አይግደሉኝ፣ ምንም አላውቅም።

ስለዚህ እፅፋለሁ እናም መዛግብቱን በመሬት ውስጥ እደብቃለሁ፤ እናም የትም መሄዴ አስፈላጊ አይደለም።

እነሆ፣ አባቴ ይህን ታሪክ ፅፏል፣ ዓላማውንም ፅፏል። እናም እነሆ፣ በሰሌዳዎቹ ላይ ቦታ ካገኘሁ እኔም እፅፈዋለሁ፣ ነገር ግን ቦታ አላገኘሁም፤ የብረት አፈርም የለኝም፣ ምክንያቱም ብቻዬን ነኝና። አባቴና ዘመዶቼ ሁሉ በጦርነት ተገድለዋል፤ እናም ወዳጆችም ሆኑ የምሄድበት የለኝም፤ እናም ጌታ ምን ያህል በህይወት እንድቆይ እንደሚፈቅድልኝ አላውቅም።

እነሆ፣ ጌታችን እናም አዳኛችን ወደ ምድር ከመጣ አራት መቶ ዓመታት አልፈዋል።

እናም እነሆ ላማናውያን ሕዝቦቼን ኔፋውያንን በሙሉ እስከሚሞቱ ድረስ ከከተማ ከተማ እንዲሁም ከቦታ ቦታ አባረሩአቸው፤ እናም ውድቀታቸውም ታላቅ ነበር፤ አዎን፣ የህዝቤ የኔፋውያን ጥፋት ታላቅና የሚያስገርም ነበር።

እናም እነሆ፣ ይህንን ያደረገው የጌታ እጅ ነው። እናም ደግሞ እነሆ፣ ላማናውያን እርስ በርሳቸው በጦርነት ላይ ናቸው፤ እናም ምድሪቱ በሙሉ የማያቋርጥ ግድያና ደም መፋሰስ ነበረባት፤ እናም ማንም የጦርነቱን ፍፃሜ አያውቅም።

እናም አሁን፣ እነሆ፣ ከላማናውያንና በምድሪቱ ላይ ይኖሩ ከነበሩት ሌቦች በስተቀር ማንም ባለመኖሩ ስለእነርሱ ከዚህ በላይ የምለው የለኝም።

እናም የሰዎቹ ክፋትም ታላቅ በመሆኑ ጌታ በህዝቡ መካከል እንዲቀሩ እስካልፈቀደላቸው ጊዜ ድረስ በምድሪቱ ከቀሩት ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት በቀር እውነተኛውን እግዚአብሔር የሚያውቅ ማንም የለም፤ እናም በምድር ገፅ ላይ የት መሆናቸውንም ማንም ሰው አያውቅም።

፲፩ ነገር ግን እነሆ፣ አባቴና እኔ ተመልክተናቸዋል፣ እናም እነርሱም እኛን አገልግለውናል።

፲፪ እናም ይህንን መዝገብ አግኝቶ ውስጡ ባሉት ጉድለቶች ምክንያት ያልኮነነው ከዚህ የበለጠ ታላቅ የሆኑ ነገሮችን ያውቃል። እነሆ፣ እኔ ሞሮኒ ነኝ፤ እናም የሚቻል ቢሆን ኖሮ ሁሉንም ነገር እንድታውቁ አደርጋለሁ።

፲፫ እነሆ፣ ይህንን ሕዝብ በተመለከተ ንግግሬን አቆማለሁ። እኔ የሞርሞን ልጅ ነኝ፣ እናም አባቴም የኔፊ ዘር ነበር።

፲፬ እናም ለጌታ ስል ይህንን መዝገብ የደበቅሁት እኔ ነኝ፤ በጌታ ትዕዛዝም የተነሳ ሰሌዳዎቹ ዋጋ የላቸውም። ምክንያቱም እርሱ በእውነት ማንም ቢሆን ጥቅም ያገኝበት ዘንድ አይቀበለውም ብሏልና፤ ነገር ግን መዛግብቱ ታላቅ ዋጋ አላቸው፤ እናም እንዲታወቁ የሚያደርጋቸው ቢኖር ጌታ እርሱን ይባርከዋል።

፲፭ በእግዚአብሔር ካልተሰጠው በስተቀር ማንም ወደ ብርሃን ሊያወጣቸው ኃይል ሊኖረው አይችልም፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ለክብሩ በቀናነት ይደረግ ዘንድ ወይንም ለጥንቱና ለረጅም ጊዜ ለተበተኑት የጌታ የቃል ኪዳን ልጆች ደህንነት እንዲሆን ፈቃዱ ነውና።

፲፮ እናም ይህ ነገር ወደ ብርሃን እንዲመጣ የሚያደርግ እርሱ የተባረከ ነው፤ በእግዚአብሔር ቃልም መሰረት ከጨለማው ወደ ብርሃን ይመጣልና፤ አዎን ይህም ከምድር ይወጣል፣ እናም በጨለማው ውስጥም ሆኖ ያበራል፣ በሕዝቡም ይታወቃል፣ ይህም በእግዚአብሔር ኃይል ይደረጋል።

፲፯ እናም ስህተት ቢኖር እነርሱም የሰው ልጆች ስህተት ናቸው። ነገር ግን እነሆ፣ እኛ ምንም አይነት ስህተት አናውቅም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር ያውቃል፤ ስለዚህ፣ የሚያስኮንነው ቢኖር በሲኦል እሳት አደጋ ላይ እንዳይሆን ይጠንቀቅ።

፲፰ እናም አሳዩኝ አለበለዚያ ትመታላችሁ ብሎ ለሚናገር—በጌታ የተከለከለውን እርሱ እያዘዘ መሆኑንም ይጠንቀቅ።

፲፱ እነሆም፣ በፍጥነት የሚፈርድ በእርሱም ላይ እንደዚሁ በፍጥነት ይፈረድበታል፤ ምክንያቱም ደመዎዙም እንደስራው ይሆናልና፤ ስለዚህ፣ የሚማታ እርሱ በድጋሚ በጌታ ይመታል።

ቅዱሳን መጽሐፍት የሚሉትን ተመልከቱ—ሰው አይምታ፣ ወይም አይፍረድ፤ ፍርድ የእኔ ናትና ይላል ጌታ፣ እናም ደግሞ በቀልም የእኔ ናት እናም እኔ እከፍለዋለሁ።

፳፩ እናም በጌታ ሥራ ላይና፣ የእስራኤል ቤት በሆኑት በጌታ የቃል ኪዳን ሕዝብ ላይ በቁጣ የሚናገርና ፀብን የሚያነሳ፣ እናም የጌታን ሥራ እናጠፋለን፣ ጌታም ከእስራኤል ቤት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አያስታውስም—በማለት የሚናገረው እርሱ ለመቆረጥና በእሳት ላይ ለመጣል አደጋ ላይ ነው፤

፳፪ ምክንያቱም የጌታ ቃል ኪዳን በሙሉ እስከሚፈፀም ድረስ ዘለዓለማዊው ዓላማው ይቀጥላል።

፳፫ የኢሳይያስን ትንቢት መርምሩ። እነሆ፣ እኔ ልፅፋቸው አልችልም። አዎን፣ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ከእኔ በፊት የነበሩት ይህችን ምድር ወርሰው የነበሩት ቅዱሳን ይጮኻሉ፣ አዎን፣ ከትቢያውም እንኳን ቢሆን ወደ ጌታ ይጮኻሉ፤ እናም ጌታ ህያው እንደሆነ ከእነርሱ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያስታውሳል።

፳፬ እናም ፀሎታቸውም ስለወንድሞቻቸውም እንደሆነ ያውቃል። እናም እምነታቸውን ያውቃል፣ ምክንያቱም በስሙ ተራሮችን ማንቀሳቀስ ይችላሉና፤ እናም በስሙም ምድርን ማናወጥ ይቻላቸዋልና፤ እናም በቃሉ ኃይልም ወህኒዎችም ወደምድር እንዲፈርሱ አድርጓል፤ አዎን፣ የጋለው ምድጃ እንኳ ሊጎዳቸው አልተቻለውም፤ የዱር አራዊትም ሆኑ መርዛማም እባቦች በቃሉ ኃይል ሊጎዷቸው አልቻሉም።

፳፭ እናም እነሆ፣ ፀሎታቸውም ደግሞ ጌታ እነዚህን ነገሮች እንዲያመጣ ለፈቀደለት ለእርሱ ጥቅም ነበር።

፳፮ እናም ማንም ሰው እነዚህ ነገሮች አይመጡም በማለት ሊናገር አይገባውም፣ በእርግጥ ይመጣሉና፣ ጌታ ተናግሮታልና፤ በጌታ እጅ ከመሬት ውስጥ ይወጣሉ፣ እናም ማንም ሊገታው አይቻለውም፤ ታዕምራቶች ቆመዋል በሚባልበትም በዚያን ቀን ይመጣል፤ እናም ይህም አንድ ሰው ከሞት እንደሚናገር አይነት ሆኖ ይመጣል።

፳፯ እናም በምስጢራዊው ሴራዎች እና በጨለማው ስራዎች የተነሳ የቅዱሳንም ደም ወደ ጌታ በሚጮሁበት በዚያን ቀን ይመጣል።

፳፰ አዎን፣ የእግዚአብሔር ኃይል ሲካድና፣ ቤተክርስቲያኖችም ሲረክሱ፣ እናም በልባቸው ኩራት በሚወጠሩበት ቀን ይመጣል፤ አዎን፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችና መምህራን በልባቸው ኩራት በሚወጠሩበት፣ የቤተክርስቲያናቸው በሆኑት ሰዎች ላይ በሚመቀኙበትም ቀን ይመጣል።

፳፱ አዎን፣ በዚያን ቀን በባዕድ ምድር ስለ እሳትና፣ ስለኃይለኛ ነፋስ፣ እናም ስለ ጭሱ ጭጋግ በሚወራበት ጊዜ ይመጣል።

እናም በተለያዩ ቦታዎችም ደግሞ ስለ ጦርነቶች፣ የጦርነት ወሬዎች እናም የምድር መናወጥ ይሰማሉ።

፴፩ አዎን፣ በምድር ገጽ ላይ ታላቅ መበከል በሚሆንበት ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም ግድያና፣ ዝርፊያና፣ ሀሰት፣ እናም ማጭበርበርና፣ ዝሙት፣ እናም ሁሉም ዓይነት እርኩሰቶች ይኖራሉ፤ በዚያም ጊዜ ብዙዎችም እንዲህ ይላሉ፥ ይህንን አድርጉ ወይም ያንኛውን አድርጉ ምንም አይደለም፣ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነቶቹን በመጨረሻው ቀን ጌታ ይደግፋቸዋልና። ነገር ግን ለእነዚህ አይነቶች ወዮላቸው፣ በመራራ መርዝ እና በዓመፅ እስራት ውስጥ ናቸውና።

፴፪ አዎን፣ በዚያን ቀን፣ ወደ እኔ ኑ፣ እናም በገንዘባችሁም ኃጢአታችሁ ይቅር ይባልላችኋል፣ የሚሉ ቤተክርስቲያናት የሚሰሩበት ቀን ይመጣል።

፴፫ እናንተ ክፉና ጠማሞች እናም አንገተ ደንዳና የሆናችሁ ህዝቦች ሆይ፣ ለራሳችሁ ጥቅም ለማግኘት ስትሉ ቤተክርስቲያንን ለምን ሠራችሁ? በነፍሳችሁ ላይ ኩነኔን ያመጣባችሁ ዘንድ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ለምን ቀየራችሁት? እነሆ፣ በእግዚአብሔር ራዕይ ላይ ተስፋ አድርጉ፤ እነሆም በዚያን ቀንም እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚፈጸሙበት ጊዜ ይመጣል።

፴፬ እነሆ፣ ጌታ በዚያን ቀን እነዚህ ነገሮች በመካከላችሁ በሚመጡበት ጊዜ በቅርቡ መምጣት ስላለባቸው ታላቅ እና አስገራሚ ነገሮች ለእኔ አሳይቶኛል።

፴፭ እነሆ፣ እናንተ እዚህ እንዳላችሁ አድርጌ እናገራችኋለሁ፣ እናም እናንተ ግን የላችሁም። ነገር ግን እነሆ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተን አሳይቶኛል፣ እናም እኔም ስራችሁን አውቃለሁ።

፴፮ እናም በልባችሁ ኩራት እንደምትራመዱ አውቃለሁ፤ እናም ከጥቂቶች በስተቀር ያማሩ ልብሶችን በመልበስ፣ በመቅናትና፣ በፀብ፣ እናም በተንኮልና፣ በስቃይ፣ እንዲሁም በሁሉንም ዓይነት ክፋቶች በመፈፀም ራሳቸውን በልባቸው ኩራት ከፍ የማያደርጉ የሉም። በልባችሁ ኩራት የተነሳ ቤተክርስቲያኖቻችሁ፣ አዎን፣ እያንዳንዱም የተበከለ ሆኗልና።

፴፯ እነሆም፣ እናንተ ገንዘብና፣ ንብረቶቻችሁን፣ እናም ያማሩ ልብሶቻችሁንና፣ የቤተክርስቲያኖቻቸሁን ማስጌጥ ከድሆች፣ እናም ከተቸገሩት፣ ከታመሙትና ከሚሰቃዩት በላይ ትወዳላችሁ።

፴፰ ራሳችሁን ለማይረባ ነገር የሸጣችሁ እናንተ የተበላሻችሁ፣ እናንተ ግብዞች፣ እናንት መምህራን ሆይ፣ ለምን ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትበክሉታላችሁ? የክርስቶስን ስም በእራሳቸው ላይ ለመውሰድ ለምን ታፍራላችሁ? በዓለም ክብር የተነሳ ከማይጠፋው ስቃይ የበለጠ መጨረሻ የሌለው ደስታ ዋጋው ትልቅ መሆኑን ለምን አታስቡም?

፴፱ እናም የተራቡና፣ የተቸገሩ፣ እናም የታረዙና፣ የታመሙ፣ እንዲሁም ስቃይ ያለባቸው በእናንተ በኩል ሳታስተውሏቸው እንዲያልፉ እየፈቀዳችሁ ህይወት በሌላቸው ነገሮች ለምን ራሳችሁን ታስጌጣላችሁ?

አዎን፣ ጥቅምን ለማግኘትና ባሏ የሞተባት ሴት በጌታ ፊት እንድታዝን፣ እናም ደግሞ አሳዳጊ የሌላቸው በጌታ ፊት እንዲያዝኑና፣ ደግሞ በእናንተ ላይም ለበቀል ከምድር የአባቶቻቸውና የባሎቻቸው ደም ወደ ጌታ እንዲጮህ ሚስጢራዊውን እርኩሰት ለምን ትሰራላችሁ?

፵፩ እነሆ፣ የበቀል ጎራዴ በላያችሁ ላይ ያንዣብባል፣ እናም የፃድቃኖችን ደም በበቀል በእናንተ ላይ የሚመልስበት ጊዜ ወዲያው ይመጣል፣ ከዚህም በኋላ ጩኸታቸውን መቋቋም አይችልምና።